News አማርኛ ለመቃኘት
የበቀቀ፣ የጥንቸል እና የተርብን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት ምስሎች

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምንነት አጭር ማብራሪያ

 አኒሜሽኑን ያስጀምሩ

ከዚህ ቀደም ስለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አስበው ያውቃሉ?

ባለፉት ስድስት ወራት እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ቻትቦቶች እንዲሁም የምስል ማፍለቂያ የሆኑ እንደ ሚድጆርኒ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ትኩረትን ስበዋል።

ይሁን እንጂ ኤአይ ወይም “ማሽን ለርኒንግ” [ማሽንን የማስተማር] ሥርዓቶች ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

በዚህ ለጀማሪ ተብሎ በተዘጋጀ ቀላል ማብራሪያ ላይ ከቻትቦቶች በተጨማሪ የተለያዩ ኤአይ ዓይነቶች እንዴት የየዕለት ሕይወታችንን እንደለወጡ እንመለከታለን።

ኤአይ እንዴት ነው የሚማረው (የሚሰለጥነው)?

ለኤአይ ቁልፍ ጉዳይ <ትሬኒንግ> ወይም ልምምድ የተባለ ሥርዓት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የኮምፒዩተር ሥርዓት ማብራሪያዎች እና መመሪያዎች የተጨመሩበት ከፍተኛ የሆነ መረጃን ይሰጠዋል።

አንዱ መመሪያ ለምሳሌ “የሰው ፊት የሚታይበትን ምስል ለይ” ወይም “እነዚህን ድምጾች በምድባቸው አስቀምጥ” የሚል ሊሆን ይችላል።

መመሪያው የተሰጠው ፕሮግራም በመረጃ ቋቱ ውስጥ ተመሳሳይነት ያላቸውን ለይቶ በምድብ በማስቀመጥ ዓላማውን ያሳካል።

ይሁን እንጂ አንዳንዴ በሂደቱ ውስጥ ማስተካከያዎች ሊያስፈልጉት ይችላሉ። ለምሳሌ “ይህ የሰው ፊት አይደለም” ወይም “እነዚህ ሁለት ድምጾች የተለያዩ ናቸው” የሚሉ እርማቶችን ይፈልግ ይሆናል። ከተሰጡት መረጃዎች እና ጥቆማዎች የተማረው ፕሮግራም የኤአይ ሞዴል ይሆናል። በልምምድ ወቅት ለኤአይ የሚሰጠው የመረጃ ጥራት የኤአይ አቅምን ይወስናል።

ይህ የልምምድ ሥርዓት እንዴት የተለያየ ዓይነት ኤአይ ሊፈጥር እንደሚችል ለመገንዘብ የተለያዩ እንስሳትን ማየት ሊጠቅም ይችላል።

በሚሊዮን ዓመታት ውስጥ በተፈጥሯዊ የአካባቢ ሁኔታ ምክንያት እንስሳት የተለያዩ ብቃቶችን እንዲያዳብሩ አስችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኤአይ ልምምዶች ኤአይ የሚሠራበትን እና የሚበለጽግበትን ሁኔታ ያዳብራል።

ኤአይ የተለያዩ ክህሎቶች እንዲኖሩት ያለማመድንበት ምሳሌዎችን ምንድናው?

ቻትቦትስ ምንድን ናቸው?

መንቁሩ ላይ ምልክት የተደረገበት በቀቀን

ቻትቦትን ልክ በቀቀን ተብሎ እንደሚጠራው ወፍ ያስቡት። በቀቀን ስለሚነገረው ቃላት ትንሽ ግንዛቤን በመያዝ ብቻ ስለ ቃሉ ሙሉ ግንዛቤ ሳይኖረው የተባለውን ቃላት ይደግማል

ቻትቦትስ ከበቀቀን በጣም የተራቀቁ ሆነው የሰው ልጅን ሕይወት ለመቀየር ከጫፍ ይድረሱ እንጂ እንደ አእዋፉ ናቸው።

ታዲያ እነዚህ ቻትቦቶች እንዴት መጻፍ ቻሉ?

