
ከ 9 ሰአት በፊት
በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞችን አውሮፓ ለመድረስ የሚያቋርጧት ሰሜናዊቷ አፍሪካዊት አገር፣ ቱኒዝያ ስደትን ለመከላከል ከአውሮፓ ህብረት ጋር ስምምነት ላይ ደርሳለች።
የአውሮፓ ህብረትና ቱኒዝያ የስደተኞች ዝውውርን ለመግታትና እንዲሁም መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞችንም ለመመለስ የሚውል የ118 ዶላር የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል።
ቱኒዝያ የሜዲትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች ዋነኛ መሸጋገሪያም በመሆን እያገለገለች ይገኛል።
በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ 72 ሺህ ስደተኞች በአብዛኛው ወደ ጣሊያን ያቀኑ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትም ችግሩን ለመቋቋም እየታገልኩ ነው ብሏል።
የመግባቢያ ሰነዱ የስደተኞችን ዝውውር ለማስቆም፣ ድንበሮችን ለማጠናከር እና ስደተኞችን ለመመለስ የሚውልም 118 ሚሊዮን ዶላር ተካትቶበታል።
በቅርብ ወራት ውስጥ በቱኒዝያ ውስጥ ያሉ ጥቁር ስደተኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ጥላቻ ምክንያት ጥቃቶችን አስተናግደዋል።
የቱኒዝያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰዒድ ስደተኞች የአገሪቱን የስነ ህዝብ አወቃቀር ለመለወጥ በተዘጋጀው ሴራ ውስጥ እየተካፈሉ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ሴራው እየተቀነባበረ ያለው “ለውጭ አገራት በሚሰሩ ከዳተኞች” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንን ንግግራቸውንም ዘረኝነት አያንጸባርቅም ብለዋል።
- 1999 የተመረተ አይፎን ስልክ 10.4 ሚሊዮን ብር ተሸጠ18 ሀምሌ 2023
- ጥቃት የደረሰበት የክሪሚያ ድልድይ በከፊል መከፈቱን ሩስያ አስታወቀች18 ሀምሌ 2023
- በሕጋዊ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዴት ማቅናት ይቻላል?15 ሀምሌ 2023
ቱኒዝያ በከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን አገሪቷን ለቀው ወደ አውሮፓ ለመሄድ እየሞከሩ ያሉ ቱኒዝያውያንም ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
የአውሮፓ ህብረት እና የቱኒዝያ ስምምነት በድንበር ላይ ያሉ ስደተኞች “ሰብዓዊ መብታቸው ሙሉ በሙሉ ይከበራል” እንዲሁም ለስደተኞቹ ህጋዊ መንገዶችን ለማመቻቸትም ይፈልጋል የሚል አንቀጽ ሰፍሮበታል።
የአውሮፓ ህብረት “ስልታዊ እና ሁሉን አቀፍ” ሲል የገለጸው ይህ ስምምነት የቱኒዝያን የምጣኔ ኃብት እድገት፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች የሚተገበርበት እንዲሁም በትምህርት፣ በምርምር እና በፈጠራዎች ላይ የተደረገ ትብብር የተደረገበት ነው ብሏል።
ስምምነቱን ለመፈረም የጣሊያን እና የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በቱኒዝ የተገኙት የአውሮፓ መሪዎች ስደትን ለመቋቋም “አስፈላጊ እርምጃ” ያሉት ሲሆን እንዲሁም “የቱኒዝያን ህዝብ የሚጠቅም” ስምምነት ማለታቸውንም ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አስነብቧል።