ጠመንጃ የያዘ ፖሊስ

20 ሀምሌ 2023, 07:52 EAT

በኒውዚሏንዷ ኦክላንድ ከተማ አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ ምክንያት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

ከተማዋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለማሰናዳት ደፋ ቀና እያለች ባለችበት ወቅት ነው ይህ የሆነው።

አንድ የፖሊስ መኮንንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ታጣቂውም መገደሉ ተገልጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስ ሂፕኪንስ ጥቃቱ እንደ የሽብር ተግባር የሚታይ አይደለም ብለዋል።

አክለው የሴቶች የዓለም ዋንጫ በታሰበለት ጊዜ እንደሚካሄድ ገልጠዋል።

ሕዝቡ ሊያውቀው የሚገባው ነገር ጥቃቱ አድራሹ እርምጃ እንደተወሰደበትና አሁን ምንም ዓይነት አደጋ እንደሌለ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እሳቸው እንደሚሉት ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ርዕዮተ ዓለማዊ መነሾ የለውም።

የኦክላንድ ከንቲባ የሆኑት ዌይን ብራውን ሁሉም የፊፋ ሠራተኞችና እግር ኳስ ቡድኖች ደኅና መሆናቸውን ማረጋገጣቸወን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ በተፈጠረው ነገር “ማዘኑን” ገልጦ ከኒውዚላንድ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋጋረ መሆኑን አሳውቋል።

“ጥቃቱ በደረሰበት አካበቢ የሚኖሩ ብሔራዊ ቡድኖች ምናልባት ተፅዕኖ ደርሶባቸው ከሆነ ለማረጋገጥ አጠገባቸው እንገኛለን።”

ቀደም ብሎ የከተማዋ ከንቲባ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።

ታጣቂው መሐል ከተማ ገብቶ ተኩስ የከፈተው በኒውዚላንድ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት1፡22 ሲሆን ሃገሪቱ ከሰዓታት በኋላ የመክፈቻውን ጨዋታ ለማድረግ እየተሰናዳች ነበር።

ታጣቂው በግምት 24 ዓመቱ ሲሆን እዚያ የግንባታ ጣቢያ ውስጥ ይሠራ እንደነበር ፖሊስ ጠቁሟል።

ፖሊስ ከተማዋ መሐል ከሚገኝ አንድ የግንባታ ጣቢያ የተኩስ ድምፅ መስማቱን አሳውቁ ወደሥፍራው እስኪያቀና ድረስ የጥይት ድምፅ ይሰማ ነበር።

ግለሰቡ በአሳንሱር ተንጠልጥሎ ለጥቂት ጊዜ ከፖሊስ ጋር ከተታኮሰ በኋላ መገደሉን ፖሊስ አሳውቋል።

ከተኩስ ልልውጡ በኋላ በከተማዋ ዋናው የቢዝነስ ቀጣና በርካታ ቁጥር ያላቸው ፀጥታ አስከባሪዎች ታይተዋል።

ኒውዚላንድ ከኖርዌይ የሚያደርጉት የሴቶች ዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ በኤደን ፓርክ ጠዋት 4 ሰዓት ይካሄዳል።

የሁለንም ደኅንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል እንደሚመደብ የኒው ዚላንድ ስፖርት ሚኒስትር ግራንት ሮበርትሰን ተናግረዋል።

ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ ዘጠነኛውን የሴቶች የዓለም ዋንጫ በጋራ አዘጋጅተዋል።