እጇን የተያዘች ታዳጊ ጥላ

20 ሀምሌ 2023

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለች በ13 ዓመቷ የተጠለፈችው ደጊቱ ዳቃሟ፤ በጠለፋት ግለሰብ ጥቃት እየደረሰባት ለሁለት ወር ያህል ጫካ ውስጥ አሳልፋለች።

የወሲብ ጥቃት ጨምሮ ከደረሰባት የአካል ጉዳት በተጨማሪ የሥነ ልቦና ጉዳቱም ቀላል አልነበረም።

በደሉን የፈጸማበት ግለሰብ ሽማግሌዎችን ወደ ቤተሰቦቿ በመላክ እርቅ ይፈጽማል፤ በኋላም ወደ ቤቱ ይዟት ይገባል።

ጉዳት ካደረሰባት ግለሰብ ጋር ትዳር እንድትመሠረት የተገደደችው ደጊቱ፣ በኋላ ላይ አምልጣ ሕይወቷን መቀየር ችላለች።

ደጊቱ ላይ የደረሰው ነገር የመጀመሪያው አይደለም። ይህ የብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ታሪክ ነው።

ጠለፋ የሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግ ጭምር ወንጀል ነው።

በዚህ ሁኔታ የተጠለፉ ሴቶች ፍትሕ ከማግኘት እርቅ ማውረድ በሚል በባህላዊ መንገድ መፍትሄ በመስጠት ወደ ሕግ እንዳይቀርቡ ይደረጋል።

ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም።

በአንዳንድ ባህላዊ ድርጊቶች ምክንያት ግን ወንጀል የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ከፍትሕ እያመለጡ መሆኑን የሚናገሩ አሉ።

ሽማግሌዎች እርቅ አውርደዋል በሚል ወንጀል ፈጻሚዎች ወደ ሕግ እንዳይቀርቡ ይደርጋሉ። በብዛት ይህ የሚደረገው አጥፊው ላይ የገንዘብ ቅጣት በመጣል ነው።

በሽምግሌዎች የሚሰጠው መፍትሔ ለተፈጸመው ወንጀል ፍትሕ ይሆናል? የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትስ ይህንን የሽማግሌዎች ውሳኔ ይቀበላል?

በጠለፋ ላይ የባህል ሕግ እና አካሄድ

የአገር ሽማግሌዎች በሚፈጠሩ ጭቶች ላይ ሠላም እንዲሰፍን ኃላፊነት አለባቸው። አለመግባባት እና ግጭቶችን በእርቅ በመፍታትም የማኅበረሰብን ትስስር ይጠብቃሉ።

ሆኖም ግን በጠለፋ ጉዳይ ላይ የሚወሰደው እርምጃ የተጎጂዎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ ይመስላል።

በቅርቡ በምዕራብ አርሲ ዞን በኮፈሌ ወረዳ አባገዳዎች ጠለፋን ጨምሮ ሌሎች ልምዶች ላይ የተለያዩ ሕጎችን አውጥተዋል።

አባ ገዳ ገብረአምላክ ጉዬ እንደሚሉት እነዚህን ሕጎች ሴቶች ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶችን ለማስወገድ የተቀመጡ ናቸው።

ሆኖም እነዚህ ሕጎች በሙሉ ግን የሴቶቹን መብቶች ከግምት ያስገቡ አይመስሉም።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ተጠርጣሪ ከፈጸመው ጥፋት ጋር ተስተካካይ ቅጣት ከማግኘት ይልቅ፣ የማምለጫ ዕድል የሚፈጥረለት ይመስላል በሚል የሚተቹ አሉ።

ከእነዚህ ባህላዊ ሕጎች ውስጥ አንዱ “ጠለፋን የፈጸመ ሰው የሰባት ከብት ቅጣት ይጣልበታል” የሚል እንደሆነ አቶ ገብረአምላክ ይገለጻሉ። የመድፈር ወንጀል የፈጸመ ሰውም በተመሳሳይ ሰባት ከብት እንደሚቀጣ ገልጸዋል።

አባ ገዳው እንደሚሉት በሴቷም ሆነ በወንዱም በኩል ምርመራ ተደርጎ “የሁለቱ ፈቃድ ከሆነ እንዲጋቡ ይደረጋል።”

የሚላኩት ሽማግሌዎች ልጅቷን የጠለፈው ግለሰብ “ቤት ያለው ወይም ቤት ባይኖረውም ለማስተዳደር የሚጣጣር ከሆነና ወደፊት ተስፋ ያለው ሰው ከሆነ እንድታገባው ይደረጋል” ይላሉ።