የተለያዩ ኤአይ አይነቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ‘large language models’ (ኤልኤልኤምስ) ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ እና በበርካታ ጽሑፎችን እንዲለማመድ ተደርጎ የተቀረጸ ነው።

ኤልኤልኤምስ ነጠላ ቃላትን ብቻ ሳይሆን በተሰጠው መለማመጃ መረጃ ውስጥ ካሉት ጽሑፎች ጋር በማነጻጸር ዓረፍተ ነገሮችን፣ የቃላት አጠቃቀምን ያውቃል።

በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ቃላትን እና ሐረጎችን በማነጻጸር ጥያቄዎችን አንብቦ ምላሽ መስጠት ይችላል።

አስደናቂው ነገር የጽሑፍ ኤአይ ከሰው ልጆች ድጋፍ ውጪ የሰዋሰው ሕግ ከማወቁም በላይ፣ የቃላት ትርጉምን በራሱ መረዳት ይችላል።

የባለሙያ አስተያየት፡ የቻትቦት የወደፊት ተስፋ

“በ10 ዓመታት ውስጥ በየትኛውም መስክ እንደ ባለሙያ የሚሠራ ቻትቦቶች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህም እንደ ሐኪም፣ መምህር፣ ጠበቃ እና የፈለጉት አይነት ባለሙያን የማማከር ሥራዎትን ያከናውናሉ።”

ሳም አልትማን
ሳም አልትማን – ቻትጂፒቲን የሠራው የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ከኤአይ ጋር መነጋገር እንችላለን?

አሌክሳን፣ ሲሪን ወይም ሌሎች ድምጽ የሚለዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው የሚያውቁ ከሆነ፣ ኤአይን እየተጠቀሙ ነው ማለት ይቻላል።

አሌክሳን፣ ሲሪን ወይም ሌሎች ድምጽ የሚለዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው የሚያውቁ ከሆነ፣ ኤአይን እየተጠቀሙ ነው ማለት ይቻላል።

በጆሮዋ ላይ ምልክት የተደረገባት ጥንቸል ምስል

የተለያዩ በጣም ጥቃቅን የድምጽ ልዩነቶችን መለየት የምትችልን ባለትላልቅ ጆሮዎች ጥንቸልን ያስቡ

ሲናገሩ ኤአይ ከጀርባ ያሉ ድምጾችን በማስወገድ፣ ንግግርዎን ወደተለያዩ ክፍሎች በመለያየት፣ በክምችቶቹ ውስጥ ካሉ ድምጾች ጋር በማዛመድ ድምጽዎትን ይቀርጻል።

ምላሽ ከመስጠቱ በፊት ንግግርዎን ወደ ጽሑፍ ይቀየራል፤ በዚህም በማዳመጥ ጊዜ የሚከሰቱ ስህተቶች ሊታረሙ ይችላሉ።

እንዲህ ዓይነቱ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ተፈጥሯዊ ቋንቋን ማቀናበር ተብሎ ይታወቃል።

ይህም ለአንድ ተግባር ከሚሰጡት “አዎ” ከሚለው ምላሽ አንስቶ፣ ስልክዎን ሊሄዱ ባቀዱበት ከተማ በቀጣይ ቀናት ስላለው የአየር ሁኔታ ጠይቀው መልስ አስከሚያገኙበት ዘዴ ድረስ ከጀርባ የሚገኝ ቴክኖሎጂ ነው።

ኤአይ ምስሎችን መረዳት ይችላል?

በዐይኗ ላይ ምልክት የተደረገባት ጉጉት ምስል

ስልክዎ ፎቶዎችዎን “በባሕር ዳርቻ” ወይም “በምሽት” በሚል ማኅደር ተቀምጦ አግኝተው ያውቃሉ?

