
20 ሀምሌ 2023, 09:56 EAT
በቴሌግራም ቻናል የተለቀቀ አንድ ምስል የቫግነሩ መሪ ቤላሩስ ገብተው ከታጣቂዎቻቸው ጋር ሲወያዩ አስመልክቷል።
የቭገኒ ፕሪጎዢን ወታደሮቹን ሲቀበል፤ ቀጥሎ ደግሞ በዩክሬን ጦርነት እየሆነ ያለው “አሳፋሪ” ነው ሲል ይደመጣል።
ግለሰቡ እንደሚጠቁመው የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች በቅርቡ ጦርነቱን ሊቀላቀሉ ይችላሉ።
ከዚህ ቀደም ቤላሩስ የቫግነር ወታደሮች ለሃገሪቱ ጦር አማካሪና አሠልጣኝ ሆነው ያገለግላሉ ያለችውንም ያረጋገጠ ምስል ነው።
ባለፈው ሰኔ መገባደጃ የቫግነር ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ ወታደራዊ አመፅ ካወጁ በኋላ ፕሪጎዢን በቪድዮ ሲታይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ብዙም ብርሃን በሌለበት አካባቢ የተቀረፀው ምስል ፕሪጎዢን አንድ አስፋልት ላይ ቆሞ ያስመለክታል። በዙሪያው ዛፎች፣ መጋዘንና ጊዜያዊ መጠለያ ዳስ የሚመስሉ ነገሮች ይታያሉ።
ቢቢሲ ቬሪፋይ፤ ዛፍ፣ ዳስና ሕንፃው የካምፑ ምዕራባዊ ጫፍ እንደሆነ ማሳያ ነው ይላል።
ከጀርባው በርካታ ሰዎች ዥንጉርጉር የወታደር ልብስ ለብሰው ድምፃቸው ከፍ ብሎ ይሰማል።
ምንም እንኳ ምስሉ ጥራት ቢጎድለውም ፕሪጎዢንን መለየት ከባድ አይደለም። በዚያ ላይ ከዚህ በፊት ሲናገር በተደጋጋሚ ለሰሙት ድምፁና አነጋገሩ የሱ መሆኑን ለመለየት አይከብዳቸውም።
- የቫግነር ቡድን አባላት ቤላሩስ መግባታቸውን የሳተላይት ምሥሎች አሳዩ19 ሀምሌ 2023
- ፑቲን በ’ብሪክስ’ ጉባዔ ላይ እንደማይሳተፉ ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች19 ሀምሌ 2023
- በክሪሚያ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ፈንድቶ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ19 ሀምሌ 2023
በዚህ ቪድዮ ላይ ፕሪጎዢን ወታደሮቹ ዩክሬን ውስጥ ያደረጉት “ገድል” ለሩሲያ ትልቅ “ውለታ” መሆኑን ጠቅሶ አሁን ጦርነቱን እያቀናበረ ያለውን ሰው ግን ወቅሷል።
“አሁን ግንባር ላይ እየሆነ ያለው ነገር እጅግ አሳፋሪ ነው። እኛ በዚህ ጉዳይ መሳተፍ አንፈልግም። አቅማችንን ሙሉ በሙሉ ማሳየት እስክንችል ድረስ መቆየት አለብን” ሲል ተደምጧል።
አክሎም “እዚህ ቤላሩስ ላልተወሰነ ጊዜ እንድንቆይ ውሳኔ ተላልፏል” ብሎ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን የቤላሩስ ጦርን “ከዓለም ሁለተኛው” የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም ይናገራል።
የቫግነር አለቃ ፕሪጎዢን ወታደሮቹ “ዝግጅት ማድረግ ይቀጥላሉ” ብሎ ወደፊት ምናልባት “ወደ ግንባር ተመልሰን አቅማችንን ሳናፍርበት እንጠቀመው ይሆናል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ይሄ አስተያየቱ የሩሲያ ጦር ለቫግነር ወታደሮች ተጨማሪ መሣሪያ ሊሰጥ አልሻተም ለሚለው ዜና ምላሽ ሊሆን ይችላል።
ምስሉ ላይ ወደሆነ ግለሰብ ዞሮ “መሪያችንና ቫግነር የሚለውን ስም የሰጠን” በማለት ሲያስተዋውቀው ይታያል።
ምንም እንኳ የግለሰቡ ስም ባይጠቀስም ብዙም ፊቱ የማይታየው የቫግነር ወታደራዊ መሪና የቀድሞው የሩሲያ ወታደር የነበረው ድሚትሪ ኡትኪን ሊሆን ይችላል።
የጦርነት ስሙ ቫግነር የቅጥረኛው ቡድን መጠሪያ ሆኖ ያገለግላል።
ደቡባዊ ቤላሩስ የሚገኘው የቀድሞ የሃገሪቱ ጦር መቀመጫ የነበረው ካምፕ በርካታ መኪናዎች መግባባታቸውን ቢቢሲ ቬሪፋይ ተመልክቷል።
ሥፍራው ከሚንስክ 103 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው ነው።
የቫግነር ወታደሮች በአጭሩ ከተቀጨው አመፅ በኋላ የፈቀዱ የሩሲያን ጦር እንዲቀላቀሉ፤ ያልፈለጉ ደግሞ የሩሲያ የቅርብ አጋር ወደሆነችው ቤላሩስ እንዲያቀኑ ተነግሯቸው ነበር።
ባለፈው ሳምንት ኮሜርሳንት ከተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “ቫግነር የሚባል ቡድን ከዚህ በኋላ የለም” ብለዋል።