
19 ሀምሌ 2023
ቢቢሲ በሳዑዲ አረቢያ በስደት የሚኖረውን ያህያን ሲያነጋግረው በእግሩ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ገና እያገገመ ነበር።
ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለስደት ከወጣ አምስት ወራቶች ያስቆጠረው ያህያ፣ እግሩን በጥይት የተመታው የሳዑዲን ድንበር ለማቋረጥ ሲሞክር እንደሆነ ይናገራል።
ያህያ ሳዑዲ ከመድረሱ አስቀድሞ ወደ የመን ነው የተሰደደው።
በየመን ደላሎች ይዘው ካቆዩት በኋላ ድንበር ተሻግሮ ወደ ሳዑዲ የሚገባበት ቀን ሲደርስ ከሌሎች ስደተኞች ጋር በመሆን በተከፋይ መንገድ መሪዎች አማካይነት ጉዞ ጀመሩ።
እጅግ አስቸጋሪውን የበረሃ ጉዞ በረሃብ እና በጥማት ተጎድተው ከተጓዙ በኋላ ያጋጣማቸው ነገር ከሞት ጋር የሚያጋፍጥ ከባድ ፈተና ነበር።
ከሳዑዲ ድንበር በተወሰነ ርቀት ላይ የአገሪቱ ድንበር ጠባቂ ወታደሮች ከክላሽ እስከ ዲሽቃና ሞርታር ታጥቀው ከፊት ለፊታቸው በከባድ ጥበቃ ላይ ነበሩ።
“የአንድ ሰዓት መንገድ ሲቀረን ከርቀት ነበር ያዩን። እኔ አንድ በመንገድ የደከመች እህታችንን ተሸክሜ ለመሻገር ነበር ያሰብኩት። እሷን ተሸክሜ ከኋላ ቀርቼ ስለነበርኩ ሲተኮስብን ተመታሁ።”
ያህያ በጥይት ፍንጣሪ መመታቱ እና መቁሰሉ ወደ ሳዑዲ ድንበር ከመገስገስ አላስቆመውም።
ከኢትዮጵያ ሲነሱ ጀምሮ በየመንገዱ በደላሎች፣ በሽፍቶች እና በታጣቂዎች ስቃይ እየደረሰባቸው፣ ገንዘብ እየተጠየቁ ሳዑዲ ድንበር ላይ የሞት ፅዋ እንደጠብቃቸው የሚናገረው ያህያ “በየበረሀው ስንት ወጣት ረግፎ ቀርቷል። በየመንገዱ እንደ እንስሳ ወድቆ የቀረው ቁጥር የለውም።
“በብዛት ዲሸቃ ነው የሚተኩሱት። ቁጥራቸው በርከት ያሉ ስደተኞች ለመሻገር ሲሞክሩ ግን ከባድ መሳርያ ሳይቀር ይተኩሳሉ” በማለት ያስረዳል።
ያህያ ከሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች እንደተተኮሰ በሚገልፀው መሳርያ እግሩ ቢመታም፣ ድንበሩን እንደምንም ተሻግሮ ወደ አገሪቱ መግባት ችሏል።
ከደረሰበት ጉዳት ለማገገምም ከአንድ ወር በላይ ሕክምና ማግኘት ነበረበት። በተደረገለት ሕክምና ዛሬ ላይ መራመድ ቢችልም ግን ትንሽ ከፍታ ቦታ መውጣት ግን ያስቸግረዋል።

ተስፋይ [ስሙን የተቀየረ ስደተኛ] ልክ እንደ ያህያ በዚህ መንገድ ያለፈ ስደተኛ ነው። ለሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ ከቆየችው ትግራይ ተነስቶ ሳዑዲ አረቢያ ከገባ ጥቂት ወራት ብቻ እንዳስቆጠረ ይናገራል።
የመን እንደገባ ወደ ሳዑዲ ለሚያሻግሩት ደላሎች እና መንገድ መሪዎች የሚሰጥ ገንዘብ ቢጠየቅም የመክፈል አቅም ግን አልነበረው። ከዚያም ክፍያውን መፈፀም የሚችልበት አቅም እስኪያገኝ እዚያው ለመቆየት ተገደደ።
እነዚህ ለክፍያ የሚሆን ገንዘብ የሚጠየቁ ስደተኞች ብሩን እስኪያገኙ ደላሎቹ በሚቆጣጠሯቸው እጅግ አስከፊ በሆኑ ማቆያ ቦታዎች እንዲቆዩ የሚደረግ ሲሆን፣ ክፍያው ከተፈፀመ በኋላ መንገድ የሚመሩ ሰዎች ተመድበውላቸው ወደ ሳዑዲ ድንበር ጉዞ ይጀምራሉ።
በዚህ መልኩ ከየመን ወደ ሳዑዲ ድንበር እንደተሻገረ የሚናገረው ተስፋይ፣ ክፍያው ሲፈጸም በመንገድ መሪዎች ድጋፍ ጉዞ ተጀምሮ ወደ ሳዑዲ ድንበር ሲደርሱ መሪዎቹ “ከዚህ በላይ እንድንመራችሁ የሚያስችል ክፍያ አልተፈፀመላችሁም” ብለው በረሃ ላይ ጥለዋቸው እንደሚመለሱ ያስረዳል።