የተጠለፈችው ሴት ጉዳት ካደረሰባት ሰው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ካልሆነች “የሚያስገድዳት የለም” የሚሉት አባ ገዳው፣ ነገር ግን ልጅቷን በማስገደድ ወደ ትዳር እንድትገባ የሚያስገድዱ ልምዶች እንዳሉ ያምናሉ።

ሽማግሌዎችም ሆኑ ቤተሰቦች ለእርቅ በሚላከው ገንዘብ በመታለል ልጅቷን ወደ ትዳር ማስገባት የተለመደ ቢሆንም ባህሉ ግን ይህንን እንደማይደግፍ ይናገራሉ።

አባገዳ ገብረአምላክ “እነዚህ ሴቶች የጠለፋቸውን ግለሰብ እንዲያገቡ ማስገደድ ትክክል አይደለም” ቢሉም “ልጅቷ ከተስማማች እና ልጁ ተስፋ ያለውና ማደግ የሚችል ከሆነ ትዳር እንዲፈጸም ሽማግሌዎች ልጅቷን የሚያሳምኑበት ሁኔታዎች አሉ።”

“በልጅቷ ፍላጎት” የሚለው ጉዳይ ግን ሙሉ ለሙሉ አሳማኝ አይደለም። ሴቶቹ ወደ ትዳር የሚገፉት በማስገደድ ብቻ ሳይሆን በማታለል፣ በማባበል እና የተለያየ ጫና በመፍጠር ጭምር ነው።

ሴቶቹን ወደ ትዳር መግፋት ከሚፈጥረው ሰቆቃ በተጨማሪ እነዚህን ጥፋት ፈጻሚዎች ወደ ሕግ አለማቅረቡ ሌላው ችግር ነው።

“ሁለት ቦታ መቀጣት አይችልም” የሚል አስተያየት አለ። አንድ ጉዳት አድራሽ በባህላዊ መንገድ ከተቀጣ ወደ ሕግ አለማቅረብ በሕግ ከተቀጣ ደግሞ በባህል አለመቀጣት አለ።

አባ ገዳ ገብረ አምላክ በሕግ የበላይነት የሚያምኑ ቢሆንም፣ እንደ ባሕል ሕግ “ሽማግሌ የአንድ ሰውን ጉዳይ አይቶ ከቀጣ. . . ወደ ሌላ አካል አሳልፎ አይሰጥም” ይላሉ።

ለተፈጸመው ጥፋት ከመቅጣት በፊት የቤተሰቡን ሃሳብ አይቶ ግለሰቡን ለፍትሕ እንዲያቀርቡ ማበረታታት ይችላል የሚሉት አባ ገዳው፤ ነገር ግን “ራሱን የቀጣን ሰው መንግሥት መቅጣት አለበት ብሎ አሳልፎ አይሰጥም።”

ሽማግሌን በመላክና በባህላዊ እርቅ የጠለፋ ጉዳይን መፍታት በገዳ ብቻ የሚታይ ሳይሆን ጠለፋ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚታይ ነው።

ደግቱ በምትኖርበት በሲዳማ ክልል የተፈጠረውም ነገር ይህንን ያሳያል።

ሽማግሌዎች ተልከው ቤተሶቿን በማሳመን ደጊቱ ጠላፊዋን እንድታገባ ተወሰነ።

በዚህ የባሕል ሕግ እና አስተያየት ላይ ሕጉ ምን ይላል?

በእጇ የሚደርስባትን ጥቃት የምትከላከል ሴት

የኢትዮጵያ ሕገ ስለጠለፋ ምን ይላል?

በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ጠለፋ ወንጀል እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል። አንዲት የተጠለፈችን ሴት በማታለል፣ በማስፈራራት፣ በማስገደድም ሆነ በሌላ መንገድ የጠለፋትን ሰው እንድታገባ ማድረግ ወንጀል እንደሆነ ሕጉ አስቀምጧል።

የወንጀል ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብት የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ለሜሳ ጉደታ እንደሚሉት “በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 587 መሠረት ጠለፋ ሙሉ ለሙሉ ወንጀል ሲሆን ከ3 እስከ 10 ዓመት እስርም የሚያስቀጣ ነው̃።”

ከጠለፋ ጋር ተያይዞ መድፈር የተፈጸመ ከሆነ ደግሞ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 629 ስር ያሉት ሕጎች ተግባራዊ ይሆናሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ “የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚቃረኑ ሕጎች መውጣት አይችሉም. . . ከወጡም ተቀባይነት የላቸውም” ይላሉ ባለሙያው።

