July 21, 2023 – BBC Amharic 

በራሪ ታክሲ

ከ 4 ሰአት በፊት

እምብራየር የተባለው የብራዚሉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ሳዎ ፓውሎ አቅራቢ በራሪ ታክሲዎች የሚያመርት ፋብሪካ ሊገነባ ነው።

ኩባንያው እንደሚለው በኤሌክትሪክ የሚሠሩት በራሪ ታክሲዎች በፈረንጆቹ 2026 ሰማይ ላይ ይወጣሉ።

እኒህ በራሪ ታክሲዎች የሚመረቱት ኢቭ በተሰኘው የእምብራየር አጋር ድርጅት ነው።

ልክ እንደ አነስተኛ እንደሄሊኮፕተር ሆነው የሚሠሩት የሰማይ ታክሲዎች ስድስት ሰው የማሳፈር አቅም ይኖራቸዋል።

ሰማይ ላይ ወጥተው ጉዞ ሲጀምሩ ለአንድ ጉዞ ከ50-100 ዶላር በነብስ ወከፍ ያስከፍላሉ።

ኢቭ የተሰኘው ድርጅት እንዳለው 3 ሺህ ታክሲዎችን ለማምረት ትዕዛዝ ተቀብሏል።

ድርጅቱ የያዝነው ዓመት ሳይገባደድ ሞዴሉን ቀድሞ እንደሚሠራ ገልጧል።

የዩኤስ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት በራሪ ታክሲዎች በፈረንጆቹ 2025 ለገበያ ይቀርባሉ ሲሉ የጊዜ ሰሌዳ አውጥተዋል።

ይህ በራሪ ታክሲ ልክ እንደ አውሮፕላን የሚንደረደርበት የተለጠጠ መንገድ ባይፈልግም፤ ነገር ግን ረዥም ርቀት መጓዝ ይችላል።

በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በራሪዎች ከመደበኛው አውራፕላን ያነሰ ድምፅና አየር በካይ ጭስ ያመነጫሉ።

በራሪው ታክሲ ዋጋው ተመጣጣኝ ከሆነ በትራፊክ ለተጨናነቁ ከተማዎች እፎይታን ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

አልፎም ዕቃ ለማጓጓዝ ጥሩ መላ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ፋብሪካው ከብራዚሏ የንግድ ከተማ ሳዎ ፓውሎ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የታውባቴ ከተማ ይገነባል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው ድሮን መሰሉ ተሽከርካሪ መጀመሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው ለታክሲ አገልግሎት ነው።

የመጀመሪያው በረራ ፓይለት ይኖረዋል፤ ቀስ በቀስ ግን አብራሪ አልባ ታክሲዎች ለገበያ እንደሚቀርቡ የድርጅቱ ዕቅድ ያሳያል።

ታክሲዎቹ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ስለሚሠሩ ከካርበን የፀዳ በረራ ያደርጋሉ።