
19 ሀምሌ 2023, 15:47 EAT
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ነሐሴ ወር ላይ ጆሃንስበርግ በሚካሄደው የ”ብሪክስ” አገራት የመሪዎች ጉባኤ እንደማይገኙ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አስታወቀ።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ) በሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል። አይሲሲ ይህንን ማዘዣ ያወጣው ህፃናትን ከዩክሬን ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ በመሆናቸው እንደሆነም በጊዜው ገልጿል።
ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አንዷ ፈራሚ ስትሆን በዚህም መሰረት አይሲሲ የእስር ትዕዛዝ ባወጣባቸው ፑቲንን የደቡብ አፍሪካን መሬት ከረገጡም በቁጥጥር ስር ማዋል ይጠበቅባታል።
ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካ ፑቲንን ለማሰር መሞከር በሩሲያ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው የሚሆነው ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካ በዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ አቋም እንዳላት የምትናገር ሲሆን ይህም ሁኔታ ከምዕራባውያኑም ጋር እሰጣ እገባ አስገብቷታል።
“አገራቱ በደረሱበት የጋራ ስምምነት መሰረት፣ የሩስያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ የማይገኙ ሲሆን ነገር ግን የሩሲያ ፌዴሬሽን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌይ ላቭሮቭ ይወከላሉ” በማለትም የፕሬዚዳንት ራማፎሳ ቃለ አቀባይ ጋዜጣዊ መግለጫ አትቷል።
ደቡብ አፍሪካና ሩስያ በምህጻሩ ብሪክስ በመባል የሚታወቀው ቡድን አባላት ናቸው። በፈጣን የምጣኔ ኃብት እድገት የነበሩት ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ እና ቻይና ብሪክ በመባል የሚታወቀውን ቡድን በአውሮፓውያኑ 2001 መስርተዋል።
- በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉት የሩሲያዋ ፖለቲከኛ እና የኦርቶዶክስ ካህን ባለቤት ማሪያ1 ሚያዚያ 2023
- ኢትዮጵያ አባል ለመሆን ስለጠየቀችው ‘ብሪክስ’ የምናውቃቸው አራት ነጥቦች7 ሀምሌ 2023
- ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀል ለፍርድ ይቀርቡ ይሆን?18 መጋቢት 2023
ደቡብ አፍሪካ በአውሮፓውያኑ 2009 ቡድኑን ስትቀላቀል ስሙም ብሪክስ ወደሚል ተቀየረ።
ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ጎን ለጎን የብራዚል፣ የህንድ እና የቻይና መሪዎች በጆሃንስበርግ በሚደረገው ጉባዔ ላይ ተሳታፊ ናቸው።
የብሪክስ አባል አገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይይዛሉ። አምስቱ አገራት በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ደግሞ የዓለምን 26 በመቶ ይሸፍናል።
ይህ ምጣኔ ሃብታቸውም በየጊዜው እየጨመረ በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ይህንን ኅብረት ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል እና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን ማሳወቃቸው ይታወሳል።