July 17, 2023 – EthiopianReporter.com 


መቀሌ ከተማ የሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት የሚገኝበት አካባቢ

ዜና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የ2015 የበጀት ድጎማ ተሟልቶ እንዳልተለቀቀለት አስታወቀ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የ2015 የበጀት ድጎማ ተሟልቶ እንዳልተለቀቀለት አስታወቀ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: July 16, 2023

በዳንኤል ንጉሤ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  የ2015  በጀት ከፌዴራል መንግሥት ከተመደበለት 13.5 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ ውስጥ፣ ለክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የደረሰው 10.4 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የትግራይ ክልል ፕላን ኮሚሽን ኃላፊ ወ/ሮ ሀንሳ ተክላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለክልሉ 13.5 ቢሊዮን ብር በጀት ቢመደብም፣ እስካሁን የተላከው 10.4 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ የ2015 ዓ.ም. በጀት በመዘግየቱ የክልሉን አንገብጋቢ ችግሮች የመፍታት አቅሙን በእጅጉ እንዳዳከመው ተናግረዋል።

አክለውም በጀቱ ያልተሟላ በመሆኑ ምክንያት የክልሉን ፋይናንስ በብቃት ለመምራት በአስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮትን መፈጠሩን አስታውቀዋል። 

ወ/ሮ ሀንሳ ከፌዴራል መንግሥት ለክልሉ  በ2014 ዓ.ም. የበጀት ድልድል ባለመደረጉ ፈተናዎች ማጋጠማቸውንና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የፋይናንስ አቅም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቁመው፣ በ2013 ዓ.ም. በክልሉ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ክፍተት እንደነበረና ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ በአስተዳደሩ ላይ ያሳደረው ጫና በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሰዋል። 

ለፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ የገንዘብ ድጎማ ጥያቄ ቢቀርብም፣ በገንዘብ ዕጦት ምክንያት እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠ ምንጮችም ገልጸዋል። በመሆኑም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን ባለመቻሉ በክልሉ የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካጋጠመው የፋይናንስ ችግር አኳያ በ2015 በጀት ዓመት ያልተከፈለው ከ2016 በጀት ዓመት ጋር አብሮ እንዲመደብ፣ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡንና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ደግሞ የ2014 ዓ.ም. የድጎማ በጀት ጭምር ሊለቀቅ ይገባል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡

ድጎማ ባለመኖሩ አፋጣኝ ውሳኔ የሚሹ ወሳኝ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነባቸው ወ/ሮ ሀንሳ ተናግረዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ እንዲመልስ ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የሚያስችል የገንዘብ አቅም እጥረት በመኖሩ ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስ ጉዳዮችን በመምራት ረገድ በርካታ መሰናክሎች እያጋጠሙት ስለሆነ፣ የ2015 ዓ.ም. በጀት ዘግይቶ መለቀቁ በክልሉ ወሳኝ ፕሮጀክቶችን ማቀድና ማስፈጸም እንዳይችል ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወጪውን በበቂ ሁኔታ ለመሸፈን አስፈላጊው የገንዘብ ድጋፍ እንዳላገኘ፣ በተደጋጋሚ ለፌዴራል መንግሥት አቤቱታ ቢያቀርብም በቂ ምላሽ አለማግኘቱን ወ/ሮ ሀንሳ ገልጸዋል። 

ለአንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና አጠቃላይ ልማቱን ለማረጋገጥ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ ትኩረት በመስጠት፣ የ2016 ዓ.ም. በጀት ጨምሮ የ2014 ዓ.ም. እና ያልተሟላው የ2015 ዓ.ም. በጀት እንዲለቅ ወ/ሮ አሳስበዋል።