በዚህ ሁኔታ በድንበር አቅራቢያ የተተዉ ስደተኞች በማያውቁት ተራራማ እና በረሃማ ቦታ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ለመጓዝ ሲሞክሩ ችግር ይገጥማቸዋል።
“የተወሰኑ ዕድል የቀናቸው ሳዑዲ ሲገቡ፣ አብዛኞቹ ግን መንገድ ስተው አድፍጠው ያለማስጠንቀቂያ አነጣጥረው ወደ ሚተኩሱ ወታደሮች አቅጣጫ በመሄድ የጥይት እራት ሆነው በየበረሃው ይቀራሉ” የሚለው ተስፋይ፣ እሱም ከሌሎች 14 ስደተኞች ጋር የብዙ ሰዎች አስከሬኖች እያየ ድንበሩን እንደተሻገረ ይናገራል።
- “አሰሪዬ ሠራተኛዋን ገድላት ስመለከት ራሴን ሳትኩ”- ሕይወት ከአረብ አገር ስደት በኋላ16 ሰኔ 2023
- ‘ካፋላ’: ከባርነት አይተናነስም የሚባልለት የአረብ አገራት ሕግ28 ጥቅምት 2022
- ለኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች እና ለቱጃሮች ያለዕረፍት የሚሰሩት የቤት ሠራተኞች ሕይወት29 ጥር 2023
ተስፋይን ጨምሮ በቡድን ሆነው ሲጓዙ ከነበሩ 15 ስደተኞች መካከል እሱ እና ሌላ ሁለተኛ ሰው ብቻ ናቸው ከሚተኮስባቸው ተኩስ ተርፈው ድንበር ተሻግረው ወደ ሳዑዲ መግባት የቻሉት።
ተስፋይ እንደሚለው ከሆነ ድንበር ለመሻገር በሚሞክሩት ላይ የሚተኮሰው ከሳዑዲ አረቢያ በኩል ሲሆን፣ ድንበር ጠባቂ ወታደሮቹ እንደየ ሁኔታው ከክላሽ እስከ ከባድ መሳርያ ነው የሚተኩሱት። በድንበሮቹ አካባቢም ምሽጎች አሏቸው።
ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው ከኦሮሚያ ክልል በ2011 ዓ.ም በድርቅ እና ግጭት ምክንያት ወደ ስደት የወጣ ሞሐመድ ሙሲም ሙሜ ይባላል። አሁን ላይ በየመን የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ይገኛል።
“በሳዑዲ በድንበር ላይ ስደተኞች በአየር እና በመሬት ይገደላሉ። ወገኖቻችን በየቦታው እየተገደሉ ነው፤ በድንበር ጠባቂዎች ብቻ ሳይሆን በሰው አዘዋዋሪዎች ጭምር ይገደላሉ። ሰዎች በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ናቸው” በማለት ስለሁኔታው ይናገራል።
አክሎም ኢትዮጵያውያን የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን ሲያስረዳ “እየተገደለን እና እየተደፈርን ነው። ወንዶች እንኳን ይደፈራሉ” ብሏል።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እየተታለሉ ድንበር ተሻግረው አደንዛዥ እጽ እንዲያጓጉዙ እየተደረገ መሆኑን በመግለፅም “ይህም በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች የሚገደሉ ወገኖቻችን ቁጥራቸው እንዲጨምር አድርጓል” ሲል ያስረዳል።

“አስከሬኖች ተሻግረን ነው ያለፍነው”
ያህያ በላያቸው ላይ እየተተኮሰባቸው ድንበሩን ሲሻገሩ የተሸከማት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ በሕይወት ተርፋ ዛሬ ሪያድ ውስጥ ትገኛለች። ሌሎች ሴቶች እና ወንዶች ግን ተመትተው ሲወድቁና ሲሞቱ ተመልክቷል። ከእነሱ በፊት ለመሻገር ሲሞክሩ በጥይት ተመትተው በረሀው ላይ የቀሩ በርካታ አስከሬኖች ማየቱንም ይናገራል።
“አስከሬን ሞልቷል። ከጭነት መኪና የተራገፈ ድንጋይ ነው የሚመስለው። የሞተውን አልፈን ነው የምንሄደው። አንዳንዶቹ ሸክማቸውን እንደያዙ፣ ሌሎቹም እንዲሁ በአንድ ላይ ተደራርበው ወድቀው አስከሬናቸውን የበረሃው ፀሐይ እያነደደው አይተናል። ብዙ ናቸው።”