ከሆነ ሳያውቁት ኤአይን እየተጠቀሙ ነው ማለት ነው። በዚህም የኤአይ ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) በፎቶዎ ላይ ያሉ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በመለየት በአንድ ላይ አስቀምጧቸዋል ማለት ነው።

ይህ ፕሮግራምም ቀላል መግለጫ ያላቸውን በርካታ ምስሎችን መሠረት በማድረግ ነው እንዲለማመድ እና እንዲለይ የተደረገው።

ምስል የሚለይን ኤአይን በርካታ ምስሎችን “ብስክሌት” የሚል መለያ ከሰጠነው፣ ብስክሌት ምን እንደሚመስል በመለየት ከመኪና እና ከጀልባ ልዩነቱን መረዳት ይችላል።

አንዳንድ ጊዜም ኤአይ በተመሳሳይ ምስሎች ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን እንዲለይ ይሰለጥናል።

የሰዎችን ገጽታ የሚለየው በእያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ ያሉ ጥቃቅን ተዛምዶዎችን በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ፊት ጋር በማነጻጸር ነው፣ የፊት ገጽታ መለያ ዘዴው የሚሠራው።

በሕክምናው በኩልም ለሕይወት አስጊ የሆኑ ዕጢዎችን ለመለየትም ተመሳሳይ ስልት ቀመሮችን መሠረት በማድረግ ነው ኤአይ እንዲሠለጥን የሚደረገው። ሐኪም ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ምስሎችን በማየት ወሳኝ መረጃን ይሰጣል።

ኤአይ እንዴት አዲስ ምስሎችን ይፈጥራል?

በቆዳዋ ላይ ባለ ገጽታ ላይ ምልክት የተደረገባት እስስት ምስል

እንደ እስስት ቀለማትን እና ሌሎች ገጽታዎችን በሚቀያይር ሁኔታ እንዲሰለጥን የተደረገ ምስል የሚለይ የኤአይ ዓይነት በቅርቡ ተሰርቷል

እንዲህ ያለው ምስል መፍጠሪያ ኤአይ ውስብስብ የዕይታ ገጽታዎችን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ፎቶግራፎች እና ሥዕሎች በመሰብሰብ ፍጹም አዲስ ምስሎችን መፍጠር ይችላል።

በማርስ ላይ የሚራመድ ሰው ምስልን የመሰሉ ፈጽሞ ያልተከሰቱ ነገሮች በፎቶግራፍ ምስል እንዲፈጥርልን ኤአይን ልንጠይቅ እንችላል።

ወይም “የእንግሊዝ እግር ኳስ አሰሠልጣኝ ፎቶን በፒካሶ የአሳሳል ዘይቤ ሥራልኝ” በማለት የምንፈልገውን የምሥል ዘይቤ ፈጠራ በተሞላበት ሁኔታ እንዲሰጠን ልናዘው እንችላል።

አዲሱ ኤአይ የሚፈጥረውን አዲስ ምስል በዘፈቀደ ከተቀቡ የምሥል ገጽታዎች በመነሳት የሥራውን ሂደት ከጥቃቅን ይዘቶች ይጀምራል።

ይህም ኤአይ በሚሠለጥንበት ወቅት ከተማራቸው ገጽታዎች መካከል ለመለየት አንዳንድ ነጠብጣቦችን በመመልከት ፍንጮችን ወስዶ የተለየ ነገርን ይሠራል።

እነዚህ ገጽታዎችም ቀስ በቀስ እየጎለበቱ ተጨማሪ የነጠብጣብ ንብርብሮችን በመጨመር የማያስፈልጉትን በማስወገድ፣ በመጨረሻም የሚፈለገው ምሥል እንዲወጣ ያደርጋል።

የማርስ ገጽ፣ ጠፈርተኛ እና መራመድን በማዋሃድ የሚፈለገውን አዲስ ምሥልን ማግኘት ይቻላል።

ምክንያቱም አዲሱ ምሥል የሚሠራው ከዚህም ከዚያም ከተወጣጡ ጥቃቅን የምሥል ክፍሎች በመሆኑ፣ ውጤቱም ከዚህ በፊት ያልተከሰተ ምሥል ይሆናል። ነገር ግን ይህ የሚመነጨው በሥልጠና ጊዜ ኤአይ ከተማራቸው በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ የምስል መዋቅሮች ነው።

ይህ ለቅጂ መብት እና በእውነተኛ አርቲስቶች፣ ዲዛይነሮች እና ፎቶግራፈሮች ከሚፈጠሩ የጥበብ ሥራዎች ሥነ ምግባር አንጻር ምን ማለት እንደሆነ የዓለም ማኅበረሰብ በአሁኑ ወቅት መነጋገር እና መጠየቅ ጀምሯል።

ያለሹፌር የሚንቀሳቀሱ መኪኖችስ?

