July 17, 2023 – EthiopianReporter.com


ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ ስደተኞች መተላለፊያዎች

ዜና በመተማ በኩል ብቻ 53 ሺሕ ስደተኞች ከሱዳን መግባታቸው ተነገረ

በመተማ በኩል ብቻ 53 ሺሕ ስደተኞች ከሱዳን መግባታቸው ተነገረ

ዮናስ አማረ

ቀን: July 16, 2023

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ሳያቋርጥ በቀጠለው የሱዳን ጦርነት ሳቢያ በመተማ በኩል በሦስት ወራት ብቻ ወደ 53 ሺሕ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ገለጸ፡፡

በግጭቱ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየተሰደዱ የሚገኙት ሱዳናውያን፣ ኤርትራውያን ወይም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አሜሪካውያን፣ ሩሲያውያንና የዓረብ አገሮች ዜጎች ጭምር መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

በመተማ ዮሐንስ ከተማ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የሚዲያ ቡድን መሪ አቶ ስጦታው ጫኔ እንደተናገሩት፣ ከሱዳን እየገቡ ላሉ ስደተኞች ሦስት መጠለያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ‹‹ስደተኞቹ ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል የተሞላበት መስተንግዶ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር የሚሠሩ 19 የረድኤት ድርጅቶችም አሉ፤›› ሲሉ የስደተኞቹን አቀባበል ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ከሳምንት ቀደም ብሎ ባወጣው ሪፖርት፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር 23 ሺሕ መድረሱን አስታውቆ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ቁጥራቸው 15 ሺሕ እንደሆነ ያመለከተ ሲሆን፣ ከመተማ ሌላ በተለያዩ አቅጣጫዎች ስደቱ መቀጠሉን ይፋ አድርጎም ነበር፡፡

በዩኤንኤችሲአር ሪፖርት መሠረት 286 ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 13 ሺሕ ሱዳናውያን፣ ስምንት ሺሕ ኤርትራውያን፣ 1,232 ደቡብ ሱዳናውያንና የሌሎች አገሮች ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል፡፡ የመተማ ዮሐንስ ከተማ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን እንደገጸው ከሆነ ደግሞ 43 አሜሪካውያንና 17 ሩሲያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገሮች ዜጎችም ተስተናግደዋል፡፡

ከስደተኞቹ ቁጥር መጨመር ጋር በተገናኘ እስካሁን ዕገዛ የማቅረቡ ርብርብ በመንግሥትም በረድኤት ድርጅቶች በኩልም የቀጠለ ቢሆንም፣ ለወደፊቱ ግን ሊታሰብበት እንደሚገባ አቶ ስጦታው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በከተማውና በአካባቢያችን የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናው ይጨምራል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የሸቀጦች አቅርቦት ችግር በከተማው መከሰቱን በመግለጽ፣ ከወዲሁ እንዲታሰብበት ጠይቀዋል፡፡

ዩኤንኤችሲአር በሪፖርቱ እንዳመለከተው የመተማ ሆስፒታል ለስደተኞች ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያደረገ ነው ብሏል፡፡ ለስደተኞቹ ከጤና ምርመራና ክትትል በተጨማሪ የምገባ፣ እንዲሁም የውኃና የንፅህና አገልግሎት መስጫ እየቀረበ መሆኑን አስረድቷል፡፡