
ከ 4 ሰአት በፊት
የጀርመን ፖሊስ መኮንኖች ከበርሊን አፋፍ ጠፍታለች ያሏትን ሴት አንበሳ ፍለጋ ላይ ናቸው።
የፖሊስ አፈ ቀላጤ እንደገለጡት ነዋሪዎች ረቡዕ ዕኩለ ለሊት ገደማ ስልክ ሲደውሉ አልፎም በቪድዮ የተደገፈ መረጃ ሲልኩ ነበር
ከዚህ በኋላ ነው በአካባቢው ታይታለች የተባለችውን ሴት አንበሳ ፍለጋ ፖሊስ የወጣው።
በትንሹ 30 የፖሊስ መኪናዎች የተመደቡ ሲሆን የእንስሳት ሕክምና ሙያተኞችም የዱር ድመቷንፍ ፍለጋ እገዛ እንዲያደርጉ ተጠርተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በራቸውን ጥርቅም አድርገው ዘግተው እንዲቀመጡ ተመክረዋል።
የጀርመኑ ቢልድ እንደፃፈው ሀሙስ ምሽት ፖሊስ አንበሳዋን “እንዳየና” ፍለጋው እንደተጧጧፈ ለአካባቢው ነዋሪዎች አሳውቋል።
በወቅቱ አንድ ፖሊስ መንገድ ዳር ሶምሶማ ይሠሩ የነበሩ ሰዎችን “ከዚህ አካባቢ በፍጥነት ውልቅ ብላችሁ ጥፉ” ሲል እንደገሰፃቸው ጋዜጣው ዘግቧል።
ነገር ግን ታይታለች የተባለችው አንበሳ የውሃ ሽታ ሆናለች። በምሽት መነፅርና በሙቀት መለኪያ የታገዘው የጀርመን ፖሊስ ፍለጋም ቀጥሏል።
- የቫግነር መሪ የቭገኒ ፕሪጎዥን በአፍሪካ ያላቸውን ተግባር እንደሚቀጥሉ ገለጹከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ የጠፋባትን ወታደር ለመፈለግ ወደ ሰሜን ኮሪያ የደወለችው ስልክ አለመነሳቱን ገለጸች20 ሀምሌ 2023
- ጃፓን ላይ የወረደው አቶሚክ ቦምብ ፈጣሪ፤ ሮበርት ኦፕንሃይመር ማን ነው?ከ 5 ሰአት በፊት
ምንም እንኳ ለጊዜው የፈላጊዎቹ ፖሊሶች ቁጥር ቢቀንስም ፍለጋው ግን እንደሚቀጥል ተገልጧል።
የአካባቢው ከንቲባ ማይክል ግሩበርት እንደሚሉት የአንበሳዋ ማንነት እስካሁን ሊረጋገጥ አልቻለም።
ትዊተር የተሰኘው ሐሳብ መጋሪያ ላይ የተለጠፈው ምስል እንደሚያሳየው ጥቅጥቅ ባለው የበርሊን አፋፍ ላይ የታየችው እርግጥም አንበሳ ናት።
አንበሳዋ ከየት እንደመጣች አልታወቀም። በሥፍራው ያሉ የእንስሳት ማቆያዎች ደግሞ እኛ ምንም እንሰሳ ሾልኮ አልወጣብንም ይላሉ።
የፖሊስ አፈ ቀላጤ ዳንዔል ኪፕ ለቢቢሲ እንደገለጡት “ለወትሮው በበጋ ወራት ሰዎች አዞ አየን ብለው ሲጣራ ዳክዬ ሆኖ ይገኛል። የዘንድሮው ግን ቀልድ አይደለም። አንበሳዋ እያጓራች አካባቢውን ስታምስ አይተናል።”
ከቤታቸው እንዳይወጡና የቤት እንስሶቻውን እንዲጠብቁ የተነገራቸው የሥፍራው ነዋሪዎች አንበሳዋን ካዩ ቶሎ እንዲሸሸጉ ተመክረዋል።
“ድንጋጤ ልንፈጥር አሊያም ልናሸብር አይደለም. . . ቢሆንም ሰዎች በእግርም ሆነ በብስክሌት ሥፍራውን ባይቃኙ መልካም ነው” ይላሉ ግሩበርት።
“የመጀመሪያው ዓላማችን አንበሳዋን በሕይወት መያዝ ነው። ሌላ አማራጭ የምንወስደው የፖሊስ አሊያም የሌሎች ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ከወደቀ ብቻ ነው።”
ሄሊኮፕተሮች፣ ድሮኖችና የሰውነት ሙቀት መጠን የሚለዩ ካሜራዎች ፍለጋ ተሰማርተዋል።
የእንስሳት ሐኪሞችና ማደንዘዣ የታጠቁ አዳኞችም ፍለጋውን ተቀላቅለዋል። መገናኛ ብዙሃንና ፖሊስ በፍርግርግ በታጠረ መኪና ነው የሚንቀሳቀሱት።
“አንበሳዋን ካያችሁ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ተረጋጉ፤ ከቻላችሁ ወደ መኪና አሊያም ሕንፃ ተጠጉ” የሚል ምክር የለገሰው በሥፍራው ያለ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ነው።