
20 ሀምሌ 2023, 07:15 EAT
ኢንስትራክተር ሠላም ዘርዓይ የላይቤርያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ፊርማዋን ማኖሯን ለቢቢሲ ገለፀች።
የቀድሞ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ ኢንስትራክተር ሠላም የላይቤሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ለሦስት ዓመት ለመምራት ፊርማዋን ማኖሯን ተናግራለች።
የቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች ቡድን እና የወንዶች ተስፋ ቡድን አሰልጣኝ የነበረችው ሠላም፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንንም በማሰልጠን ከፍተኛ ስም እና ዝናን አትርፋለች።
ኢንስትራክተር ሠላም ይህንን እድል እንዴት እንዳገኘች ስትናገር የላይቤርያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ቡድኑን ማሰልጠን ትፈልግ እንደሆን የሚጠይቅ በግል መልዕክት እንደደረሳት ታስታውሳለች።
“መጀመርያ አላመንኩም ነበር፤ ትኩረትም አልሰጠሁትም ነበር” የምትለው ኢንስትራክተር ሠላም ዘርዓይ፣ ፍላጎቷን ከገለፀች በኋላ ረዥም ቃለመጠይቅ ተደርጎላት ተመረጠች።
የላይቤርያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ከአምስት አገራት የተመረጡ ሌሎች አሰልጣኞች ጋር ተወዳድራለች። ባገኘችው እድል የተሰማትን ደስታ ለቢቢሲ አጋርታለች።
ከላይቤርያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ንግግር ከጀመረች አራት ወር ያህል እንደሆናት የተናገረችው ሠላም፣ ይህ እድል ለእርሷ መሰጠቱ የፈጠረባትን ስሜት ተጠይቃ “ሕልሜን ገድቤ አላውቅም። ግን የዛን ጊዜ ሕልሜ እየተቃረበ መሆኑ ነው የተሰማኝ። የእውነት በጣም ነው ደስ ያለኝ። በዛው ልክ ደግሞ ኃላፊነቱም ተሰምቶኛል” ብላለች።
አክላም “. . .ሴት ሆኖ ይህንን እድል ማግኘት በራሱ ትልቅ መነሳሳት ነው የሚፈጠረው ብዬ አስባለሁ። ሌላው ደግሞ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰልጣኞች በብዙ ነገር ይታማሉ። በችሎታም ጭምር። እርሱን ሃሳብ የሚያስቀይር ነው ብዬ ነው የማስበው። ከኃላፊነት አንጻር ደግሞ እዚያ ሄጄ እንዲሳካልኝ የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ። ምክንያቱም ከዚህ ደግሞ ሌሎች አሰልጣኞች እኔ ያገኘሁትን እድል አግኝተው በዛው መንገድ እንዲሄዱ የመጀመርያ እንደመሆኔ መጠን ኃላፊነት ይሰማኛል ማለት ነው።” ብላለች
ኢንስትራክተር ሠላም ከላይቤርያ ቡድን ጋር ከተፈራረመች ሦስት ሳምንት የሆናት ሲሆን በቀጣይ ቀናትም ወደ ላይቤርያ በማቅናት ስራዋን ትጀምራለች።
ኢንስትራክተር ሠላም ኢትዮጵያውያን ወንዶች ከዚህ ቀደም የሌላ አገር ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን ልምድ እንዳላቸው አስታውሳ፣ በሴቶች “እንግዲህ የመጀመርያዋ እኔ ነኝ ማለት ነው በአጋጣሚ” ትላለች።
- ስለሴቶች የዓለም ዋንጫ ምን ያህል ያውቃሉ? ራስዎን በእነዚህ 10 ጥያቄዎች ይፈትኑ14 ሀምሌ 2023
- ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በምን ምክንያት መንገድ ስታ የ380 ሺህ ብር ሽልማት አመለጣት?8 ሀምሌ 2023
- “ሊዲያ የሚለው ስም ራሱ ይዳኛል”፡ ‘ፊሽካ የሰቀለችው’ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ29 ሰኔ 2023
ላይቤርያ ከኢንስትራክተር ሠላም ምን ትጠብቃለች?