ያለሹፌር የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን ከኤአይ ጋር በተያያዘ ለአስርታት ውይይት ሲደረግባቸው ነበር። የእነዚህ መኪኖች ሐሳብም በሳይንስ ልቦለዶች አማካይነት በሕዝቡ ሕሊና ውስጥ ተቀምጦ የቆየ ነው።

እነዚህ ያለሾፌር በራሳቸው የሚሽከረከሩ መኪኖች ካሜራ፣ ራዳር እና በጨረር የሚመራ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ናቸው።

በክንፎቹ ላይ ምልክት የተደረገበት የተርብ ምሥል

360 ዲግሪ ዙሪያ ገባውን መመልከት የሚችል እና እየበረረ አቅጣጫውን ማስተካከል እና በዙሪያው ያሉ ነገሮችን መለየት የሚያስችል ተፈጥሮ በክንፎቹ ላይ ያለውን ተርብ ያስቡ

በተመሳሳይ ኤአይ ይህንን አይነት ዘዴን በመጠቀም በዙሪያው ያሉ ነገሮች እና አካላት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይለያል። የሚንቀሳቀሱ ከሆነ መኪና፣ ብስክሌት፣ እግረኛ ወይም ሌላ ነገር ስለመሆናቸው በእንቅስቃሴያቸውን ዓይነት ለመገንዘብ ይችላል።

ኤአይ በእውነተኛው ዓለም የሚደርስ አደጋን ለማስወገድ ጥሩ መኪና የማሽከርከር ብቃት ምን እንደሚመስል እንዲረዳ እና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ ለማስቻል በሺዎች የሚቆጠር ሰዓታት ሥልጠና አድርጓል።

ቀድሞ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነው የአሽከርካሪ ሰዎችን ባህሪይን ለመረዳት ለበርካታ ዓመታት ትንበያ አጋዥ የሆነ ስልተ ቀመር ለማዘጋጀት ጥረት ሲደረግ ነበር። ነገር ግን ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ መኪኖች በእውነተኛ መንገዶች ላይ የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችን ለመረዳት የሚያስችሉ ሚሊዮኖች ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ መረጃዎችን ሰብስበዋል። አሁን አሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ሹፌር አልባ መኪኖች በክፍያ መንገደኞችን እያጓጓዙ ነው።

እነዚህ እራሳቸውን ችለው የሚንቀሰቀሱ መኪኖች፣ አዲስ ቲክኖሎጂዎች ከቴክኒክ ችግሮች ባሻገር ሌሎችንም የሰዎችን ችግሮች መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው።

የመንግሥት ሕግ እና የደኅንነት ደንቦች፣ አጠቃላይ እንቅስቃሴን በማሽን ቁጥጥር ስር ማድረግ ከሚያስከትለው የስጋት ስሜት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሳሉ። እነዚህም በራሳቸው የሚሽከረከሩ መኪኖች ወደፊት ሙሉ በሙሉ ጎዳናዎች ላይ እንዳይታዩ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ።

የባለሙያ አስተያየት፡ ከሰውም በላይ አስተማማኝ ናቸው

“ደኅንነታቸው የተጠበቀ መንገዶች እንዲኖሩን እንፈልጋለን። በአሁኑ ወቅት አንድን ተግባር በብቃት በመፈጸም የሰው ልጅ እና ሮቦቶች በአንጻራዊ ሁኔታ እየተቀራረቡ ይመስላል። እየታየ ካለው መሻሻል አንጻር አሁን እያደርግነው ያለው ውይይት ያለፈውን መለስ ብለን የምናይበት ይሆናል። ምክንያቱም ሮቦቶች ከሰዎች የተሻሉ ስለሚሆኑ፣ ብዙም የሚያነጋግረን ጉዳይ አይሆንም።”

ካይል ቮግት
ካይል ቮግት – ክሩዝ የተባለ በራሱ የሚሽከረከር መኪና አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ኤአይ ስለእኔ ምን ያውቃል?