በበረሀው ከወደቁ አስከሬኖች መካከል አብዛኞቹ የሴቶች እንደነበሩ የሚናገረው ያህያ፣ ከእሱ ጋር ተመትተው ቆስለው ድንበሩን መሻገር የቻሉ አራት ሰዎች እንዳሉም ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከድንበር ጠባቂ ወታደሮች በማይተናነስ መልኩ ደላሎቹ በስደተኞቹ ላይ የሚያደርሱት ስቃይ እና እንግልት ከባድ እንደሆነ የሚናገረው ተስፋይ በበኩሉ፣ ዕድሜያቸው እስከ 12 የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም የዚህ ሰለባ መሆናቸውን ሲሆኑ ማየቱን ይገልፃል።
ደላሎቹ ካለምንም ርህራሄ በዕድሜ ያልደረሱትን ጭምር ከአገራቸው እንዲወጡ በማድረግ የመን ውስጥ እያጎሯቸው መሆኑን በመጥቀስ፣ ከየመን ወደ ሳዑዲ ለመሻገር ሲሞክሩ የጥይት እራት ሆነው እየቀሩ ናቸው ይላል።
አክሎም “እኔ ድንበሩን ስሻገር በቁጥር መግለፅ የማልችለው የአካባቢዬ ሰዎች አስከሬን ሳይቀር ነው ያየሁት። ቀድመውን ለመሻገር ከሞከሩት ስደተኞች እንዲሁም ከእኛ ጋር ከነበሩ በርካቶች ተመትተው ሞተው እያየን ነብሳችንን ለማዳን ስንሮጥ ነበር” ሲል ያጋጠመውን ያስታውሳል።
- “ወንጀል ሳይፈጽሙ የመታሰር ያህል ነው” በአሠሪዎቻቸው የሚበዘበዙ ስደተኞች ሰቆቃ28 ሚያዚያ 2022
- ለሥራ ወደ ውጭ አገራት ለሚሄዱ ምን ታስቧል፣ ምንስ አሳሳቢ ነገር አለ?28 ሚያዚያ 2023
ከዚህ ሁሉ ዋጋ በኋላስ?
ሕይወቱን በሞት ቁማር አስይዞ አስከሬኖችን ተሻግሮ የሳዑዲ አረቢያን ድንበር እንደተሻገረ የሚናገረው ተስፋይ፣ ያን ሁሉ ሰቆቃ አልፎ በአሁኑ ጊዜ በሐዘን እና ቁጭት ውስጥ ይገኛል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሳው ወደ ስደት ከመነሳቱ በፊት ሲሰማ እና ሲያስብ የነበረውን ሁኔታን ሊያገኝ አለመቻሉ ነው።
“እዚህ ያለው ሁኔታ እንደጠበቅኩት አይደለም። ሥራ የለም። በፀሐይ እየነደድን ነው። አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው። በየት በኩል ይገኝ ይሆን እንጂ የምመለስበት ዕድል ባገኝ በፍፁም አላመነታም ነበር። ቁጭቱ ሊወጣልኝ አልቻለም” ሲል ስላለበት ሁኔታ ይናገራል።
ዛሬ በስደት አገኘዋለሁ ብሎ የጠበቀውን እና ሲሰማው የነበረውን ማግኘት አልቻለም። ይልቁንም በረሃ ላይ ምግብ እና ውሃ እንዲሁም መጠለያ በሚገባ ሳያገኝ፣ ዕድሉ ሲገኝ የቴምር ዛፍ የመንከባከብ ሥራ እየሰራ ይገኛል።
ከአገር ቤት ሲነሳ የነበረው መረጃና ተስፋ አሁን በመሬት ላይ ከጠበቀው ጋር ፈፅሞ ሊጣጣምለት እንዳልቻለ የሚናገው ያህያም፣ ልክ እንደ ተስፋይ ካለበት ለመድረስ የከፈለውን ዋጋ ያህልም ባይሆን አሁን ያለበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራል።
እሱ እና ተስፋይ እንደሚሉት መንግሥት ዜጎቹ በሳዑዲ አረቢያ ስላሉበት እጅግ አስከፊ ሁኔታ መረጃ ሳይኖረው ቀርቶ ሳይሆን “ለጉዳዩ ትኩረት ካለመስጠት እና ለዜጎቹ ካለ መቆርቆር” ሺዎች በበረሀ ወድቀው እየቀሩ ነው ይላሉ።
ይቅርና በበረሀ ለሚወድቁት በሳዑዲ እስርቤቶች ስላለው አሰቃቂ የኢትዮጵያውያን ሁኔታ እንኳ አስቸኳይ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ባለመቻሉ መንግሥታቸውን ይወቅሳሉ።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ዜጎችን ሲመልስ እንደነበር ይታወቃል።
ስለግድያው ምን ተባለ?
የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን እንደመሸጋገሪያ በሚጠቀሙበት የየመን እና የሳዑዲ አረቢያ ድንበር ላይ በርካታ ስደተኞች በሳዑዲ የፀጥታ ኃይሎች ሆን ተብሎ እየተገደሉ መሆኑን ‘ሚድል ኢስት አይ’ የተባለው የዜና ድረ-ገፅ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር’ (MMC)] የተባለው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጥናት እና ትንተና መረብ ሐምሌ 5/2023 እ.ኤ.አ ያወጣውን አዲስ ጥናት መሠረት በማድረግ ድረ-ገጹ ባጠናቀረው ዘገባ ላይ “ሥራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በስናይፐር እና በሞርታር ኢላማ ሆነዋል” ብሏል።
የግድያው ሰለባ የሆኑት ስደተኞች በኢኮኖሚ ችግር እና በጦርነት ሳቢያ ከአገራቸው በመፈናቀል ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ፣ ከዚያም በአደገኛ ሁኔታ በባሕር ወደ የመን፣ በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በየብስ ለመሻገር ሲሞክሩ በድንበር በጠባቂዎች እየተገደሉ መሆናቸውን የ‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሰንተር’ መረጃ ያመለክታል።
የሳዑዲ-የመን ድንበር በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደገኛ እየሆነ መምጣቱ የሚነገር ሲሆን፣ ከጥር 1 እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2022 በነበረው ጊዜ ብቻ ወደ 430 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው እና 650 መቁሰላቸው ‘ሚድል ኢስት አይ’ ገልጿል።
ይህ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ተፈፀመ የተባለው ግድያ እና ጥቃት በየመን የሁቲ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት አል-ጃውፍ በሚባል መስመር ሲሆን፣ ተመሳሳይ ጥቃቶችም በሳዑዲ አረቢያ ጂዛን ግዛት መፈጸማቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ ስጋቱን የገለፀ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2022 “በስደተኞች ላይ ስለሚፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” በርካታ ልዩ ዘገባዎች አውጥቶ ነበር።
ድርጅቱ እንደገለጸውም ከተጎጂዎች መካከል 30 በመቶ ሴቶች እና 7 በመቶ ህጻናት ናቸው።
በአካባቢው ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች እርዳታ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች የተጎዱትን መርዳት አልቻሉም።
በስተደኞች ላይ በሚከፈተው ተኩስ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ሕክምና ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ የሚጥሩ ቢሆንም፣ ራቅ ባለ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሆስፒታልም አቅሙ የተገደበ ነው ይላል ዘገባው።
እንደ ‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሰንተር’ የተባለው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጥናት እና ትንተና መረብ ገለጻ እስካሁን ድረስ በግድያው እና በመብት ጥሰቶቹ ላይ ምንም አይነት ውጤታማ ምርመራ አለመካሄዱን አስታውቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በስልክ እና በኢሜይል በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በኩል ስለቀረቡት ክሶች ምላሽ እና ማብራሪያ ለመጠየቅ ባለፈው ሳምንት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢሜይል ጥያቄ ብናቀርብም፣ ይህ ዘገባ እስከ ታተመበት ቀን ድረስ ምላሽ አላገኘንም።