የሴልቲክ የወርቅ ሳንቲም

ከ 4 ሰአት በፊት

1.4 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ የሴልቲክ የወርቅ ሳንቲም ሰርቀዋል የተባሉት አራት ሰዎች ጀርመን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ባለፈው ኅዳር አንድ ምሽት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳንቲሞች ባቫሪያ ከሚገኝ አንድ ሙዚየም ተወስደዋል።

አብዛኛዎቹ ሳንቲሞች በአንደኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ ናቸው።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት “ከበቂ በላይ ማስረጃ ተገኝቷል”፤ ምርመራውም እንደቀጠለ ነው።

የወርቅ ሳንቲሞቹ ተገኝተዋል ወይ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ፖሊስ ትንሽ ጊዜ ስጡኝ ብሏል።

የባቫሪያ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ዮዋኪም ኸርማን እንደሚሉት ግለሰቦቹ ፕሮፌሽናል ሰርስሮ ገቢዎች ናቸው።

የባቫሪያ ፖሊስ አለቃ እንደገለጡት “ፖሊስ ግለሰቦቹ የዘረፉትን ንብረት ከተለያዩ ቦታዎች ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ነው።”

የተሰረቁት ሳንቲሞች በፈረንጆቹ 1999 ባቫሪያ ውስጥ ማንቺንግ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአርኪዮሎጂስቶች ቁፋሮ የተገኙ ናቸው።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ይህን ያህል ብዛት ያለው የሴልቲክ የወርቅ ሳንቲም ተቆፍሮ የተገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

ሳንቲሞቹ ከ2006 ጀምሮ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ሰው እንዲጎበኛቸው ሆነዋል።

ነገር ግን የሌባ ሲሳይ ከመሆን አልዳኑም።

ፖሊስ እንደሚለው ተጠርጣሪዎቹ የሙዚየሙን ‘አላርም ሲስተም’ መዝብረው ነው ውስጥ የገቡት።

ልክ ሰብረው ወደ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በአቅራቢያው ያለ አንድ የበይነ-መረብ ገመድ የተበጠሰ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ዳታ ማግኘት ተስኗቸው ነበር።

ይህ ማለት ‘አላርም ሲስተሙ’ አሊያም የድረሱልኝ ማሳወቂያ አይሠራም፤ በሮቹ ደግሞ ክፍት ናቸው ማለት ነው።

የድረሱልኝ ማሳወቂያ ባይሠራም ከ10 ደቂቃ በታች የወሰደውን ዝርፊያ መቅዳት ችሏል።

ባለሥልጣናቱ አሁን ለማወቅ እየጣሩ ያሉት ዝርፊያው የተደራጀ የወንጀል ቡድን ሥራ ወይስ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ዘርፊያዎች ጋር ግንኙነት ያለው ነው? የሚለውን ነው።

በ2017 100 ኪሎ ግራም የሚመዝን የወርቅ ሳንቲም በርሊን ከሚገኝ ስታድየም እንደተዘረፈ ይታወሳል።

ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ዘራፊዎች 21 ጌጣጌጦችና ሌሎች ንብረቶች ሲወስዱ በሲሲቲቪ ታይተዋል።

የሴልቲክ የወርቅ ሳንቲሞች መዘረፋቸው ሙዚየሙንና የአካባቢውን ሰዎች እግጅ አሳዝኗል።