የጠፋው የአሜሪካ ወታደር

20 ሀምሌ 2023, 16:16 EAT

ያለ ፈቃድ ወደ ሰሜን ኮሪያ ግዛት የገባውን የአሜሪካ ወታደር በተመለከተ ለመደራደር አሜሪካ ያደረገችው የስልክ ጥሪ በሰሜን ኮሪያ በኩል ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን አሜሪካ ገልጻለች።

ትራቪስ ኪንግ የተባለው የአሜሪካ ወታደር ወደ ሰሜን ኮሪያ ግዛት ዘልቆ የገባው ባለፈው ማክሰኞ ነበር። ስለወታደሩ ዕጣ ፈንታም ሆነ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ከሰሜን ኮሪያ በኩል ስልክ ባለመነሳቱ ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ሰሜን ኮሪያ ብዛት ያላቸው ሚሳኤሎችን እየሞከረች ባለችበት ወቅት እና የሁለቱ አገራት ግንኙነት ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ በሻከረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

ከዓለም የተገለለችው ሰሜን ኮሪያ “ቀጣይነት ባለው የዜጎች እስራት” እና “እስረኞችን በከፋ ሁኔታ በማስተናገድ” ስሟ ይነሳል። የኪንግ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በዝቅተኛ ማዕረግ ደረጃ ያለ የወታደር አባል ለሰሜን ኮሪያ የሚኖረው የፕሮፖጋንዳ ሚዛን ዝቅተኛ ስለሚሆን ምናልባት በቅርቡ ልትለቀው ትችላለች የሚል ግምት ቢኖራቸውም የወታደሩ እጣ ፈንታ ግን ከዚህም የተለየ ሊሆን ይችላል።

በሁለቱ አገራት መከካከል የተጀመረ ንግግር ባለመኖሩ ሁኔታው ወደየት ሊያመራ እንደሚችል መገመት ከባድ ነው። ከአሜሪካ በኩል የተደረገውን የግንኙነት ሙከራ ሰሜን ኮሪያ ለመቀበል አለመሞከሯ ደግሞ ሌላ ጥርጣሬ የሚያጭር ጉዳይ ሆኗል።

ወታደሩ ከነበረበት ደቡብ ኮሪያ በስነ ምግባር ምክንያት ወደ አሜሪካ ሊመለስ በዝግጅት ላይ እያለ ነው ይህ ሁኔታ የገጠመው።

የ23 ዓመቱ ወታደር ወደ አሜሪካ ሊመለስ የበረራው ጊዜ በቀረበበት ወቅት ባልታወቀ ሁኔታ ቀድሞ ወዳዘጋጀው የድንበር አካባቢ ጉብኝት ተጓዘ።

ይህን ያደረገበት ምክንያት ባይታወቅም የአሜሪካ የጦር ባለስልጣናት ግን ወታደሩ በፈቃዱ ድንበሩን እንደተሻገረ ተናግረዋል።

ወታደሩ ያቋረጠበት ድንበር በ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት የተከፈለ ሲሆን በሽዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች በደቡቡ የኮሪያ ክፍል ይገኛሉ።

ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ተንታኞች ሰሜን ኮሪያ የወታደሩን መያዝ ለፕሮፓጋንዳ ልትጠቀምበት ትችላለች ይላሉ። ምናልባትም በአገሪቱ ሚዲያ በቅርቡ አቅርበው ዓላማቸውን ሊያስፈጸሙበት እንደሚችሉ ጄምስ ፍሬትዌል የተባለ ተንታኝ ግምቱን አስቀምጧል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ወታደር በማዕረግ ደረጃው ዝቅተኛ ከሚባሉት መካከል በመሆኑ ያን ያክል የፕሮፖጋንዳ ግብ አይመታላቸውም የሚሉ ተንታኞች አሉ።

ዲፕሎማቶች እና ወታደራዊ መኮንኖችም ጉዳዩን እልባት ለመስጠት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር እየሞከሩ ነው።

ነገር ግን ሰሜን ኮሪያን ማነጋገር ቀላል አይደለም። ከሰሜን ኮሪያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሌላት አሜሪካ በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር ሌሎች የመገናኛ አማራጮች እንዳሏት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰዎች በስዊድን እና በደቡብ ኮሪያ በኩል ለመገናኘት ቢጥሩም እስካሁን ግን ምንም የተገኘ መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስሌላቸው ሰሜን ኮሪያ የሚገኘው የስዊድን ኢምባሲ አሜሪካን ወክሎ ሰሜን ኮሪያ ጋር ሊደራደር ይችላል የሚል መላምት አለ። ቢሆንም ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ድንበሩ ዝግ በመሆኑ የኢምባሲ ሰራተኞች በዚያ አይገኙም።

ድንበሩ አካባቢ ያለውን ቦታ የሚቆጣጠሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ መኮንኖች ከሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ አዛዦች ጋር በየቀኑ ይደዋወላሉ።

ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ አዛዦች ስልክ አያነሱም።

በቅርብ ጊዜ በሕገ ወጥ መልኩ ወደ ሰሜን ኮሪያ የገቡ የአሜሪካ ዜጎች ወንጀል ፈጽመው ጥፋተኛ ካልተባሉት በስተቀር በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ተለቀዋል።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት አሁን በአሜሪካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል ካለው ፍጥጫ አንጻር ይህንን ወታደር አግቶ መያዙ ለሰሜን ኮሪያ ያን ያክል ጥቅም የሚያስገኝ አይደለም።

ምናልባት በሕገ ወጥ መልኩ ድንበር በመጣሱ የተወሰነ ካሳ ጠይቃ ወታደሩን ልትለቀው ትችላለች ይላሉ።

ሊሆን የሚችለው ምናልባት የተወሰነ ፕሮፖጋንዳ ከተሰራበት በኋላ ወታደሩ በሰላም ወደ አሜሪካ ሊመለስ ይችላል።

በወረርሽኙ ምክንያት አቋርጠውት የነበረውን ግንኙነት ለመጀመርም ምናልባት ይህ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ተንታኞቹ ገልጸዋል።