የችሎት መዶሻ

ከ 9 ሰአት በፊት

በእነዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተከሳሾች ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሲሆን፣ ተከሳሾቹን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን የቀረቡ ዘገባዎች እንዲነሱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ከዚህ ቀደም በዋስትና ጥያቄው ዙሪያ የተከሳሽ ጠበቆች እና ዐቃቤ ሕግ ያቀረቡትን ክርክር መሠረት አድርጎ ነው ውሳኔ የሰጠው።

በቀደመው ችሎት የተከሳሽ ጠበቆች የተከሳሾች የዋስትና ጉዳይ መታየት ያለበት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ሳይሆን የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ እና በሕገ መንግሥቱ መሆን እንዳለበት እንዲሁም የቀረበባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም በማለት ተከራክረው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ተሳታፊ በመሆን፣ የሽብር ድርጊት በመምራት፣ በማደራጀት አላቸው ባለው ተሳትፎ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና የተከሰሱበት አንቀጽ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲሆን ተከራክሮ ነበር።

ከተከሳሾች ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ችሎቱ በዛሬው ዕለት ውድቅ አድርጎ ተከሳሾች በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በመሆን ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የችሎቱ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች “ፊታቸውን በማዞር፣ በጭብጨባ እና በዝማሬ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን” ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።

ከተከሳሾች መካከል መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ እና ገነት አስማማው የተባሉት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው፣ ጉዳያቸው በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ እንዲታይ በጠበቆቻቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ነገር ግን ዐቃቤ ሕግም ግለሰቦቹ የተከሰሱት ከጋዜጠኝነት ሙያቸው ጋር በተያያዘ ሳይሆን “የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነው” በማለት ለችሎቱ ማስረዳቱ ተገልጿል።

ችሎቱ በተጨማሪም ተከሳሾችን በተመለከተ የመንግሥት እና የፓርቲ መገናኛ ብዙኃን ከፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠን መግለጫ መሠረት በማድረግ ምሥላቸው ከጦር መሳሪያዎች ጋር ተቀናብሮ ያቀረቧቸው ዘገባዎች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ)፣ ፋና ቴሌቪዥን፣ አማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን (አሚኮ)፣ ኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙኃን (ኦቢኤን) እና ዋልታ ቴሌቪዥን ዘገባዎቻቸውን ከበይነ መረብ መድረኮቻቸው ላይ እንዲያነሱ ትዕሳዝ ሰጥቷል።

በዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ መዝገብ የተከሰሱት 51 ሰዎች ሲሆኑ፣ በዛሬው ችሎት የቀረቡት ግን 23ቱ ናቸው። ለተቀሩት ተከሳሾች ፖሊስ መጥሪያ በማድረስ በሐምሌ 25/2015 ዓ.ም. በሚኖረው ቀጣይ ቀጠሮ እንዲገኙ አዟል።