ማሕበራዊ ሚድያዎች

ከ 4 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ አሁን ከወራት ዕገዳ በኋላ ዋና ዋና ማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ያለቪፒኤን እገዛ መጠቀም ይቻላል።

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ የተባሉት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸው ማኅበራዊ ሚድያዎች በቀጥታ አገልግሎት መስጠት ካቆሙ ሰነባብተው ነበር።

ዕገዳው የተጣለው ባለፈው የካቲት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን ውጥረት ተከትሎ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነበር።

ኔትብሎክስ የተሰኘው የበይነ መረብ መረጃ ሰብሳቢ ድረ-ገፅ በአውሮፓውያኑ ሐሙስ የካቲት 9/2023 ፌስቡክ፣ ቴሌግራም እና ቲክቶክ ኢትዮጵያ ውስጥ ክልከላ እንደተጣለባቸው አሳውቆ ነበር።

አርብ የካቲት 10 ደግሞ ዩቲዩብ ክልከላ እንደተጣለበት ኔትብሎክስ ዘግቧል። ኔትብሎክስ በወቅቱ መንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮም ይህን ያደረገው ተጠቃሚዎች ወደ ዩቲዩብ መጉረፋቸውን በመመልከት ነው ብሏል።

ቢሆንም ክልከላውን ለማለፍ ቪፒኤን መጠቀም እንደሚቻል ድረ-ገፁ በዘገባው አካቶ ነበር።

በተመሳሳይ ወቅት ቶፕ10ቪፒኤን የተሰኘው መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ተቋም በኢትዮጵያ የቪፒኤን ፍላጎት 1430 በመቶ እንደጨመረ መዘገቡ አይዘነጋም።

ኢትዮቴሌኮም በወቅቱ እኚህ ዋና ዋና ማኅበራዊ ሚድያዎች ለምን እንደታገዱ በግልፅ የሰጠው አስተያየት አልነበረም።

ቢቢሲ የተወሰኑ ማኅበራዊ ሚድያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ከኢትዮቴሌኮም ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ ነበር።

በርካታ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ክልከላዎቸን ለማለፍ ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን) መጠቀም ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል።

33 ሚሊዮን የዳታ እና ኢንተርኔት ደንበኞች ያሉት ኢትዮቴሌኮም ማኅበራዊ ሚድያዎቹ ለምን እንደተዘጉ ያለው ነገር ባይኖርም፤ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ባለፈው ሰኔ የሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው “ሁኔታው ከመሥሪያ ቤታቸው አቅም በላይ መሆኑን” መናገራቸው ይታወሳል።

የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው መሥሪያ ቤት “ያለ ቪፒኤን በይነ መረብ ማግኘት አልተቻለም” የተባለው ሐሰት ነው ሲል በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ ገልጧ ነበር።

ምንም እንኳ ባለፈው መጋቢት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሸማጋይነት በዋናው ሲኖዶስና እና የቋንቋ አካታችነትን በማንሳት ራሱን ችሎ ለመቆም በወጣው ሲኖዶስ መካከል መግባባት ቢደረስም የበይነ መረብ ዕግዱ ለወራት ዘልቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ትዊት

የበይነ-መረብ ክልከላ

አክሰስ ናው የተባለው ለኢንተርኔት አገልግሎት መዳረስ የሚሟገት ተቋም እንደሚለው፣ ብዙውን ጊዜ መንግሥታት የበይነ-መረብ ክልከላ የሚያደርጉት ተቃውሞ፣ ብሔራዊ ፈተና እና ምርጫ ሲኖር ነው።

ድርጅቱ እንደሚለው ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት 2023 እስከ ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በ21 አገራት 80 ጊዜ የኢንትርኔት መቆራረጦች አጋጥመዋል።

በግንቦት ወር በሕንድ እና በጊኒ በርካታ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ክልከላ እንደተደረገባቸው ድረ-ገፁ ይጠቅሳል።

በኢህ ዓመት በዓለም ዙሪያ የበይነ-መረብ በተለይ ደግሞ የማኅበራዊ ሚድያ ክልከላ ካደረጉ 21 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

