ጸረ መንግሥት የአደባባይ ተቃውሞ

ከ 5 ሰአት በፊት

በኬንያ መንግሥት የጣለውን የግብር ጭማሬ ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገደሉ።

የሁለቱ ሰዎች ህይወት ያለፈው ረቡዕ ሐምሌ 13/ 2015 ዓ.ም ኪሱሙ ከተማ በነበረው የአደባባይ ተቃውሞ ነው።

በመዲናዋ ናይሮቢ እና በባህር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳም የኑሮ ውድነት በከፋበት መንግሥት የጣለውን የግብር ጭማሬ ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞችም ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ረጭቶባቸዋል።

በተጨማሪም በርካታ ተቃዋሚዎች በጥይት ተመትተው ቆስለዋል።

በአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ጥምረት የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ለሶስት ቀናት የተጠራ ነው።

የኬንያ መንግሥትም በሁለቱ ዋነኛ ከተሞቿ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ዘግቷል።

በርካታ የንግድ ተቋማትም ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ዘረፋና ውድመት በመፍራት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

በርካቶችም ከየእለት እንቅስቃሴቻቸው ታቅበዋል።

ባለፈው ሳምንት በነበረው ተመሳሳይ ተቃውሞ 14 ሰዎች የሞቱ ሲሆን አስሩ በፖሊስ በጥይት ተገድለው ነው።

የሰብዓዊ ተሟጋች ተቋማትም ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የጸጥታ ኃይሎች ኃይልን ያለ መጠን ተጠቅመዋል በሚል ትችት አቅርበዋል።

ናይሮቢ በሚገኝ የመማሪያ ክፍልም በተተኮሰ አስለቃሽ ጭስም ከ50 በላይ ህጻናት ተጎድተው ሆስፒታል ገብተዋል።

በመላው አገሪቷ የተካሄደ ያለው የአደባባይ ተቃውሞ የነዳጅ ግብሩን በእጥፍ ያሳደገውና ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ፖሊሲን ያስተዋወቀ አዲስ የፋይናንስ ህግ መውጣቱን ተከትሎ ነው።

የአገሪቱ ፖሊስ አዛዥ ህዝባዊ ተቃውሞው ለሃገር ደህንነት ስጋት መሆኑን በመግለጽ ሁከቱን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች በመላው አገሪቱ ተሰማርተዋል ብለዋል።

በናይሮቢ እንዲሁም በሌላኛዋ ከተማ ናኩሩን ጨምሮ በአንዳንድ ከተሞች ተቃዋሚዎች መንገዶችን ዘግተው በፖሊስ ላይ ድንጋይ ወርውረዋል።

በናኩሩ በነበረው ተቃውሞ አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን ከነዚህም አራቱ በተከፈተባቸው ተኩስ ነው። ሌሎች ሁለት ግለሰቦችም በምስራቅ ማኩኒ በጥይት ተመትተው ቆስለዋል።