
ከ 5 ሰአት በፊት
ሐምሌ 16 ንጋት 1945 (እአአ) ሮበርት ኦፕንሃይመር ከአንድ ክፍል ሆኖ ዓለምን ሊቀይር የሚችል ክስተት ይጠባበቃል።
10 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ‘ትሪኒቲ’ የተሰኘ ስም የተሰጠው የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ሙከራ ሊካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ሙከራው በአሜሪካዋ ግዛት ኒው ሜክሲው ውስጥ ዮርናዳ ዴል ሙዌርቶ በረሃ ነው የሚከወነው።
ኦፕንሃይመር ተጨንቋል። ለወትሮውም ቀጫጫ ነበር፤ ያን ሰሞን ግን ‘ፕሮጀክት ዋይ’ የተባለው “የማንሃታን ፕሮጀክት” ጉዳይ ሰውነቱን በላው።
የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ አቶሚክ ቦምብ መገንባት ነው።
ኦፕንሃይመር የዚህ ፕሮጀክት አባት ነበር። ጭንቀቱ አክስቶት 52 ኪሎ ግራም ደርሷል። ቁመቱ 178 ሴንቲ ሜትር ነው። ቅጥነቱ እና ቁመቱ ተደባልቀው እንደ ፌስታል በነፋስ ሊበር የተዘጋጀ መስሏል።
ያን ሌሊት ለአራት ሰዓታት ብቻ ነው ያሸለበው። ጭንቀቱን በሲጋራው ጭስ አሳፍሮ እያበነነ ነው ያደረው።
የታሪክ ፀሐፊዎቹ ካይ በርድ እና ማርቲን ሼርዊን 2005 አሜሪካን ‘ፕሮሚቲየስ’ የተሰኘ የኦፕንሃይመርን ሕይወት የሚዳስስ መፅሐፍ አሳትመዋል።
መፅሐፉ ላይ እንደሚጠቅሱት ያቺ ቀን ለኦፕንሃይመር ልዩ ቀን ነበረች።
ይህን መፅሐፍ አድርጎ የተሠራው የክሪስቶፈር ኖላን ፊልም ‘ኦፕንሃይመር’ ሐምሌ 21/2023 በዩናይትድ ስቴትስ ይለቀቃል።
በርድና ሼርዊን በመፅሐፋቸው እንደሚገልጡት ልክ የሙከራው ቦምብ ሊፈነዳ ቆጠራ ሲጀምር አጠገቡ የነበሩት ጄኔራል፣ ኦፕንሃይመርን በንቃት ሲመለከቱ የተሰማቸውን እንዲህ ይገልጣሉ “ቆጠራው እየጨመረ ሲመጣ የዶክተር ኦፕንሃይመርም ጭንቀት እያየለ መጣ። ሲተነፍስ እንኳ አይሰማም ነበር።”
ቦምቡ ሲፈነዳ የፈነጠቀው ብርሃን የፀሐይ ብርሃንን ኢምንት አደረገው። ይህ ፍንዳት መቼም ታይቶ አይታወቅም። የፈጠረው ንቅናቄ እስከ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ተሰምቷል።
የፍንዳታው ድምፅ መልክዓ ምድሩን ሲያናጋው፣ ነጩ ሰማይ የጅብ ጥላ በመሰለ ጭስ ታፈነ።
ኦፕንሃይመር በረዥሙ ተነፈሰ።
“እንዴት ይራመድ እንደነበር በፍፁም አልረሳውም፤ ከመኪናው እንዴት እንደወረደ ከአእምሮዬ አይጠፋም…” ይላል የኦፕንሃይመር የቅርብ ጓደኛ የነበረው አይሲዶር ራባይ።
- ከሂሮሺማ እና ከናጋሳኪ የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት ለወሬ ነጋሪነት የተረፉት ሴቶች9 ነሐሴ 2020
- የዓለምን የጦርነት ገጽታ ይቀይራል የተባለው የሩሲያው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል22 መጋቢት 2023
- ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በማን እጅ ነው ያለው?7 መጋቢት 2022