ኢትዮጵያ ለባሕላዊ ሕጎች እና አስተምሮዎች ሕገ መንግሥቱን እስካልተቃረኑ ድረስ ዕውቅና ትሰጣለች። በተጨማሪም አንድ ሰው ባሕላዊ ሕጎችን እና አስተምሮዎችን የመቀበል እና የመተውም መብት አለው ይላሉ።

የጠለፋ ጉዳይን አስመልክቶ የተቀመጡት የባሕል ሕጎች በማኅበረሰቡ መካከል እርቅ እንዲወርድ ለማድረግ ትልቅ ጥቅም እንደሚኖራቸው የሚገልጹት አቶ ለሜሳ፣ ነገር ግን ይህን የጠለፋ ወይንም የመድፈር ወንጀል የፈጸመን ሰው “ይህንን ያህል ከብት ክፈል ተብሎ የተወሰነበትን ቅጣት ብቻ በመክፈል ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ሊሆን አይችልም” ይላሉ።

“ይህም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23/1 ላይ ተገልጿል።”

ስለዚህ ባሕላዊ ሕጎች ተጎድተው የማኅበረሰባዊ ግንኙነታቸው የተቋረጠ፣ ሞራላቸው የተጎዳ ሰዎችን “ለመመለስ፣ እርቅ በማውረድ ሠላም እና መረጋጋትን በማምጣት በፍቅር እንዲኖሩ ከማድረግ ውጭ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ የሚያድርግ አይደለም” ሲሉ የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የነጻ ሕግ አገልግሎት አስተባባሪ ወ/ሮ ሃና ኃይለመለኮት በበኩላቸው እንደዚህ አይነት ወንጀል “በግለሰብ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሳይሆን ማኅበረሰብ ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ነው የሚታየው” ይላሉ።

“ይህ ወንጀል ሴቷ ላይ ቢፈጸምም ጉዳት የደረሰባት ግን እሷ ብቻ ሳትሆን ማኅበረሰቡም ላይ ነው ተብሎ ነው የሚታሰበው።”

በዚህ ምክንያት ተመሳሳይ ወንጀሎችን የሚመረምረው የሕግ አካል ሳይሆን ፖሊስ፤ ወንጀለኛውን የሚከሰው ደግሞ ጠበቃ ሳይሆን ዐቃቤ ሕግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንን ወንጀል የፈጸመ ሰው እርቅ አውርዶ ከልጅቷ ጋር ትዳር ቢመሰርትም “በወንጀሉ ከመጠየቅ ሊያመልጥ አይችልም” ይላሉ።

ወ/ሮ ሃና ጨምረው ይህን ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ ላይ ክስ የሚመሠርተው በተበዳይ ሳይሆን በዐቃቤ ሕግ መሆኑን ተናግረዋል።

“ተበዳይ ይህንን ሰው አልከስም ስላለችም የሚቋረጥ ነገር አይደለም።”

በዚህ ወንጀል ፈጻሚው ላይ አልመሰክርም ብትል እንኳን ፍርድ ቤት እሷን የማስገደድ መብት እንዳለው ባለሙያዋ ተናግረዋል።

“በተለያዩ ቦታዎች ይህ ተለምዷል። ይጠልፋታል፣ ይደፍራታል ከዚያ በኋላ ግን ከወንጀሉ ለማምለጥ ወደ ቤተሰቧ ሽማግሌ በመላክ እንድታገባው ያደርጋል” ይላሉ።

“ይህንን የሚያደርገው ከወንጀሉ ከለላ ለማግኘት ነው። ሕጉ ደግሞ ያንን ከለላ ነው ያነሳበት።”

“የአገራችን ሕግ ብታገባትም ከቤተሰቧም ጋር እርቅ ብታወርድ ከወንጀል ተጠያቂነት አታመልጥም እያለ ነው” ሲሉ የሕጉን አካሄድ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ይህን የጠለፋ ወንጀል የፈጸመ ሰው በባሕል ከተቀጣ በኋላ በሕግ አይቀጣም የሚለውን ባሕላዊ መሪዎች ያላቸውን አቋም ስህተት እንደሆነ አቶ ለሜሳ ይናገራሉ።

“በዚህ ጉዳይ ላይ በባሕል መቅጣት እና ማስታረቅ ወንጀሉን ለመቀነስ ጥሩ ቢሆንም በባሕላዊ መንገድ ስለተቀጣ በመደበኛው ሕግ ፍርድ ቤት በመቅረብ በአገሪቱ በወጡ ሕጎች ደግሞ አይጠየቅም ተብሎ አቋም መያዙ መሉ ለሙሉ ስህተት ነው” ይላሉ።

