July 17, 2023 – BBC Amharic 

አረንጓዴ አሻራ

17 ሀምሌ 2023, 08:17 EAT

ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም. ከንጋት ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ ለመትከል ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ ባለስልጣናት ዛሬ ለ12 ሰዓታት በሚቆየው ዘመቻ ግማሽ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዟል ይላሉ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ንጋት በሰጠው መግለጫ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ሁነት ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደተዘጋጁ የችግኝ መትከያ ቦታዎች እያመሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ በሆነው ዘመቻ ከዚህ ቀደም በክረምት ወራት ተመሳሳይ ዘመቻዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ዛሬ በሚካሄደው ዘመቻ መንግሥት 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ “ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና መንደሮች ከአምናው የበለጠ በመትከል የየራሳቸውን ሪከርድ እንደሚሰብሩ እናምናለን። እያንዳንዳችንም የየራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን” ብለዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት 2011 ዓ.ም. የክረምት ወራት ላይ መንግሥት 20 ሚሊዮን ሕዝብ በተሳተፈበት ዘመቻ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አሃዝ በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።

ዛሬ ለመትከል ከታሰበው ግማሽ ቢሊዮን ችግኝ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው፣ 263 ሚሊዮን ችግኝ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚተከል ይሆናል።

በተጨማሪም 142 ሚሊዮን ችግኞችን በአማራ ክልል፣ በደቡብ 60 ሚሊዮን እንዲሁም በትግራይ ክልል 20ሺህ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት በማሕበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም። ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው። ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን ፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን፤ በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው።

እኔ ነገ በተደጋጋሚ ለመትከል ተዘጋጅቻለሁ። እናንተስ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ጽሑፋቸው ዕቅዳቸው ክብረ ወሰን መስበር መሆኑን ቢገልጹም ኢትዮጵያ ጊነስ ዎርልድ ሬኮርድስ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ለመጠየቅ እቅድ ይኖራት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

በጊነስ ተመዝግቦ ያለው ከፍተኛ የችግኝ ተከላ እአአ 2016 ላይ በሕንዷ ኡትራ ፕራዴሽ ግዛት በአንድ ቀን የተተከሉት 50 ሚሊዮን ችግኞች ናቸው።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ በ20ኛ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 35 በመቶ የሚሆነው በዛፍ የተሸፈነ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ አሃዝ ከ4 በመቶ የሚሻገር አይደለም።