
19 ሀምሌ 2023, 15:20 EAT
በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ውጤቱ ያስመዘገብኩት በጥረቴ እና በፈጣሪ እርዳታ ነው አለች።
የመጀመሪያውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናን ከወሰዱ 150 ሺህ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 40.65 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
ከእነዚህም ውስጥ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ነቀምት ካምፓስ ተማሪ የሆነችው ኦብሲኔ ጋሮማ “በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ውጤት” ማስመዝገቧን ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።
በነርሲንግ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዋ ኦብሲኔት፣ ከ100 ከተያዘው የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና 99 ነጥብ ማስመዝገቧን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ቢቢሲ በአጠቃላይ በፈተናው ከፍተኛው ውጤት የሚባለው ምን ያህል እንሆነ እና እንደ ኦብሲኔ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ስንት እንደሆኑ ለማወቅ አልቻለም።
በዚህ ፈተና ለስኬት የበቃሁት “በፈጣሪዬ ነው። እኔም ተማሪ እንደመሆኔ ግዴት ስላለብኝ በደንብ ነው የተዘጋጀሁት” ብላለች።
ኦብሲኔት እንደምትለው የጤና ተማሪዎች ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከምርቃት በፊት ለፈተና እንደሚቀመጡ አስታውሳ፣ አሁን ደግሞ አገር አቀፍ የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ስታውቅ ለፈተናው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ስትዘጋጅ እንደቆየች ገልጻለች።
“በአጠቃላይ መውጫ ፈተና ለጤና ተማሪዎች ከባድ ይሆናል ብዬ አላስብም” የምትለው ኦብሲኔ “የተማርኩትን ነው የተፈተንኩት። …በችሎታዬም በፈጣሪዬም እተማመን ነበር” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
- የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ ያለፉት 40 በመቶ መሆናቸው ተገለጸ15 ሀምሌ 2023
- “የወገኖቻችንን አስከሬኖች እየተሻገርን ነው ሳዑዲ የገባነው” ኢትዮጵያውያን ስደተኞች19 ሀምሌ 2023
- የሴንጋፖር ፓስፖርት የዓለማችን ‘ጠንካራው’ ሲባል፣ የኢትዮጵያ ደግሞ ደረጃው ተሻሻለ19 ሀምሌ 2023
ትምህርት ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ይፋ ባያደርግም ፈተናውን ከወሰዱ ከከግማሽ በታች የሚሆኑት ናቸው የማለፊያ ነጥብ ማምጣት የቻሉት።
ለፈተና ከተቀመጡት የግል የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ደግሞ የማለፊያ ነጥብ ከሆነው ከ50 ነጥብ በላይ ማስመዝገብ የቻሉት 17.2 በመቶው ብቻ ናቸው።
በአገሪቱ ካሉት ከፍተኛ የግል የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ተማሪው ኦብሲኔት በፈተናው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ተከትሎ ለሁለተኛ ዲግሪ ነጻ ትምህርት ዕድል በተቋሙ እንድትማር ስኮላርሺፕ ሰጥቷታል።
ኦብሲኔት ስለተሰጣን የትምህርት ዕድል ደስተኛ መሆኗን በመግለጽ፣ ነገር ግን ስኮላርሺፑን ስለመቀበሏ ግን ገና አለመወሰኗን ለቢቢሲ ተናግራለች።
“በዚያ ዩኒቨርሲቲ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። በጣም ጥሩ የሚባል ውጤትም ነበረኝ” የምትለው ኦብሲኔት፤ እንዲሁ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷም ጥሩ ውጤት እያስመዘገበች እዚህ መድረሷን ታስታውሳለች።
ይህ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ላለመፈተን ተማሪዎች ጥረቶችን ቢያደርጉም ትምህርት ሚኒስቴር ግን የትምህርት ጥረት አንዱ ማረጋገጫ በመሆኑ ሁሉም ተመራቂ ተማሪ ፈተናውን መውሰድ ግዴታቸው ነው በሚል ፈተናው እንዲሰጥ አድርጓል።
በመጀመሪያ ዲግሪ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ማለፊያ ነጥብ ማምጣት ያልቻሉ ተማሪዎች፣ ከስድስት ወራት በኋላ በድጋሚ ፈተናውን መውሰድ እንደሚችሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።