
20 ሀምሌ 2023, 08:55 EAT
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ወደቦች የሚያመሩ መርከቦችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፏን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የስንዴ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።
ሩሲያ እነዚህን መርከቦች እንደ ወታደራዊ ኢላማም ሊቆጠሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያም ነው ያስተላለፈችው።
በዚህ ሳምንት በጥቁር ባህር በኩል እህል ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለማጓጓዝ ከሚያስችለው ስምምነትም እንደወጣች ሩሲያ አስታውቃለች።
ሩሲያ በእቃ ጫኝ መርከቦች ላይ ለሚደርስ ጥቃት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ እያቀደች ነው ሲሉም የዋይት ሃውስ ቃለ አቀባይ ከሰዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካገኙ አገራቸው ወደ ስምምነቱ በአፋጣኝ እንደምትመለስም ተናግረዋል።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ የሩሲያን የግብርና ባንክን ከዓለም አቀፉ የክፍያ ስርዓት ጋር ማገናኘት አንዱ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን የወደብ ከተማ ማይኮላይቭ ላይ ረቡዕ ምሽት ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በኦዴሳ ወደብም ላይ እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
ሩሲያ በጠቀለለቻት ክሪሚያም በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በደረሰ ጥቃት አንዲት ታዳጊ መገደሏን የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረዋል።
በኦዴሳ ወደብ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን አስመልክቶ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ ሆን ብላ የእህል ወጪ ንግድ መሰረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዚህም ተጋላጭ አገራትን ለበለጠ አደጋ ጋርጣለችም ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በጥቁር ባህር አካባቢ ያሉ ሌሎች አገራትም የእቃ ጫኝ መርከቦች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማለፍ እንዲችሉ ጣልቃ መግባት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
- ዩክሬን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ አገራት የምትልከው እህል ምን ያህል ነው?24 ነሐሴ 2022
- በኬንያው ጸረ መንግሥት የአደባባይ ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገደሉ20 ሀምሌ 2023
- ዩክሬን እና ሩሲያ እህል ወደ ውጭ እንዲላክ ምን ለማድረግ ተስማሙ?23 ሀምሌ 2022
“ሐምሌ 12፣ በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ በጥቁር ባህር በኩል ወደ ዩክሬን ወደቦች የሚያመሩ መርከቦች የጦር መሳሪያ ጫኝ መርከቦች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ” ሲልም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አትቷል።
“እነዚህ መርከቦች ከኪየቭ አገዛዝ ጎን ቆመው በዩክሬን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑም ይቆጠራሉ” ሲል አክሏል።
ይህንም ተከትሎ በአውሮፓ የአክሲዮን የገበያ ልውውጥ የስንዴ ዋጋ ረቡዕ 8.2 በመቶም ጨምሯል።
በዚህም አንድ ቶን የስንዴ ዋጋ 219. 78 ዩሮ እንዲሁም የበቆሎ ዋጋም 5.4 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።
የአሜሪካ የስንዴ ገበያም 8.5 በመቶ ጭማሬ ረቡዕ እለት አሳይቷል።
ይህም ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የታየ ከፍተኛ ጭማሬ በሚልም ተመዝግቧል።
የዩክሬን የግብርና ሚኒስትር ማይኮላ ሶልስኪ እንዳሉት በጥቃቱ 60 ሺህ ቶን ያህል እንደወደመ እንዲሁም የእህል ወጪ ንግድ መሰረተ ልማትም መጎዳቱን ነው።
ሩሲያ ከእህል ስምምነቱ በወጣች በሰዓታት ውስጥ ነው የዩክሬንን ወደቦች ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው።