July 19, 2023 – Konjit Sitotaw
ለአማራ ብሔራዊ ክልልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ኃይል ፓሊስ አባላት የተላከን ዱቄት ሸጠው ለግላቸው ጥቅማቸው ያዋሉ የጎንደር ከተማ የሥራ ሃላፊዎች በጽኑ እሰራት መቀጣታቸው ተገለጸ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ሀይል ፓሊስ መምርያ የሚኒሊክ ክፍለጦር የሎጀስቲክ ኃላፊ የሆነው 1ኛ/ተከሳሽ ኮማንደር ኡስማን መሐመድ፤ ለልዩ ኃይል ፓሊስ አባላት አገልግሎት የሚውል 199 ኩንታል “የፊኖ ዱቄት” ከፓሊስ ኮሚሽን ከልዩ ሀይል መምርያ ዘርፍ ይረከባል፡፡
ከዚህም ውስጥ 129 ኩንታል ዱቄት በሲኖትራክ የጭነት መኪና በመጫን፤ ጭልጋ ሰራባ ልዩ ኃይል ካንፕ ማድረስ ሲገባው፤ መስከረም 25/2015 ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ላይ ከተጫነው ዱቄት ውስጥ 80 ኩንታል ለአንዱ ኩንታል 4 ሺሕ አምስት መቶ ብር በመተመን፤ 80 ኩንታሉን በጎንደር ከተማ ለሚገኘው ለሐሮን ዳቦ ቤት በ360 ሺሕ ብር መሸጡ ተገልጿል።
ከኮማንደሩ በተጨማሪም፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፓሊስ መምርያ የ3ኛ ፓሊስ ጣቢያ ትራፊክ ፓሊስ ሆኖ የሚሰራ ዋና ሳጅን እንድሪስ ሐሰን ወንጀልን የመከላከል ኃላፊነት እያለበት ከሕዝብና ከመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የዳቦ ቤቱን ባለሀብት ሻጭ እና ገዥን በስልክ ያገናኘ እና ያስማማ በመሆኑ ወንጀለኛ ተደርጓል።
በዚህም የመንግሥት ንብረት የሆነው የዳቦ ዱቄት እየተራግፉ ባሉበት በአካባቢው በነበሩ የጸጥታ ሃይሎች እጅ ከፈንጅ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፓሊስ መምርያ የሙስና ነክ ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትህ መምርያ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች የሥራ ሒደት በጋራ በተቋቋመ የምርመራ ቡድን ምርመራው ተጣርቶ ለዞኑ ፍትህ መምርያ መላኩ ተገልጿል።
የዞን ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን መርምሮ በ10 የሰው እና የሰነድ ማስረጃ አስደግፎ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ለ/33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 31/2/ስር የተመለከተውን የመሰረተ ሲሆን፤ ክሱንም ለማዓከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል።
ጉዳዩ በክርክር ቆይቶ ሰኔ 15 /2015 በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፤ አንደኛ ተከሳሽ ኮማንደር ኡስማን መሐመድ በአምስት ዓመት ጽኑ እሰራትና በ3 ሺሕ ብር፤ ዋና ሳጅን እንድሪስ ሐሰን በሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጽኑ እስራትና በኹለት ሺሕ ብር እንዲቀጡ መወሰኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትህ መምርያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።