
ከ 2 ሰአት በፊት
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ካደረገው የጥቁር ባህር እህል የመላክ ስምምነት ሩሲያ በተናጠል መውጣቷን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማስረዳታቸውን አስታወቁ።
በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ተደረገ በተባለው የሐምሌ 13 የስልክ ልውውጥም ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሩስያ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እህል እንዲተላለፍ ከተደረሰው ስምምነት ራሷን አግላለች ሲሉ መናገራቸውን ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።
ሩሲያና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ጋር በመሆን በጥቁር ባህር በኩል ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ ለመክፈት መስማማታቸውንም ተከትሎ እህል ለተለያዩ አገራት እየተላከ እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያም ከዚህ ተጠቃሚ እንደነበረች ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነግሬያቸዋለሁ ብለዋል።
በጥቁር ባህር ስምምነት ኢትዮጵያ 300 ሺህ ቶን ምግብ እንደተላከላት እንዲሁም በተጨማሪም በዩክሬን ሰብዓዊ ተነሳሽነትም 90 ሺህ ቶን እህል ተልኮላታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በተናጠል በጥቁር ባህር በኩል ይደረግ ከነበረው የእህል ማጓጓዝ ስምምነት ራሷን አውጥታለች እንዲሁም “የቅኝት ስራዎችን በህገወወጥ መንገዶች እያገደች ነው፣ የዩክሬንን ወደቦችና የኃይል መሰረተ ልማቶች እያወደመች ነው ሲሉም” ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ በስልክ ነግሬያቸዋለሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጋር በስልክ ስለመወያየታቸው ሐምሌ 13/ 2015 ዓ.ም ባወጡት በትዊተር መልዕክታቸው ገልጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርዘር ያለ መረጃ ባይሰጡም በሁለትዮሽ እና አለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሰላም የሚመጡበት መንገዶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሩሲያ ወደ ዩክሬን የሚያመሩ መደቦች እንደ ወታደራዊ ኢላማ ሊቆጠሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቂያ ከሰሞኑ ማስተላለፏን ተከትሎም ዓለም አቀፉ የስንዴ ዋጋ መናሩ ተዘግቧል።
እንዲሁም በኦዴሳ ወደቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በጥቁር ባህር አካባቢ ያሉ ሌሎች አገራትም የእቃ ጫኝ መርከቦች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማለፍ እንዲችሉ ጣልቃ መግባት አለባቸው ሲሉም ከሰሞኑ ዘለንስኪ አሳስበዋል።
ዩክሬን የአለም ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዋስ ሆና ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን ዘለንስኪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጨላቸዋለሁ ብለዋል።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር በጸጥታ፣ በዲጂታይዜሽን እና በሌሎችም የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመመስረት ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ከአፍሪካ አገራት ጋር የውይይት መድረክ መፍጠርን አስፈላጊነት አጽንኦት መስጠታቸውን አስፍረዋል።
“የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረት የመላው አፍሪካ ድምጽ ለኛ በጣም ጠቃሚ ነው” ሲሉም ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን አስረድተዋል።
- ዩክሬን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ አገራት የምትልከው እህል ምን ያህል ነው?24 ነሐሴ 2022
- ሩሲያ ወደ ዩክሬን የሚያመሩ መርከቦችን በተመለከተ በሰጠችው ማስጠንቀቂያ የስንዴ ዋጋ ናረ20 ሀምሌ 2023
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዚህ የስልክ ንግግራቸው አገራቸው ለዓለም አቀፉ የሰላም ጉባኤ እያደረገችው ስላለው ዝግጅት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።
ሩሲያ በወደቦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ያነሳችው ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም ሲሆን ይህም መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል ባለው መተላላፊያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ አስችሏቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን እህል ዋነኛ ገዥ ሲሆን፤ ይህንንም እህል በረሃብ አደጋ ውስጥ ወደሚገኙ አገሮችም ይልካል። የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዩክሬን ለኢትዮጵያ የገዛው ስንዴ በጂቡቲ በኩል መላኩ ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀው ስንዴው ተቋሙ በጦርነት እና በአስከፊ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመመገብ የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል።
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልል በተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት በርካታ ሚሊዮኖች የእርዳታ ጥገኛ ሆነዋል። እንዲሁም በሶማሌና ክልልም በተከታታይ የዝናብ እጥረት ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች በድርቅ የተጠቁ ሲሆን የዓለም ምግብ ፕሮግራም እነዚህን ነዋሪዎች ለመደጎምም ከዩክሬን እህል እንደሚገዛም ማስታወቁ ይታወሳል።
ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) እንዴት ነው የሚሠራው?
ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመው ነበር።
የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?
- ከኦዴሳ እና ሁለት አጎራባች ወደቦች ወደ ኢስታንቡል የባሕር ዳርቻ መተላለፊያ (ኮሪደር) 310 ማይል የባሕር ርዝመት (357 ማይል) እና ሦስት የባሕር ማይል ስፋት ያለው
- መሣሪያ በተጠመደባቸው የወደብ ውሃ ውስጥ የዩክሬን መርከቦች ወደ ውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ የእህል ጭነት መርከቦችን እንዲያጅቡ
- ጭነቶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምታለች
- የሩሲያ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ስጋት ለማስወገድ ቱርክ መርከቦችን እንድትመረምር
- ሩሲያ በጥቁር ባሕር በኩል እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ መላክ ተፈቅዶላታል
- ስምምነቱ ከ120 ቀናት በኋላ ማለትም በኅዳር አጋማሽ ያበቃል