ንቦች ያሉበት ቦታ በተለይ የሚታይበት የማር እንጀራ ምሥል

አንዳንድ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች በቁጥር የሚሠሩ ሲሆኑ፣ አሃዞችን በከፍተኛ መጠን በመሰብሰብ እና በማዋሃድ የጎላ ጥቅም ያላቸው መጠነ ሠፊ መረጃን ይፈጥራሉ።

ስለእያንዳንዳችን የገንዘብም ሆነ የማኅበራዊ እንቅስቃሴ በርካታ መረጃዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ይገኛሉ። ይህም ኤአይ ስለውሳኔያችን እና ባህሪያችን ትንበያ ለመስጠት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

በሱፐርማርኬቶች የሚሰጡን የደንበኝነት ካርዶች በየሳምንቱ በምንፈጽመው ግዢ አማካይነት ልማዳችንን እና ምርጫችንን ለመለየት ይቻላል። አበዳሪ ድርጅቶች ምን ያህል ገንዘብ እንዳለን እና ዕዳችንንም ያስከፍሉናል።

ኔትፍሊክስ እና አማዞንን የመሳሰሉ የፊልም አቅራቢ ድርጅቶች ባለፈው ምሽት ምን ያህል ሰዓት ፊልም እንደተመለከትን ይመዘግባሉ። የማኅበራዊ ሚዲያዎችም ምን ያህል ቪዲዮዎች ላይ በዕለቱ አስተያየት እንደሰጠን ያውቃሉ።

ይህ የእርስዎን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው አሃዝ ሲሆን፣ በዚህም ኤአይ ዘዴዎች ከእነዚህ መረጃዎች በመነሳት ማኅበራዊ ምርጫ ስለሆነ ጉዳይ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችላል።

በዙሪያችን እየተከናወኑ ካሉ ነገሮች አንጻር ኤአይ የዕለት ከዕለት ሕይወታችንን እየቀረጸው ይገኛል ማለት ይቻላል። ብድር ማግኘት ይችሉ እንደሆነ ከመወሰን አንጻር እና የሚያዩትን ማስታወቂያ መሠረት በማድረግ በሚፈጽሙት ግዢ ላይ ተጽእኖን ያሳድራል።

ኤአይ ሁሉንም ነገር መሥራት ይችላል?

የአንበሳ አካል፣ የጉጉት ፊት፣ የበቀቀን መንቁር፣ የጥንቸል ጆሮ እና የተርብ ክንፎች ያሉት ምሥል

ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ክህሎቶች በማዋሃድ አንድ ወጥ የኤአይ ሞዴል መሥራት ይቻላል?

ይህ በጣም በቅርቡ ከኤአይ አንጻር እየተፈጠሩ ካሉ እመርታዎች መካከል አንዱ ነው።

ይህም ዘርፈ ብዙ [መልቲሞዳል] ኤአይ የሚባል ነው። ይህም ምሥሎችን፣ ጽሑፎችን፣ ድምጾችን ወይም ቪዲዮዎችን የመሳሰሉ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን በመመልከት በመካከላቸው ያለን አዲስ አይነት አቅጣጫን ለማግኘት ያስችላል።

ይህ መልቲሞዳል የተባለው ዘዴ ከቻትጂፒቲ አንጻር ለታየው ታላቅ እመርታ አንድ ምክንያት ሲሆን፣ ሞዴሉም ጽሑፍን ብቻ ይጠቀም ከነበረው ጂፒቲ3.5 ምሥልንም ወዳካተተው ጂፒቲ4 በማደግ ነው አሁን ካላበት የደረሰው።

ይህ አንድ ወጥ የኤአይ ሞዴል የትኛውንም ዓይነት መረጃ በማቀናበር ሁሉንም ሥራዎች ማከናወን ይችላል። በዚህም ቋንቋዎችን ከመተርጎም አንስቶ፣ አዲስ የመድኃኒት ዓይነት አስከማዘጋጀት የሚደርስ ነው። ይህም ሁሉን አቀፍ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤጂአይ) በመባል ይታወቃል።

ለአንዳንዶች ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምርምር የመጨረሻ ግብ ነው፣ ለሌሎች ደግሞ በሳይንስ ልቦለዶች ላይ ያለው እና የሰው ልጅ ያልደረሰባቸው እና ያልተቆጣጠራቸው ለኅቀቶች ላይ ለመድረስ የሚያስችል መንገድ ነው ይላሉ።

ኤአይ እንዴት ነው የሚሠለጥነው?

አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኞቹን የኤአይ ዘዴዎችን የማሠልጠኑ ሂደት “ቁጥጥር የሚደረግበት መማር” (supervised learning) በመባል ይታወቅ ነበር።

ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ የሥልጠና መረጃዎች መለያ ተሰጥቷቸዋል፣ ኤአይም የመረጃዎቹን ተያያዥነት እንዲለይ ተጠይቆ ነበር።

ይህንንም ተያያዥነት ኤአይ በሌላ አዲስ መረጃ ላይ ተግባራዊ በማድረግ በመረጃው ትክክለኝነት ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎ ነበር።

ለምሳሌም ለኤአይ አስራ ሁለት ፎቶዎች ቀረቡለት፤፤ ስድስቱ “መኪና” የሚል ስም ተሰጣቸው ቀሪዎቹ ስድስት ደግሞ “ቫን” (ሌላ ዓይነት መኪና) በሚል ተሰየሙ።

ስድስት ቀይ መኪኖች እና ስድስት ነጭ ቫኖች

ቀጥሎም ኤአይ በዕይታ ያላቸውን ገጽታ በመለየት መኪኖቹን እና ቫኖቹን በሁለት ቡድኖች ለይቶ እንዲያስቀምጥ ታዘዘ።

ታዲያ ፎቶዎቹን በሁለት ቡድን እንዲለይ ሲጠየቅ ውጤቱ ምን ሆነ ብላችሁ ታስባላችሁ?

ነጭ መኪና

ከዚህ አንጻር ኤአይ ብልህ ሆኖ አልተገኘም፤ ይህ ቫን ነው ብሎ ምላሽ ሰጠ።

አሁን ደግሞ ይህንን እንዲያይ ተደረገ።

ቀይ ቫን

ኤአይ መኪና ነው ብሎ መልስ ሰጠ።

በእርግጥ ለዚህ ስህተት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከዚህ አንጻር ይህ ኤአይ እንዲለይ ተደርጎ የሰለጠነው በውስን ምሥሎች ላይ በመመሥረት በመሆኑ፣ አነስ ያለ መኪና ይሁን ቫን ለመለየት የተጠቀመው ቀለምን ነው።

የሚያስደንቀው ነገር የኤአይ ፕሮግራም በአንድ ነገር ላይ ውሳኔ የሚሰጠው በእራሱ መንገድ ነው። ነገር ግን ውሳኔው የበለጠ ትክክለኛ እንዲሆን ሰዎች ሊረዱት ይችላሉ።

ሁለቱን አዲስ ምሥሎ ለመለየት በሞከረበት ጊዜ ስህተት መሥራቱን ልናሳውቀው እንችላለን። ይህም ምሥሎቹን ለመለየት የሚያስችለው አዲስ ገጽታዎችን እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል።

ነገር ግን ከሁሉ በበለጠ ይህ ኤአይ የሚገጥመውን ስህተት በርካታ የተለያዩ ምስሎችን በመስጠት አሰልጥኖ የሚኖረውን መረጃ እንዲሰፋ በማድረግ ማስተካከል ይቻላል።

አብዛኞቹ የኤአይ ሥርዓቶች የሚሠለጥኑበት መንገድ የሆኑትን እነዚህን ቀላል ተግባራት በከፍተኛ መጠን በአንድ ላይ በመፈጸም የማይታመኑ ውስብስብ ውሳኔዎችን እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል።

ኤአይ እንዴት በራሱ መማር ይችላል?

