በክሪሚያ የጦር መሳሪያ ማከማቻ  ፍንዳታ

19 ሀምሌ 2023, 14:46 EAT

ሩስያ በጠቀለለቻት ክሪሚያ ግዛት የጦር መሳሪያ ማከማቻ መፈንዳቱን ተከትሎ ከ2ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ።

በጦር መሳሪያ መከማቻው አቅራቢያ ከፍተኛ ቃጠሎ መነሳቱም ተከትሎ ለሰዓታት የፈጀ ፍንዳታም አስከትሏል ተብሏል።

ይህም ፍንዳታ የአራት መንደሮች ነዋሪዎችን አፈናቅሏል።

የአካባቢው ባለስልጣናትም የግዛቲቷን ደቡባዊ ግማሸ የሚያቋርጠውን አውራ ጎዳና ዘግተዋል።

በስታርይ ክሪም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ቦታ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ መንስዔም አልተገለጸም።

ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች መሰረት ዩክሬን ባደረሰቻቸው ሶስት ጥቃቶች እንደሆነ ነው።

ሩስያን ከክሪሚያ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ ከሰሞኑ ጥቃት የደረሰበት ሲሆን በዚህም በመዝናናት ላይ የነበሩ ሁለት ባልና ሚስት ሲገደሉ እንዲሁም ሴት ልጃቸው ቆስላለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከባህር ላይ በተነሱ የዩክሬን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ነው ስትልም ሩሲያ ከሳለች።

ክሪሚያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባልሰጠው ህዝበ ውሳኔ ሩሲያ ከዩክሬን የጠቀለለቻት ግዛት ናት።

የዩክሬን የደህንነትና የስለላ አገልግሎት ኤችዩአር ቃለ አቀባይ ለሃገሪቱ ብሔራዊ የመንግሥት ሚዲያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኤችዩአር ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያለችው ዩክሬን ናት በማለት በቴሌግራም መልዕክት አስተላልፈዋል የተባለው ሃሰት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በሌሊት የደረሱ ፍንዳታዎች ሩሲያ ካደረገችው ከባድ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ጋር ተገጣጥሟል።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት እነዚህ የሩሲያ ጥቃቶች ያነጣጠሩት በአብዛኛው በዩክሬን ደቡባዊ ኦዴሳ ከተማ ላይ ነው።

በርካታ የክሩዝ ሚሳኤሎች እና ኢራን ሰራሽ የሆኑ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ከጥቁር ባህር፣ ክሪሚያና ደቡባዊ ሩሲያ ግዛቶች በመነሳት ወሳኝ በሆኑ መሰረተ ልማቶች እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንም የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።

37 የሩስያ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተመትተው ቢወድቁም በርካታ ቁጥር ያላቸውም የዩክሬን መከላከያዎችን ሰብረው መግባታቸው ተገልጿል።

የኦዴሳ ባለስልጣናት እንደተናገሩት በነዚህ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውንና የመኖሪያ ህንጻዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው። በወደቡ ላይም የእህልና የነዳጅ ማከማቻዎች ጥቃት እንደደረሰባቸውም ተዘግቧል።