እንደ አሰልጣኝ ሠላም ከሆነ የላይቤርያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላለፉት ሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት ውድድር ላይ ተሳትፎ እንደማያውቅ ተረድታለች።
ነገር ግን የራሳቸው ሊግ እንዳላቸው እና በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተፎካካሪ የሆነ ቡድን እንድታዘጋጅ እንደሚጠበቅባት ትናገራለች።
ብሔራዊ ቡድኑን በማሰልጠን ሂደት ሊገጥሟት የሚችሉትን ፈተናዎች ስትናገር “ከሜዳ ውጪ የሚገጥመኝ ነገር አዲስ አገር፣ አዲስ አስተሳሰብ እና አዲስ የሆነ የእግር ኳስ ሕይወት ነው የምጀምርው። ይህ ቀላል ተግዳሮት ይሆናል ብዬ አላስብም ለሱም እየተዘጋጀሁ ነው” ብላለች።
ኢንስትራክተር ሠላም ከላይቤርያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ሁለት አመት የጸና ሆኖ፣ አንድ ዓመት ግን እንደምታሳየው ብቃት የሚጨመር አልያም የሚቀነስ እንደሚሆን ተናግራለች።
በእነዚህ ዓመታት ቡድኑን ፌዴሬሽኑ እንደሚያስበው ተፎካካሪ ማድረግ፣ “ከዚያም አልፎ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ሆኖ ባየው ደስ ይለኛል” ትላለች።
አሰልጣኝ ሰላም አጭር ኳስ እየተቀባበለ ወደ ግብ የሚደርስ ቡድን እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እያጠቃ ጎል ላይ የሚደርስ ቡድንም የሚያስደስታት ናት።
“ብዙ ጊዜ ቡድን የምገነባው በዚህ መካከል ነው፤ አሁንም ይህንኑ ነው ይዤ የምቀጥለው” ስትል የላይቤርያ ቆይታዋ ምን ሊመስል እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግራለች።
የላይቤርያ ቡድንን እያሰለጠንሽ ባለበት ወቅት ቀድሞ ታሰለጥኛቸው የነበሩት ሉሲዎችን የመግጠም እድል ቢፈጠር ምን ዓይነት ስሜት ይሰማሻል ብሎም ቢቢሲ ጠይቋታል።
“ባይሆን ደስ ይለኛል የእውነት ለመናገር። ቢሆንም ደግሞ ስራዬን እንዳከብር አንተም እንደምትጠብቅ ተስፋ አደርጋለሁ። የምችለውን ሁሉ አድርጌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለማሸነፍ ነው የምሞክረው። ነገር ግን ባይሆን እመርጣለሁ።”
ቢቢሲ ለኢንስትራክተር ሠላም ስለሚከፈላት ክፍያ መጠን ጠይቆ “ውላቸው ላይ ስለሚከፈለኝ ክፍያ እንዳልገልጽ የሚያሳስብ አንቀጽ አለው። ግን በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ አንጻር ጥሩ እና እኔን የሚመጥን ክፍያ ነው ብዬ አስባለሁ፤” በማለት በደፈናው ማለፍ መርጣለች።

ከተጫዋችነት እስከ ኢንስትራክተርነት
በአዲስ አበባ በተለምዶው 24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ሠላም ዘርዓይ እግር ኳስን ከወንዶች ጋር በመጫወት ነው የጀመረችው።
በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ በተጫዋችነት ያሳለፈችው ሠላም፣ በ2001 ዓ.ም ነው የአሰልጣኝነት ስልጠናን በመውሰድ ወደ ስልጠናው ዓለም የገባችው።
አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ለመጀመርያ ጊዜ ስላሰለጠነችው ቡድን ስትጠየቅ የወንዶች ቡድን ነበር ትላለች።
ኤስዋይጂ የተባለው ይህ የወንዶች ቡድን በወቅቱ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ የሚወዳደር ቡድን ነበር።
የነበሩት ሁለቱም አሰልጣኞች ጥለውት በመሄዳቸው አቶ ሳሙኤል ተገኝ የተባሉ የቡድኑ ኃላፊ የአሰልጣኝነት መንበሩን እነድትረከብ ጥያቄ አቀረቡላት።
እርሷ ግን የእድሜዋን ልጅነት እና የልምዷን ማነስ አይታ አሻፈረኝ አለች።
አቶ ሳሙዔል በብርቱ በመወትወታቸው እና ችሎታው እነዳላት ደጋግመው ስለነገሯት ኃላፊነቱን ተቀብላ ወደስራ ገባች።
ከዚያ በመቀጠል በ2004 ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን አሰልጣኝ የመሆን ዕድል አገኘች።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ሆና እያሰለጠነች ከቆየች በኋላም ጊዮርጊስ በ2005 የሴቶች ቡድን ሲያቋቁም በቀጥታ ዋና አሰልጣኝ ሆና ተመርጣ ማሰልጠን ጀመረች።
በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ በርካታ ወጣቶችን ለዋናው ቡድን እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችያለሁ የምትለው ሠላም ቀጣይ መዳረሻዋ የኢትዮፕያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ሆነ።
በ2010 ዓ.ም ላይ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡደንን ካሰለጠነች በኋላ የኢትዮፕያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣን አድርጎ ሾሟታል።
ኢንስትራክተር ሠላም በወቅቱ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ይዛ በሴካፋ ዋንጫ አዳዲስ ተጫዋቾችን በመያዝ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ ረትታ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በካሜሩን በደርሶ መልስ ከተሸነፈች በኋላ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተለያይታለች፡፡

የእኔ ስኬታማ ጊዜ የምትለው የቱን ነው?
የጊዮርጊስ ቡድንን በወጣትነት እድሜዋ ለማሰልጠን መመረጧን እንደ ትልቅ ስኬት አንደምትቆጥረው ትናገራለች።
በጊዮርጊስ ቆይታዋም የተለያዩ ልጆችን ለብሔራዊ ቡድን በማስመረጥ የተሻለ ሪከርድ እንዳላት ትናገራለች።
በካፍ ውስጥ የሚገኝ የሴት ኢንስትራክተሮች ፓናል ውስጥም አባል መሆኗን ትናገራለች።
“በአጠቃላይ የእግር ኳስ ሕይወቴ አሁን ካለኝ እድሜ አንጻር ፈጣን እና በስኬት የተሞላ ነው ብዬ ነው የማስበው።”