ክትትል በማድረግ የሚሰጥ ትምህርት ውጤታማው ልምምድ ነው፤ ይሁን እንጂ በቅርቡ በኤአይ የተደረሱ ግኝቶች ያለ ክትትል ማለማመድ እንዲቻል አድርገዋል።

በቀላል ቋንቋ ውስብስ በሆነ ስሌት እና በከፍተኛ መረጃ አማካይነት ኤአይ የሰው ልጅ ክትትል ሳያደርግበት በራሱ ሊማር ይችላል ማለት ነው።

ለዚህ ብዙ ታዋቂ የሆነው ጥሩ ምሳሌ ቻትጂፒቲ ነው።

በኢንተርኔት ላይ ያሉ ጽሑፎች እና በዲጂታል መልኩ የተቀመጡ መጽሐፎች እጅግ በርካታ መሆናቸውን ተከትሎ በወራት ልዩነት ውስጥ ቻትጂፒቲ በራሱ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ቃላትን ማጣመርን ተምሯል።

በውጭ ቋንቋ የተጻፉ ምሥልን የያዙ በርካታ መጽሐፍት አልዎት እንበል።

በሂደት ከስዕል ወይም ከፎቶ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ የአንድ ተመሳሳይ ቃልን ትርጉም ሊረዱ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የማያውቁት ቃል ከቤት ስዕል ጋር ተደጋግሞ ሲቀርብ።

ከቤት ሥዕል ጋር ተደጋግሞ ከሚቀርበው ቃል ጋር ተቀጥያ ሆኖ የሚቀርብ ቃልም ካለ እንዲሁ ትርጉሙን ሊረዱ ይችላሉ።

ቻትጂፒቲም እንዲሁ የቃላት አገባብን እና ግንኙነትን በመረዳት የራሱን ሞዴል በመፍጠር የቃላት ትርጉመ ምን ሊሆን እንደሚችል በመረዳት አዳዲስ አረፍተ ነገሮችን መፍጠር ተለማምዷል።

ቻትጂፒቲ ይህን ማድረግ የሚቻለው አንድ ቃል ብቻውን እንዲሁም በዓረፍተ ነገሮች ውስጥ እንዴት እንደገባ ከፍተኛ መጠን ባለው መረጃ ውስጥ አጠቃቀሙን ካስተዋለ በኋላ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋሉ በተደጋጋሚ በማንበብ ነው።

ባለፉት ዓመታት ሰው በሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ላይ የታየው እድገት በዘርፉ ጉጉት እንደማሳደሩ ሁሉ አሳሳቢነቱን የሚያወሱ ድምጾች መሰማታቸውም አልቀረም። በዚህ መካከል ግን የኤአይ እድገት መቀዛቀዝን አያሳይም።

በሳይንስ ልብወለድ ውስጥ ያየናቸው አዎንታዊ እና አስፈሪ ነገሮች እውን የሆኑ ይመስላሉ። ገና ከአሁኑ ኤአይ ከሰው ልጆች ልኅቀት በላይ አቅም እንዳለው የሚያሳይ ዓለም ውስጥ ነው ያለነው።

የባለሙያ አስተያየት፡ ልክ እንደ ልጆች አድርገው ያስቧቸው

“እነዚህን ማሽኖች ውስብስብ በሆነው ዓለም ውስጥ ሥነ-ምግባር እንዲኖራቸው ማድረግ እንችላለን ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ያለው ልጆቻችንን እንዴት እንደምናሳድግ እና ለመጪው ዓለም እንዴት እናዘጋጃችዋለን በሚለው ጥያቄ ውስጥ ነው። ልጆችን ስናሳድግ ወደፊት ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል በትክክል አናውቅም። ለአንዳንድ ጥያቄዎች መልሶችን እራሳቸው ፈልገው እንዲያገኙ እንጂ ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልሶችን በቀጥታ አንስጣቸውም።”

ሞ ጋውዳት
ሞ ጋውዳት – የጉግል ኤክስ የቀድሞ አዘጋጅ እና ከፍተኛ ባለሥልጣን

አዘጋጆች

ጽሑፍ፡ በፖል ሳርጀንት

ዲዛይን በጄኒ ሎው፣ ዴቢ ሎዡ፣ ፓትሪሺያ ኦፎኖ እና ኦሊ ፖዌል

ዲቨሎፕመንት በአሲዝ ፔሬራ እና አሊ ሸትልስ

ተጨማሪ አርትኦት በኤማ አትኪንሰን እና ቤላ ሁሬል። ምሥጋና ለሜሪ አሕመድ

ምስሎች፡ ጌቲ ኢሜጅስ