ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ተቃውሞ ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል
የምስሉ መግለጫ,ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ተቃውሞ ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል

19 ሀምሌ 2023, 10:03 EAT

የኬንያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገውን አዲስ ግብር እና የኑሮ ውድነትን መሠረት በማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲው ለሦስት ቀናት የጠራው ተቃውሞ ዛሬ በአገሪቱ ተጀምሯል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ በጠባብ ውጤት ተሸንፈው ውጤቱን አሁን ድረስ የማይቀበሉት ራይላ ኦዲንጋ የሚመሩት የተቃዋሚው አዚሚዮ ላ ኡሞጃ ጥምር ፓርቲ ባለፉት ሳምንታት የአደባባይ ተቃውሞዎች አድርጎ ነበር።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና በሌሎች ከተሞች በተካሄዱ ተቃወሞዎች በትንሹ 10 ሰዎች በፖሊስ መገደላቸው ተዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ ተቃዋሚዎች በመንግሥት ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለማጠናከር ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ተቃውሞን ጠርተዋል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶን ጨምሮ ከፍተኛ የፀጥታ እና የደኅንነት ባለሥልጣናት የታቀደው ተቃውሞ መካሄድ እንደሌለበት በመግለጽ፣ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ሕግ አስከባሪዎች አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚውስዱ አስጠንቅቀዋል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎች በትምህርት ቤቶች አካባቢ በጦር መሳሪያ የተደገፈ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል በዛሬው ዕለት በተለይ በናይሮቢ እና በሞምባሳ ከተሞች ትምህርት ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ አዘዋል።

ፖሊስ ረቡዕ፣ ሐሙስ እና አርብ ይደረጋል ስለተባለው ተቃውሞ የቀረበለት ማሳወቂያ እንደለሌ በመግለጽ፣ በጎዳናዎች ላይ ተቃውሞ እንደማይኖር እና የሕዝቡን ደኅንነት እና እንቅስቃሴ ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል።

ምንም እንኳን ባለሥልጣናት ሕዝቡ የተለመደውን መደበኛ እንቅስቃሴውን እንዲያደርግ ጥሪ ቢያቀርቡም በዋና ከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ በእጅጉ ተቀዛቅዟል፣ የፀጥታ ኃይሎችም በስፋት ተሰማርተዋል።

ባለፈው ሳምንት እና ከዚያ ቀደም ብሎ በተለያዩ ቀናት በተካሄዱት ተቃውሞዎች የደረሰውን ሞት እና የንብረት ውድመት መንግሥት ተቃዋሚዎች በቀሰቀሱት ረብሻ የተፈጠረ ነው ሲል ከሷል።

ይህ ለሦስት ቀናት ይካሄዳል የተባለው ተቃውሞ ያሳሰባቸው የኬንያ የሃይማኖት መሪዎች ተቃዋሚዎች ያቀዱትን ተቃውሞ እንዲሰርዙ እና መንግሥትም ያዘጋጀውን የግብር ሕግ በማዘግየት ውይይት እንዲያደርጉ ሲማጸኑ ቆይተዋል።

የተለያዩ ምዕራባውያን አገራት መንግሥታትም ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚቀጥል ከሆነ አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን እንደሚችል በማሳሰብ ንግግር እንዲጀምር ጥሪ አቅርበዋል።