
19 ሀምሌ 2023, 08:47 EAT
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በሚቀጥለው ወር ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲመጡ ጠብቆ የበቁጥጥር ስር የዋመዋል ሐሳብ በሩሲያ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው የሚሆነው አሉ።
በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚፈለጉት ፑቲን ከሩሲያ ከወጡ በስምምነቱ ፈራሚ አገራት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነት ፈራሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፑቲንን ለማሰር መሞከር በሩሲያ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው የሚሆነው ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ይህንን ያሉት ቭላድሚር ፑቲን የተጋበዙበት ዓለም አቀፍ ስብስብ የሆነው የብሪክስ አገራት ጉባኤ በአገራቸው ሊካሄድ ሳምንታት ሲቀረው ነው።
የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ፑቲን ከሩሲያ ምድር ወጥተው ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ከሄዱ በተገኙበት ይታሰሩ ይላል።
ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ስትሆን፣ ተከሳሹን በመያዝ የመተባበር ግዴታ አለባት።
ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተቀብላ ታስፈጽማለች ተብሎ አይጠበቅም። አገሪቱ የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከዚህ ቀደም ሳትፈጽም ቀርታለች።
እአአ 2015 ላይ የወቅቱ የሱዳን ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦማር አልበሽር በራሳቸው ዜጎች ላይ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በሚፈለጉበት ጊዜ ወደ ደቡብ አፍሪካ ቢሄዱም በቁጥጥር ስር ሳይውሉ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
- ከቱፓክ ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ አካሄደ19 ሀምሌ 2023
- ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የማኅበራዊ ሚድያ ክልከላዋን አነሳች18 ሀምሌ 2023
- በኬንያ ዛሬ በተጀመረው የሦስት ቀናት ተቃወሞ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘጉ19 ሀምሌ 2023
ደቡብ አፍሪካ እራሷን ጨምሮ ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ቻይና እና ሕንድ አባል የሆኑበት የብሪክስን ስብሰባ በነሐሴ ወር ታስተናግዳለች።
ይህንን ስብሰባ እንዲታደሙ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጋብዘዋል። አንዳንድ ሙያተኞች ይህ ጥምረት ፈጣን ዕድገት የሚያስመዘግቡ አገራትን ያካተተ በመሆኑ የቡድን ሰባት አገራት ሌላው አማራጭ ይሆናል ይሉታል።
የደቡብ አፍሪካ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ዲሞክራቲክ አሊያንስ ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚመጡበት ጊዜ እንዲታሰሩ ባለሥልጣናትን ለማስገደድ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል።
የፍርድ ቤት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ይህንን ጉዳይ በፍጹም እንደማይደግፉት ነው። “ደቡብ አፍሪካ የፕሬዝዳንት ፑቲንን እስር ለማስፈጸም ግልጽ ችግር አለባት” ብለዋል።
“የሩሲያን ፕሬዝዳንት ለማሰር መሞከር ጦርነት ማወጅ መሆኑ ግልጽ ነው። ከሕገ መንግሥታችን ጋር በሚጣረስ መልኩ በሩሲያ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ነው” ብለዋል ራማፎሳ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ግጭት እንዲያበቃ የሁለቱን አገራት መሪዎች ካነጋገሩ የአፍሪካ አገራት መካከል ራማፎሳ አንዱ ናቸው። ይህንን የሰላም ጥረት በሚቃረን መልኩ ፑቲንን ለማሰር መሞከር ግን መዘዙ የከፋ ነው ብለዋል።
ባለፈው ወር የአፍሪካ ልዑካን ሩሲያን እና ዩክሬን ለማደራደር ጦርነቱን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱት ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካም።
የተባበሩት መንግሥታት በሩሲያ ላይ ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት አልተቀበሉትም ነበር። ለዚህም የተለያዩ ጉዳዮች በምክንያትነት ይቀርባሉ።
በበርካታ የአፍሪካ አገራት እና በሩሲያ መካከል ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ግንኙነት አለ። ከእነዚህም መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች።
ማዕቀብ የተጣለባቸው የሩሲያው ቱጃር ቪክቶር ቨክሴልበርግ የደቡብ አፍሪካውን ገዥ ፓርቲ፣ አፍሪካን ናሽና ኮንግሬስን በመርዳት ቀዳሚው እንደሆኑ ይነገራል።