July 17, 2023 – EthiopianReporter.com 

ኤልያስ ተገኝ

July 16, 2023

የተለያዩ የምግብ ምርቶች ለሸማቾች የሚቀርቡበት የሾላ ገበያ

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በመላው አገሪቱ የሚገኙ 119 የተመረጡ የገበያ ቦታዎችን መሠረት አድርጎ ይፋ በሚያደርገው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ፣ በሰኔ ወር ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የዋጋ ግሽበት 31.4 በመቶ ሲደርስ፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ 29 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስታወቀ፡፡

የሰኔ ወር ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 29.3 ከመቶ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑ ሲገለጽ፣ በግንቦት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 30.8 በመቶ እንደነበር፣ በ2015 የበጀት ዓመት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በአማካይ በየወሩ 2.2 በመቶ ይጨምር እንደነበረ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

የሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት የሰኔ ወር ጋር ሲነፃፀርም የ31.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ በሪፖርቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ ልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰጌጫዎች፣ ነዳጅ፣ ሕክምና፣ የትምህርት መሣሪያዎችና ጌጣጌጦች ላይ የተመዘገበው ጭማሪ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን በአኃዝ ደረጃ የሚመዘገበው የዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት መጠነኛ ቅናሽ እየታየበት መሆኑን የሚገልጽ ሪፖርት ይፋ ቢደረግም፣ አሁንም ውስን በሆኑ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ላይ ተለዋዋጭ ሆኖ ከሚታየው መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ በስተቀር በተለይም ምግብ ነክ ያልሆኑ ክፍሎች የዋጋ ጭማሪ እያገረሸ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሸማቾች ይናገራሉ፡፡

ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ በሚል የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳይደረግ በተለያዩ ተከታታይ ጊዜያት ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም፣ አሁንም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ እንደ አካባቢዎቹ ሁኔታ ጭማሪ እየተስዋለበት መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዘንድሮ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 37 በመቶ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሏል። ነገር ግን ከዚህ የበለጠ ዝቅ ማድረግ አለብንም፣ እንሠራለንም። ምርታማነትን ለማስፋት ዘንድሮ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር ተጨማሪ መሬት ይታረሳል። በዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ15 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ይታረሳል ማለት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርናና የገጠር ልማት የፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ታደሰ ኩማ (ዶ/ር) ከአንድ ዓመት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ያደረጉትን ጥናት መሠረት አድርገው ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት፣ የዜጎች የምግብ ዋስትና ሳይረጋገጥ ባለው የዋጋ ግሽበት የአገር ዕድገት ማሰብ አዳጋች ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የተለያዩ ምርቶች ዋጋ ከሚንርበት ምክንያቶች የመጀመርያው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ሲሆን፣ አቅርቦት ከአገር አቀፍ ፍላጎት አንፃር ዝቅተኛ በመሆኑ ለዋጋ ንረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ፍላጎትን በበቂ ሁኔታ ሊመልስ የሚችል አቅርቦት ሳይኖር ሲቀር የምርቶች ዋጋ ከፍ እንደሚል፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ቢኖረውም የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር፣ የነዳጅ ዋጋና ሌሎችም ምክንያቶች የምግብ ዋጋን በተለየ ሁኔታ ከፍ አድርጎታል ሲሉ ታደሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የገበያ ሥርዓት መዛባት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የገበያ ሰንሰለቱን ሥርዓተ አልባ አድርጎታል የሚሉት የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪው፣ በዚህም ምክንያት በምርት ቦታዎች ጭምር የደላሎች ጣልቃ ገብነት መኖሩን፣ እነሱም ጡንቻ ያላቸው በመሆናቸው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ እንደ ችግር ጠቁመው ነበር፡፡