ወ/ሮ ሃናም እንደዚህ ዓይነት ክፍተት የሚታየው በፖሊሶች እና በፀጥታ አካላት ዘንድ ሕጉ ምን ይላል በሚለው ላይ የግንዛቤ ችግር በመኖሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

“ሕጉ በዚህ ወንጀል ጉዳይ በዝርዝር ተቀምጧል። በጉዳዩ ላይ ግን ግንዛቤ መፈጠር አለበት” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9/1 እንደሚገልጸው “ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው “የትኛውም ሕግ፤ የትኛውም ባሕላዊ አስተምህሮ፤ የትኛውም ሥልጣን ያለው አካል ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተቀባይነት የሌለው እና ሥራ ላይ ሊውል የማይችል ነው” ብለዋል።

ሴቶች የጠለፋቸውን እንዲያገቡ ለምን ይገደዳሉ?

የእኛ ማኅበረሰብ ለተጠለፈች ወይንም ለተደፈረች ሴት ያለው አስተያየት ተጎጂዋን የሚጠቅም ወይንም ቀና ብላ እንድትሄድ የሚያድርግ ሳይሆን እንድታፍር የሚያድርግ እና የሚያገላት ነው።

ከጎጂ በላይ የተጎዳችው ላይ ነው ጫናው የሚያርፈው።

በዚህ ምክንያት ‘የደፈራት ሰው ካገባት እንጂ ሌላ ወንድ አያገባትም’ በሚል አስተያየት ይህቺ ሴት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያደረሰባትን ግለሰብ እንድታገባ ትገደዳለች።

ባሕላዊ ሽማግሌዎችም ልጅቷን “ከእፍረት ለማዳን” የሚል እና ሌሎች ምክንያቶችን በማቅረብ የጠለፋትን ሰው እንድታገባ ሃሳብ ያቀርባሉ።

የጠለፋ ወንጀል የተፈጸመባቸው ሴቶችም ጉዳት የፈጸመባቸውን ሰው ለማግባት ይስማማሉ የሚለው ጉዳይ በሰፊው ጥናት እንደሚፈልግ ወ/ሮ ሃና ይናገራሉ።

ሆኖም በሥራቸው አጋጣሚ ከተመለከቱት ተነስተው አብዛኛዎቹ ሴቶች ይህንን ውሳኔ የሚቀበሉት በማኅበረሰቡ ግፊት ነው።

ጠለፋን ጨምሮ በሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች ላይም “ጉዳት ካደረሰው በላይ መገለሉ የሚበዛው ጉዳት የደረሰባቸው ላይ ነው” ብለዋል።

“ከጠለፋት ሰው ወጥታ ወደ ማኅበረሰቡ ስትመለስ የማኅበረሰቡ አቀባበል እንዴት ነው? በኋላስ ትዳር የመመሥረቷ ዕድል ምን ያህል ነው? ትዳር በቃኝ አልፈልግም ብትልስ ማኅበረሰቡ እንዴት ይመለከታታል?

“እነዚህን ስናይ ማኅበረሰቡ ተጎጂዎችን መልሶ የመጉዳት ባህሪ አለው። እዚህ ላይ ደግሞ መሥራት አለብን” ይላሉ።

ስለዚህ ሴቶች መገለል እና በተጨማሪ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመሸሽ በሚል የማይፈልጉት ውሳኔ ለመወሰን ይገደዳሉ ይላሉ።

የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት የቤተሰባቸው ስም እና ክብር ለመጠበቅ እንዲሁም ወደፊት ዕድላቸው ስለሚያሰጋቸው የጠለፋቸውን (እና ደፈራቸውን) ለማግባት ይገደዳሉ።

ጠላፊዋን እንድታገባ በአገር ሽማግሌዎች የቀረበውን እርቅ የደጊቱ ቤተሰቦች ተቀብለዋል። በውሳኔው ያልተደሰተችው ደጊቱ ግን ከጠላፊዋ አምልጣ የራሷን መንገድ ተከትላለች።

ይህ ደግሞ ብዙ መዘዝ አስከትሏል። ደጊቱን ከቀዬዋ እንድትሰደድ፣ የወላጆቿ ትዳር እንዲፈርስ እና እናቷ በደረሰባቸው ጫና የአእምሮ ታማሚ ለመሆን በቅተዋል።

ደጊቱ ሦስተኛ እህቷን ከጠለፋ ብታስመልጥም ሁለተኛ እህቷ ተጠልፋ ለማግባት ተገዳለች።