
19 ሀምሌ 2023, 11:45 EAT
ከዓለም አገራት ፓስፖርቶች ሁሉ በበለጠ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሯ ሲንጋፖር ፓስፖርት ‘ጠንካራው’ ሲባል፣ የኢትዮጵያ ከነበረበት ደረጃ መሻሻል አሳየ።
ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የተገኘ መረጃ የሲንጋፖር ፓስፖርትን የያዙ ሰዎች ከ227 መዳረሻዎች 192 ወደሚሆኑት ያለ ቪቫ ለመጓዝ በማስቻል ነው ከሁሉ ልቆ የተገኘው።
በዓለም ካሉ ደካማ ፓስፖርቶች መካከል የሚመደበው የኢትዮጵያ ፓስፖርት ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረበት 97ኛ ደረጃ ጥንካሬው ተሻሽሎ ወደ 83ኛ ከፍ ብሏል።
የዓለም አገራትን የፓስፖርት ጥንካሬ ደረጃን የሚያወጣው ሄንሌይ የፓስፖርቶችን ጥንካሬ የሚለካው፤ ተጓዦች በያዙት ፓስፖርት ምክንያት ቪዛ ቀድመው ሳያስፈልጋቸው ወደ ስንት አገራት መጓዝ ይችላሉ የሚለውን በማጤን ነው።
በሄንሌይ ሪፖርት ላይ ቀድሞ ቪዛ አለማስፈለግ ማለት ወደ መዳረሻ ለመጓዝ ቪዛ አለመጠየቅ አልያም በመዳረሻ ቪዛ የማግኘት መብት ማለት ነው።
ተቋሙ የፓስፖርት ደረጃን የሚያወጣው ያለ ቪዛ ለሚደረግ የጉዞ መዳረሻ አንድ ነጥብ በመስጠት ነው።
ሲንጋፖር የዓለማችን ጠንካራ ፓስፖርት ባለቤት የሆነችው ለአምስት ዓመታት መሪ ከነበረችው ጃፓን ቦታውን በመረከብ ነው።
ሙሉ በሙሉ ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በተገኘው መረጃ መሠረት የጀርመን፣ የጣሊያን እና የስፔን ፓስፖርትን የያዙ ተጓዞች ወደ 190 መዳረሻዎች ያለ ቪዛ መጓዝ እንደሚችሉ አሳይቷል።
ለበርካታ ዓመታት ቁጥር አንድ ባለ ጠንካራ ፓስፖርት ደረጃን ተቆናጣ የነበረችው ጃፓን ከኦስትሪያ፣ ከፊንላንድ፣ ከፈረንሳይ፣ ከላክሰመበርግ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከስዊድን ጋር በእኩል 189 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
- “የወገኖቻችንን አስከሬኖች እየተሻገርን ነው ሳዑዲ የገባነው” ኢትዮጵያውያን ስደተኞች19 ሀምሌ 2023
- ራማፎሳ፡ ቭላድሚር ፑቲንን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ማሰር ጦርነት ማወጅ ነው19 ሀምሌ 2023
- ከ25 ዓመት በፊት ከተፈጸመው ከቱፓክ ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በአንድ ቤት ላይ ብርበራ አካሄደ19 ሀምሌ 2023

ኢትዮጵያ
ሄንሌይ ኤንደ ፓርትነርስ የተባለው ድርጅት በ2023 ሦስተኛ ሩብ ዓመት የዓለም አገራት የፓስፖርት ጥንካሬን በሚመለከት ያወጣው በዚህ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ደረጃውን ማሻሻሉን አሳይቷል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ባወጣው የደረጃ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ፖስፖርት ከ109 ፓስፖርቶች ጋር ተነጻጽሮ በ46 ነጥብ 97ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር።
በ2023 ሦስተኛ ሩብ ዓመት ሪፖርቱ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ፓስፖርት በ47 ነጥብ ደረጃውን አሻሽሎ ከ103 ፓስፖርቶች 89ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ይህ ማለት የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች አሁን ላይ ቀድሞ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ 47 መዳረሻዎች መጓዝ ይችላሉ ማለት ነው።
ደካማዎቹ ፓስፖርቶች
በሄንሌይ የፓስፖርት ደረጃ ላይ አሁንም አፍጋኒስታን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታን እና የመን አምስቱ እጅግ ደካማ ፓስፖርት ያላቸው አገራት ሆነዋል።
