ፔንታገን

ከ 9 ሰአት በፊት

ፔንታገን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደራዊ የኢሜል መልዕክቶች በስህተት የሩሲያ አጋር ወደሆነችው ማሊ መላኩ ተገለጠ።

መልዕክቶቹ መጨረሻው ‘. mil’ ወደተሰኘ ኢሜል መላክ ሲገባቸው በስህተት ‘.ml’ ወደሚል አድራሻ በመሄዳቸው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ለዓመታት የአሜሪካን ወታደራዊ ኢሜል ስትቀብል ከርማለች።

አንዳንዶቹ ኢሜሎች የይለፍ ቃል፣ የሕክምና ታሪክ እና የከፍተኛ ወታደሮች የጉዞ ዝርዝር መረጃ የተካተተባቸው ናቸው።

ፔንታገን ይህን ስህተት ለማስተካከል እርምጃ መውሰዱን ገልጧል።

ፋይናንሻል ታይምስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን ሲዘግብ ከ10 ዓመት በፊት አንድ ኔዘርላንዳዊ ጉዳዩን ይዞት እንደነበር ፅፏል።

ዮሐንስ ዙርቢዬር፤ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ የማሊን ‘ዶሜይን’ ለማስተካከል ኮንትራክት ተቀብሎ እየሠራ ቢሆንም ከቅርብ ወራት ጀምሮ ግን በርካታ ያለአድራሻቸው የተላኩ ኢሜሎች መቀበሉ ተነግሯል።

ከተላኩት ኢሜሎች መካከል አንዳቸውም ሚስጥራዊ መረጃ የሚል ርዕስ የተሰጣቸው ባይኖሩም ጋዜጣው እንደዘገበው በርካታ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ይዘዋል።

የወታደራዊ ካምፖች አድራሻ፣ የሕክምና መረጃዎች፣ የፋይናንስ መረጃዎችና የከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የጉዞ ዕቅድና መልዕክቶች ተገኝተዋል።

ዙርቢዬር በያዝነው ወር ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉዳዩን ለማሳወቅ ደብዳቤ ፅፏል።

ደብዳቤውን ከማሊ መንግሥት ጋር ያለው ውል ሊጠናቀቅ ስለሆን “የዩናይትድ ስቴትስ ጠላቶች መረጃውን ሊያገኙት ይችላሉ” በሚል ስጋት ነው።

የማሊ ወታደራዊ አገዛዝ ከሰኞ ጀምሮ እኒህን የኢሜል መልዕክቶች የመመልከት ዕድል ይኖረው ነበር።

ኔዘርላንዳዊው የቴክኖሎጂ ሰው ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ ነው።

የወቅቱን የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት አሜሪካ “ከፍተኛ ሚስጢር” ያዘሉ ወታደራዊ መረጃዎች በሌላ ቴክኖሎጂ ስለትምትልክ በጠላት እጅ ሊወድቁ አይችሉም።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መሥሪያ ቤታቸው ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ አንድ የኢሜል መልዕክት በተሳሳተ ዶሜይን ሊወጣ ሲሞክር እንዲታገድና ለላኪው ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው እንደሚደረግ ገልጠዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ ሰዎች የሚፈጥሩት ስኅተት ትልቅ ስጋት ይፈጥራል።