አክሰስ ናው እንደሚገልጠው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ተነስቶ የነበረው ጦርነት ቢቋጭም መንግሥት በክልሉ የበይነ-መረብ አገልግሎት ለመመለስ ጊዜ ወስዶበታል ሲል ተችቶ ነበር።

ከትግራይ ክልል አልፎ በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች አንዳንድ የማኅበራዊ ሚድያ መድረኮች ክልከላ እንደተደረገባቸውም ድርጅቱ ይጠቅሳል።

በተጨማሪ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በአማራ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የሞባይል ስልክ አገልግሎት መቋረጥ አጋጥሞ እንደነበር ያወሳል።

ድርጅቱ ከመረጃ ቋቴ አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት 24 ጊዜ የበይነ-መረብ ክልከላዎችን አድርጓል።

ይህ ቁጥር ኢትዮጵያ በይነ-መረብ በመዝጋት ከአፍሪካ አገራት ቁንጮዋ እንድትሆን ያደርጋታል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ምያንማር፣ ኢራን፣ ሕንድ፣ ዩክሬን እና ሩሲያ በይነ-መረብ የተቋረጠባቸው አገራት ሆነው ተመዝግበዋል።

በሌላ በኩል ስታቲስታ የተባለው የመረጃ ቋት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 በይነ-መረብ በመዝጋቷ 145.5 ሚሊዮን ዶላር ከስራለች ይላል።

የአፍሪካ አገራት ከእስያ አገራት በመቀጠል በይነ-መረብ በመዝጋት ሁለተኛ ናቸው። በተለይ ደግሞ ፌስቡክ የተባለው ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ብዙውን ጊዜ ዒላማ ይደረጋል።

ቡርኪና ፋሶ ለረዥም ጊዜ ፌስቡክን በመዝጋት የሚያክላት የለም። ሩሲያ ደግሞ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ፌስቡክ እና በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ዘዴዎች ላይ ተደጋጋሚ ክልከላ አድርጋለች።

በጠቅላላው ከ2019-2023 ባለው ጊዜ በበይነ-መረብ መቆራረጥ ምክንያት የዓለማችን ምጣኔ ሃብት 42 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል።

ቶፕ10 ቪፒኤን እንደሚለው በያዝነው ዓመት [2023] በበይነ-መረብ መቋረጥ ምክንያት ኢትዮጵያ 484.4 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷን አመልክቷል።

ዓለም አቀፍ ትችት

በኢትዮጵያ መንግሥት በማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ ክልከላ መጣሉን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቅፍ የመብት ተሟጋቾች ወቀሳቸውን አሰምተዋል።

ከሁሉ ቀድመው ድምፃቸውን ካሰሙ ድርጅቶች መካከል የሰዎች ዲጂታል መብት እንዲከበር የሚሠራው አክሰስ ናው አንዱ ነው።

አክሰስ ናው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዜጎቹ የነፈገውን የማኅበራዊ ሚድያ አገልግሎት በፍጥነት እንዲከፍት ጠይቆ ነበር።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ በ2022 ‘የተባበሩት መንግሥታት ኢንተርኔት ገቨርናንስ ፎረም’ የተባለ ስብሰባ አሰናድታ መልሳ በይነ-መረብ መዝጋቷ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየትም ሰጥቷል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ክልከላው አንድ ወር ከዘለቀ በኋላ መንግሥት ዕግዱን እንዲያነሳ ጠይቆ ነበር።

የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ መንግሥት ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የጣለው ክልከላ የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና መረጃ የማግኘት መብትን የሚጋፋ ነው ማለቱ ይታወሳል።

አምነስቲ አክሎ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያ የገባቻቸው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ማዕቀፎችን ከመጣሱም በላይ ከአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚጣረስ ነው ሲል ወቅሷል።

የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄና 47 የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በወርሃ ሚያዝያ የኢትዮጵያ መንግሥት የበይነ-መረብ ክልከላውን እንዲገታ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልከው ነበር።

ደብዳቤው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በይነ-መረብን እንደ መሣሪያ እየተጠቀመ ነው ሲል በቅርቡ የተከሰቱ መቆራረጦችን ጠቅሶ ወቀሳ ይሰነዝራል።