በ1960ዎቹ ኦፕንሃይመር በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ልክ ቦምቡ ሲፈነዳ ከአንድ የሂንዱ መፅሐፍ የባጋቫድ ጊታ መስመር ትዝ እንዳለው ይጠቅሳል። እንዲህ ይነበባል “እነሆ አሁን እኔ ሞት ሆኛለሁ። የዓለማት አውዳሚ።”
ከፍንዳታው በኋላ ባሉት ቀናት ድባቴው እየባሰበት እንደመጣ በወቅቱ የሚያውቁት ጓደኞቹ ይናገራሉ።
“ሮበርት በጣም ቀዝቃዛ እና ቆዛሚ ሰው ሆኖ ነበር። በተለይ ደግሞ በእነዚያ ሁለት ሳምንታት። ምክንያቱም ምን ሊመጣ እንደሚችል ያውቀዋል” ይላል አንድ ጓደኛው።
አንድ ጠዋት የጃፓኖችን ዕጣ ፈንታን በተመለከተ “እኒህ ምስኪን ሕዝቦች። እኒህ ምስኪን ሕዝቦች” እያለ ሲያጉተመትም ተሰምቷል።
ከቀናት በኋላ እነሆ ኦፕንሃይመር ድጋሚ በጭንቀት ተወጥሮ በጥሞና እና በፍርሃት ተውጦ ተገኘ።
“እኒህ ምስኪን ሕዝቦች” ያላቸውን ሰዎች የረሳቸው ይመስላል። ከወታደራዊ አመራር ጓደኞቹ ጋር ስብሰባ ተቀምጧል።
በርድና ሸርዊን እንደሚሉት በጣም አሳስቦት የነበረው ጉዳይ “ቦምቡ እንዴት ባለ ሁኔታ ይጣል?” የሚለው ነበር።
“በፍፁም ዝናብ ወይም ደመና ባለበት ሊጣል አይገባም። ከፍ ብሎ ከፈነዳ ዒላማው ላይ የታሰበውን ያህል ጉዳት ላያመጣ ይችላል።”
ትሪኒቲ የተሰኘው የሙከራ ፍንዳታ ከተደረገ ከአንድ ወር በኋላ የጃፓኗ ሂሮሺማ በአቶሚክ ቦምብ ብትንትኗ ወጣ።
ኦፕንሃይመር ይህን ዜና ለሥራ ጓደኞቹ ካሳወቀ በኋላ “ሁለት እጆቹን አጣምሮ ጭንቅላቱን አስደግፎ ልክ አንድ ሽልማት እንዳሸነፈ ግለሰብ ነበር የሆነው” ይላል አንድ በሥፍራው የነበረ ግለሰብ።
“ጭብጨባው ጣራ ነካ።”
ኦፕንሃይመር የማንሃታን ፕሮጀክት አንጎል እና ልብ ነበር። በዚህ ፕሮጀክት ላይ ከተሳተፉ ሰዎች እንደሱ ማንም ነብስ እና ሥጋውን ለሥራው አልሰጠም ይላሉ።
ጄሬሚ በርንስታይን ከጦርነቱ በኋላ ከኦፕንሃይመር ጋር ሠርቷል። 2004 (እአአ) ባሳተመው አንድ መፅሐፍ ላይ “ኦፕንሃይመር በዚህ ፕሮጀክት ላይ ባይሳተፍ ኖሮ፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ኒውክሌር መሣሪያ ጥቅም ላይ ሳይውል ሊጠናቀቅ ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ።”
ብዙዎቹ ኦፕንሃይመር የልፋቱ ውጤት “ፍሬ ሲያፈራ” የተሰማውን ስሜት በተለያየ መንገድ ገልፀውታል።
በርድ እና ሼርዊን ኦፕንሃይመርን “አንዳች ሊረዱት የሚከብድ ፍጥረት ነው” ይሉታል።
“የፊዚክስ ንድፈ-ሐሳብ ልሂቅ፤ የአንድ ታላቅ መሪን ግርማ ሞገስ የተላበሰ፤ ጥበብ እና ውበት የሚያስደስቱት ሳይንቲስት።”
ነገር ግን አንዳንድ ጓደኞቹ በዚህ አይስማሙም።
1904 ኒው ዮርክ ከተማ የተወለደው ኦፕንሃይመር የመጀመሪያው የጀርመን እና የአይሁድ ትውልድ ውጤት ነው።
በላይኛው ምዕራብ ኒው ዮርክ ከሚገኘው ግዙፉ የቤተሰቡ ቤት ውስጥ በቤት ሠራተኞች፣ በሹፌሮች እና በአውሮፓ የጥበብ ውጤቶች ተከቦ ነው ያደገው።
