
20 ሀምሌ 2023, 10:18 EAT
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ከዛሬ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ክልላዊ የሰዓት እላፊ መጣሉን አስታወቀ።
በክልሉ በአዲስ መልክ ተቀስቅሶ የሰዎች ህይወት መጥፋቱ መዘገቡንም ተከትሎ ነው በምሽት ሰዓታት የመንቀሳቀስ ገደብ የተጣለው።
በሰዓት እላፊው መሰረት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓትንም መንቀሳቀስም ተከልክሏል።
በስራ ላይ ከተሰማሩ የጸጥታ ኃይሎች በስተቀርም ተሽከርካሪዎች እና ግለሰቦችም በተጠቀሱት ሰዓት ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መልዕክት ተላልፏል።
ከምሸት የሰዎችና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ገደብም ተላልፏል።
ከጸጥታ አካላት ውጪ ግለሰቦች የትኛውንም ጦር መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉም መደንገጉ ተጠቅሷል።
በክልሉ ከሰሞኑ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በመገምገም የካቢኔ አባላቱ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውንም የክልሉ ኮሚዩኑኬሽን በማህበራዊ ትስር ገጹ አስታውቋል።
የክልሉ መንግሥት በተነሳው ግጭት የሞቱም ሆነ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር ባይገልጽም “በሰላም መደፍረሱ እጃቸው ያለበት አመራርም ሆነ ሌላ አካላት” ተጣርቶም ተጠያቂም እንደሚደረጉ ነው በመግለጫው ቃል የገባው።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ግጭት መጀመሩን እንዲሁም የብሄር መልክ የያዙ ግጭቶች በሁለት አካባቢዎች መታየታቸውን ዘግበዋል።
- ከሰሞኑ የጋምቤላ ጥቃት ጀርባ ያለው ቡድን ማን ነው?18 ሰኔ 2022
- በጋምቤላ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ15 ሰኔ 2022
- በርካቶችን ያስደነገጠው የጋምቤላው ቪዲዮ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ17 ሰኔ 2022
በክልሉ ርዕሰ መዲና ጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ምንጮች ትናንት ሐምሌ 12/ 2015 ዓ.ም የንግድ ተቋማትና ቢሮዎች ተዘግተው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በግንቦት ወር በጋምቤላ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መሞታቸውና ከ10 በላይ መቁሰላቸውንም በተመለከተ ዘገባዎች ወጥተዋል።
ባለፈው ዓመትም የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት በመክፈት ከተማዋ ለቀናት ከተለመደ እንቅስቃሴዋ ውጪ ሆና እንደቆየችና ከ40 በላይ ሰዎችም መገደላቸው ይታወሳል።
ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግዷል።
ክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግጭቶች ያጋጠሙት ሲሆን፣ በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎችም ጥቃት ይፈጽሙበታል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ክልሉ ከ480 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መኖርያ ነው።