ጥቃት የደረሰበት የክሪሚያ ድልድይ

18 ሀምሌ 2023, 07:43 EAT

ሩስያን ከክሪሚያ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ ጥቃት ከደረሰበት ከአንድ ቀን በኋላ በከፊል መከፈቱን ሩስያ አስታወቀች።

ለተሽከርካሪዎች በተወሰነ መልኩ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ነው ባለስልጣናቱ ያስረዱት።

ተሽከርካሪዎች የድልድዩን አንደኛውን ክፍል እየተጠቀሙ መሆናቸውንም ቪዲዮዎችን ያጋሩ አንድ ባለስልጣን ተናግረዋል።

በድልድዩ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በመዝናናት ላይ የነበሩ ሁለት ባልና ሚስት ሲገደሉ እንዲሁም ሴት ልጃቸው ቆስላለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከባህር ላይ በተነሱ የዩክሬን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ነው ስትልም ሩሲያ ከሳለች።

በዩክሬን ወደቦች በኩል ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የሚላከው የእህል ስምምነትን ሩሲያ ለማራዘም ፈቃደኛ አለመሆኗን ያስታወቀች ሲሆን ነገር ግን ይህ ጥቃት የበቀል እርምጃ ሊሆን ይችላል የሚለውንም አስተባብላለች።

በድልድዩ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የመሰረተ ልማት አንዱ በሆነው ትራንስፖርት ላይ የተፈጸመው የሽብር ተግባር ነው በማለትም የሩሲያ መንግሥት አውግዟል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም አገራቸው ለዚህ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።

የዩክሬን ሃይል በአዴሳና በሌሎች ደቡባዊ ግዛቶች ላይ ሩሲያ የአየር ጥቃት ልትፈጽም ነው ሲል አስጠንቅቋል።

በሌሊት ድልድዩን የሚያቋርጡ መኪኖችን የሚያሳይ ቪዲዮ የለጠፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማራት ኩሲኒሊን መስከረም አጋማሽ ላይ ሁለቱም የድልድዩ ክፍሎች ወደቀደመ አገልግሎት መስጠታቸው እንደሚመለሱም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በጥቃቱ ድልድዩ ቢመታም የድልድዩ ድጋፎች ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ገልጿል።

ሩሲያና የክሪሚያን ግዛት የሚያገናቸው ይህ ከርች የተሰኘው ድልድይ የመንገድና የባቡር ጉዞዎች የሚደረጉበት ሲሆን አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2018 ነው።

ክሪሚያ ዓለመ አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባልሰጠው ህዝበ ውሳኔ ሩሲያ ከዩክሬን የጠቀለለቻት ግዛት ናት።

ዩክሬን በይፋ ጥቃቱን እንደፈጸመች ባትናገርም ከውሃ በተነሱ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች)ን በመጠቀም ጥቃቱን ዩክሬን እንዳደረሰች የደህንነት መስሪያ ቤቱ ምንጭ ለቢቢሲ ሩሲያ ተናግረዋል።

እስካሁን ቢሲሲ እነዚህን ዘገባዎች የሚያረጋግጥበት የዕይታ ማስረጃ አላገኘም።

ድልድዩ ሩሲያ በኃይል በተቆጣጠረቻቸው ደቡባዊ የዪክሬን ግዛቶች ላይ ለጦሩ አስፈላጊ የመሳሪያና ሌሎች አቅርቦቶች የሚተላለፍበት ወሳኝ መስመር ነው።