ምንም እንኳ እንዲህ ተንደላቆ ቢኖርም የልጅነት ጓደኞቹ ሞልቃቃ ሳይሆን እንደውም ለጋስ ነበር ይሉታል።
የትምህርት ቤት ጓደኛው ጄን ዲዲሻይም “ዐይን አፋር ቢሆንም በጣም ብሩህ ጭንቅላት የነበረው ልጅ ነበር” ትላለች።

ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነው በግሪክ እና በላቲን ቋንቋዎች የተጻፉ የፍልስፍና ሥራዎችን ያነብ የነበረ ኦፕንሃይመር ያደገበትን ቤት ትቶ ኬሚስትሪ ለማጥናት ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ገባ።
ነገር ግን ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሳለም ይሁን ወደ እንግሊዝ አቅንቶ ኬምብሪጅ ሲማር ሕይወቱ ቀላል እንዳልነበረ በወቅቱ ይፅፋቸው የነበሩ ደብዳቤዎች ያሳብቃሉ።
በአንድ ወቅት ኦፕንሃይመር ከግል አስተማሪው ጋር ባለመስማማቱ ምክንያት በላቦራቶሪ ኬሚካል የተሞላ አፕል ከመምህሩ ጠረጴዛ ላይ ትቶ ይሄዳል።
አጋጣሚ ሆኖ አስተማሪው አፕሉን ሳይበላ ቀረ። ነገር ግን ኦፕንሃይመር ኬምብሪጅ የሚቆየው የአእምሮ ጤና ባለሙያን ከጎበኘ ብቻ እንደሆነ ተነገረው።
ኦፕንሃይመር ይህን ወቅት ወደኋላ መለስ ብሎ ሲያስታውስ፣ ብዙ ጊዜ በተለይ ደግሞ የገና በዓል አካባቢ ራሱን ለማጥፋት ያስብ እንደነበር ይናገራል።
የሥነ-አእምሮ ባለሙያ ያልረታው የኦፕንሃይመር ጭንቅላት ለንባብ ተረታ። ሁሉን እርግፍ አድርጎ ትቶ እየተራመደ ሳይቀር ያነብ ገባ።
በ1926 ወደ እንግሊዝ ሲመለስ የጀርመን ጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ንድፈ-ሐሳብ ክፍል ኃላፊ የሆኑትን ሰው አገኛቸው።
ኃላፊው ወደ ተቋሙ መጥቶ የፊዚክስ ትምህርት እንዲማር ጋበዙት። ለዚህ ነው ኦፕንሃይመር “1926ን ወደ ፊዚክስ የመጣሁበት ዓመት ነው” ሲል የፃፈው።
ወደ አሜሪካ ተመልሶ ሃርቫርድ ለጥቂት ወራት ከቆየ በኋላ ወደ ካሊፎርኒያ አቀንቶ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ።
ኦፕንሃይመር በ1940 ከባዮሎጂስቷ ካትሪን ሐሪሰን ጋር ጋብቻ ፈፀመ።
በ1939 የፊዚክስ ሙያተኞች ስለኒውክሌር ጦርነት ከፖለቲከኞች በላይ ይጨነቁ ነበር። ይሄኔ ነው አልበርት አይንስታይን የፃፈው ደብዳቤ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ቀልብ የገዛው።
በ1942 ኦፕንሃይመርና አብረውት የሚሠሩት ጓደኞቹ ቦምብ መሥራት እንደሚቻል ለአሜሪካ መንግሥት አሳዩ። እንደ ሳይንቲስት እኛ ቦምቡ መሥራት እንጂ ለምን እንደሚውል አያገባንም የሚል ዓይነት አቋም ነበረው።
በስተመጨረሻም ያሰበው ተሳክቶ ዘ ማንሃታን ፕሮጀክት በተሰኘው ፕሮግራም ሥር አቶሚክ ቦምብ እንዲሠራ ሆነ።
ኦፕንሃይመር በመጨረሻዎቹ ዓመታት ቦምቡን በመሥራቱ ቢደሰትም፣ ባደረሰው ውድመት ግን ያዝን እንደነበር ይነገራል።
የመጨረሻዎቹን የሕይወቱን 20 ዓመታት ፕሪንስተን ውስጥ ከእነ አልበርት አይንስታይን ጋር ሲያስተምር ኖረ።