
ከ 3 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቫግነሩ መሪን ጊዜ እየጠበቁላቸው እንደሆነ የሲአይኤ ዳይሬክተር ተናገሩ።
ቅጥረኛ ተዋጊው ቫግነርን እየመሩ ያለው የቭገኒ ፕሪጎዢን ባለፈው ወር በሩሲያ ላይ ወታደራዊ አመጽ አውጀው ከ24 ሰዓታት በኋላ መክሸፉ ይታወሳል።
ፕሪጎዢን አቅደውት የከሸፈው ይህ አመጽ ፑቲን በገነቡት አይነኬ የአስተዳደር ስርዓት ላይ ያሉ ጉልህ ድክመቶችን ያጋለጠ ነው ሲሉም የሲአይኤ ኃላፊ ዊሊያም በርንስ ተናግረዋል።
ኃላፊው በአስፐን የጸጥታና የደህንነት ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የሩስያው መሪ በፕሪጎዢን ላይ የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብለዋል።
“እየተመለከትን ያለነው በጣም የተወሳሰበ ዳንስ ነው” ሲሉም ኃላፊው ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።
ፕሪጎዢን ቤላሩስ ታይተዋል ተብሎ ስለወጣው ቪዲዮ የተጠየቁት ኃላፊው በቤላሩሷ መዲና ሚንስክ እንዲሁም በሩሲያ እንደነበሩም ተናግረዋል።
ፑቲን በቫግነሩ መሪ ላይ የተሻለ ዕቅድ ለመጠንሰስም ጊዜ ሊገዙ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ቅጥረኛው ተዋጊው ቡድን አሁንም ቢሆን እንደ አፍሪካ እንደ አህጉር፣ ሊቢያ እና ሶሪያ ባሉ አገራት ለሩሲያ አመራሮች ዋጋ አለው ብለዋል።
- የቫግነሩ መሪ ቤላሩስ ገብተው ለወታደሮቻቸው “ንግግር ሲያደርጉ ታዩ”20 ሀምሌ 2023
- የቫግነር ቡድን አባላት ቤላሩስ መግባታቸውን የሳተላይት ምሥሎች አሳዩ19 ሀምሌ 2023
- በክሪሚያ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ፈንድቶ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ19 ሀምሌ 2023
እናም ፕሬዚዳንት ፑቲን ቡድን ከመሪው ለመነጠል ሊሞክሩ ይችላሉም ብለዋል።
ፑቲን በቀላቸውን ለመወጣት ሊጠብቁ እንደሚችሉም የሲአይኤ ኃላፊ ተናግረዋል።
“ፑቲን በአጠቃላይ በቀልን አሰላስሎና ባልጠበቀው ሰዓት የሚፈጽም ነው” ብለዋል ኃላፊው
አክለውም “በእኔ ልምድ ፑቲን ለተፈጸመበት ነገር ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ የማይል ሰው ነው ስለዚህ ፕሪጎዢን ከተጨማሪ ቅጣት ቢያመልጥ ነው የሚገርመኝ” ሲሉም አስረድተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የቫግነር መሪ የመመረዝ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።
“እኔ እሱን [የቫግነሩን መሪ] ብሆን የምበላውን ምግብ እጠነቀቅ ነበር፤ አይኔን ከምግቡ ላይ አልነቅልም ነበር” ሲሉም የሲአይኤ ኃላፊ አሹፈዋል።
“ፕሪጎዢን ብሆን የምግብ ቀማሼን አላባርረውም ነበር” ሲሉም የፕሬዚዳንት ባይደንን ሃሳብ አስተጋብተዋል።