
18 ሀምሌ 2023
በኬንያ የዓለም መጨረሻን በጾም እየተጠባበቁ በረሃብ የረገፉ ሰዎች ቁጥር ከ400 በላይ መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።
በረሃብ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን በሚልም በሻካሆላ ጫካ ውስጥ ሲጠባበቁ ነበሩ የተባሉትን አስከሬኖች በቁፋሮ ነው የተገኘው።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ ላይ ፖሊስ ሌላ ተጨማሪ 12 አስከሬኖችን ካገኘ በኋላም የሟቾች ቁጥር ከ400 በላይ መድረሱ የተገለጸው።
በኬንያ ደቡባዊት ምስራቅ በሚገኘው ሻካሆላ ጫካ ውስጥ ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ነበሩ።
የተወሰኑት ለቀናት በመጾም በረሃብ ሲሞቱ ሌሎቹ ደግሞ በከፍተኘ ድብደባና በመታነቅ እንደሞቱም ተነግሯል።
የዚህ እንቅስቃሴ መሪ ፖል ማኬንዚ የዓለም መጨረሻ እንደተቃረበ በመስበክ ተከታዮቹ ኢየሱስን ለማግኘት የሚችሉት በረሃብ ሲሞቱ እንደሆነ አሳምኗቸዋል።
ፖል ማኬንዚ እስካሁን በይፋ አልተከሰሰም።
ባለፉት አሥርታት ብዙ አስደናቂ ሰባኪዎች ታይተዋል። የኬንያው ፓስተር ማኬንዚ ግን ይለያል።
ተከታዮቹን፣ በፍጥነት በረሃብ ሙቱና ኢየሱስን አግኙት ብሎ ያሳምናቸዋል። ያላቸውን ሳይጠራጠሩ ያደርጋሉ።
ብዙዎቹ ተከታዮቹ ታዲያ ከገጠሪቱ ኬንያ የመጡ፣ ችግር ያቆራመዳቸው ናቸው።
ያለቻቸውን ጥሪት፣ የእርሻ መሬት እና ጎጆ ለእርሱ ቤተክርስቲያን ተናዘውለት ይቺን ዓለም ይሰናበታሉ።
ፓስተሩ በአስተምህሮው ርህራሄን አያውቅም። ሕጻናት ጭምር በረሃብ እንዲሞቱ ያበረታታል።
ልጇ ‘ኢየሱስን እንዲያገኝ’ የጓጓች እናት የምትወደውን የአብራኳን ክፋይ በረሃብ ጠብሳ ሕይወቱ እንድታልፍ ታደርጋለች።
- በመቶዎች የሞቱበት የኬንያ የእምነት ቡድን አባላት እልቂት በነፍስ አድን ሠራተኛው ዐይን10 ሰኔ 2023
- ከረሃብ የተረፉት ኬንያውያን ራስን በማጥፋት ወንጀል ክስ ቀረበባቸው13 ሰኔ 2023
- የጎዳና ላይ ነጋዴ የነበረው ፓስተር ተከታዮቹን እንዴት በረሃብ እንዲሞቱ ማሳመን ቻለ?2 ግንቦት 2023
ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በረሃብ ከተረፉት መካከል 65ቱ ኬንያውያን ራስን በማጥፋት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ራሳቸውን ያስራቡት እነዚህ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከረሃብ ተርፈው በነፍስ አድን ማዕከል ውስጥ ቢገቡም ምግብ አንመገብም ብለው አሻፈረኝ ማለታቸው ተሰምቷል።
አቃቤ ህግ ከሰሞኑ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከረሃብ በህይወት የተረፉት እነዚህ ግለሰቦች የአዕምሮ እና የህክምና ምዘና እስኪደረግላቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ አመልክቷል።
ምግብ አንበላም በማለታቸውም የነፍስ አድን ማዕከሉ እነሱን ለማቆየት እንደማይቻለውም ተገልጿል።
ለአቃቤ ህግ ጥያቄውም ፍርድ ቤቱ ከሰሞኑ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የብሪታንያ ቅኝ ገዥዎች ባወጡትና ኬንያ በምትተዳደርበት ህግ መሰረት የራስን ህይወት ማጥፋት ወንጀል ነው።