July 17, 2023 – Konjit Sitotaw
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው የድርቅ ሁኔታ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ሲል የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡
የአለም የምግብ ፕሮግራም ትናንት ባወጣው መረጃ፤ በሶማሊያ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች፣ በኢትዮጵያ 516 ሺሕ ሰዎች እንዲሁም በኬንያ 466 ሺሕ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
በሦስቱ አገራት ድርቅ በተከሰተባቸው ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በመግባታቸው፤ በአካባቢው የምግብ ዋስትና እጦት እየተባባሰ ነው ሲልም ገልጿል።
ከ2020 መገባደጃ ጀምሮ ባሉ ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ከመደበኛው የዝናብ መጠን በታች በመጣሉ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ድርቅ ማጋጠሙን ተከትሎ፤ በእፅዋት፣ በውሃ ሃብት፣ በኑሮ እና በግጦሽ ሃብት ላይ እንዲሁም በግብርና ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገመተው፤ በአካባቢዎቹ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ድርቅ ምክንያት 23.4 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ እጥረት እና 5.1 ሚሊዮን ሕጻናት ለከፋ የምግብ እጦት መዳረጋቸውን ገልጿል።
__