በ2023 የፓስፖርት ደረጃ ከአፍሪካ ደካማ ፓስፖርት ያላቸው 10 አገራት ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ላይቤሪያ፣ ኮንጎ ሪፓብሊክ እና ቡሩንዲ ናቸው።
ባለፉት 10 ዓመታት ፓስፖርታቸው ትልቅ እድገት ያሳየ አገራትም በዚሁ ሪፖርት ላይ ተመላክተዋል።
የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ፓስፖርት ባለፉት 10 ዓመት ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ቀዳሚው የጉዞ ሰነድ ሆኗል። የአረብ ኤሜሬቶች ከነበረበት 56ኛ ደረጃ ዘንድሮ 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ቻይና እና ካምቦዲያ በተመሳሳይ ፓስፖርታቸው በዓመታት ውስጥ ጥንካሬያቸው ከጨመረ አገራት መካከል ውስጥ ተካተዋል።
የፓስፖርት ደረጃው ከቀነሱ አገራት መካከል ደግሞ ተጽእኖ ፈጣሪዎቹ ሁለት ምዕራባውያን አገራት ተጠቃሽ ናቸው።
ከአስር ዓመታት በፊት በዚህ የደረጃ ሰንጠረዥ ቁጥር አንድ የነበሩት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጊዜ ሂደት ደረጃቸው ወርዶ አሁን ላይ ዩኬ 4ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጠ አሜሪካ ደግሞ 8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የሃንሊይ ኤንደ ፓርትነርስ የ2023 የሦስተኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት ከፓስፖርት ጥንካሬ በተጨማሪ የትኞቹ አገራት ቪዛ ሳይጠይቁ ተጓዦችን ይቀበላሉ የሚለውንም አጥንቷል።
የትኛውም ተጓዥ ቪዛ ሳይስፈልገው ወይም በመዳረሻው ቪዛ በመስጠት ሙሉ በሙሉ ለተጓዦች ክፍት ከተባሉ 12 አገራት መካከል አፍሪካውያኑ ቡሩንዲ፣ የኮሞሮስ ደሴቶች፣ ጂቡቲ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ እና ሲሼልስ ይገኙበታል።
አፍጋኒስታን፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ቱርክሜንስታን ደግሞ የየትኛውም አገር ዜጋ ቀድሞ ቪዛ ሳያገኝ ጉዞ የማይፈቅዱ አገራት ሆነዋል።
የበርካታ አገራትን ዜጎችን ቪዛ ከሚጠይቁ አምስት አገራት መካከል ደግሞ ኤርትራ አንዷ ሆናለች።

የፓስፖርት ጥንካሬ የሚወሰነው በምንድን ነው?
የዓለም ባንክ እንደሚለው ከሆነ የአንድ አገርን የፓስፖርት ጥንካሬ ከሚወስኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ዜጎች የሚያገኙ የነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን ነው።
ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው አገራት ከደሃ አገራት በተሻለ ወደ በርካታ አገራት ቪዛ ቀድሞ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው መጓዝ ይችላሉ።
ከነፍስ ወከፍ ገቢ በተጨማሪ የአንድ የአገር ሁለንተናዊ ሰላም ከአገሪቱ የፓስፖርት ጥንካሬ ጋር በቀጥታ ይገናኛል።
በአንድ አገር የሽብር ጥቃቶች እና የውስጥ ግጭቶች የበረከቱ ከሆነ እንዲሁም በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ካሉ የዚያች አገር ዜጎች ዓለም አቀፍ ጉዟቸው የተገደበ ይሆናል።
ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የሌላቸው እና ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለባቸው አገራት ዜጎችም በተመሳሳይ ቪዛ የሚጠየቁባቸው መዳረሻዎች ከፍተኛ እንዲሆኑ አድርጓል።
ለማሳያም ምጣኔ ሃብታቸው የደቀቀባቸው፣ ማዕከላዊ መንግሥታቸው የተዳከመባቸው አልያም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የበዙባቸው እንደ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ያሉ አገራትን ፓስፖርት የያዙ ዜጎች በብዙ መዳረሻዎች ቪዛ ይጠየቃሉ።