ዳግም ተስፋዬ ለእናቱ ሜዳሊያ ሲሰጥ

ከ 1 ሰአት በፊት

ዳግም የ2015 ዓ.ም የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነው።

የተሸለመውን ሜዳሊያ ለእናቱ ሸልሟል።

ከእነ ዳግም ቤተሰብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያልሄደችው እናቱ ብቻ ናት።

“እናቴ እኔን ለማስተማር እሷ 12ኛ ክፍል አቋረጠች” ይላል ዳግም።

“ትምህርት ካልገባሁ እያልኩ አስቸገርኳት፣ ያኔ እሷ በግል ትማር የነበረውን ትምህርት አቋርጣ እኔን አስገባችኝ። በመሆኑም ዛሬ እኔ ያገኘሁት ሜዳሊያ የእርሷም ስለሆነ ነው የሸለምኳት” ዳግም ሜዳሊያውን ለምን ለእናቱ እንደሰጠ ሲጠየቅ ለቢቢሲ የሰጠው ምላሽ ነው።

ዳግም ተስፋዬ ይባላል።

ተወልዶ ያደገው ባሕር ዳር ነው።

ለቤተሰቦቹ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው።

በዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ከታዩ ክስተቶች የዳግም ተስፋዬ ውጤት አንዱ ነው።

ዳግም የተማረው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ነው።

እንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ምርጫው አልነበረም።

አዲስ አበባ ወይም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመማር ነበር ቀዳሚ ምርጫውን ያስቀመጠው።

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያመጣው ከፍተኛ ውጤት ደግሞ ይህንን ምርጫውን እንደሚያስጠብቅለት እርግጠኛ ነበር።

ነገር ግን አንደኛና ሁለተኛ ምርጫው አልተጠበቀለትም።

“አመዳደባችን ላይ ችግር ነበር፣ የእኛ አካባቢ ተማሪዎችን እዚሁ አካባቢ ነበር የመደቡን” በማለት ምርጫው ያልተከበረለትን ምክንያት ያስረዳል።

ዳግም እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ፕላንት ሳይንስን ለመማር መረጠ።

ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ የተቋቋመ እንደመሆኑ ብዙ የትምህርት ዘርፎችን ምርጫ ውስጥ ለማካተት ለዳግም አልተሳካለትም። “ከነበሩት የትምህርት አይነቶች የተሻለ መስሎ የታየኝን መርጨ ተማርኩ” ይላል የፕላንት ሳይንስ ተመራቂው ዳግም።

ዳግም በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አራት ዓመታትን አሳልፏል።

በአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታው 64 ኮርሶችን ወስዷል።

ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ብቻ ኤ (A) ሆነውበታል። 61ዱ ኤፕላስ (A+) ናቸው።

ትልቅ ውጤት በማስመዝገቡ ዳግም ደስተኛ ነው።

ነገር ግን በድንገት የተፈጠረ ደስታ አይደለም ይላል።

ላለፉት ዓመታት በተከታታይ ያደረግኩት “የጥረት ውጤቴ” ስለሆነ ዛሬ የምረቃ ቀን በመሆኑ ብቻ እንደተለየ ቀን አላየውም ይላል።

ዳግም ለስኬቱ ሁለት ነገሮችን በዋናነት ይጠቅሳል። የመጀመሪያው “ራስን መግዛት” መሆኑን ይገልጻል። በወጣትነት ዕድሜ ብዙ ፍላጎቶች ይኖራሉ።

እነዛን ፍላጎቶች በመግታት ለዓላማ ብቻ ራስን መግዛት መቻሉ የስኬቱ ዋነኛ ምንጭ እንደሆነ ይገልጻል።

ሁለተኛው የዳግም የስኬት ምንጭ ቤተሰብ መሆኑን ይናገራል።

“ቤተሰቦቼ የሰጡኝ ነጻነት እና በራሴ እንድወስን ማድረጋቸው ዓላማዬን እንዳልዘነጋ አድርጎኛል” ይላል።

ዳግም ስለቤተሰቦቹ በብዛት ማውራት ይወዳል።

ባስመዘገበው ስኬት ደስተኛ ያደረገው የቤተሰቦቹን ደስታ ማየት በመቻሉ እንደሆነ ይናገራል።

“ለእነሱ ብዬ እንደተማርኩ ነው የሚገባኝ” የሚለው ዳግም፣ እነርሱ [ቤተሰቦቹ} ላደረጉልኝ ነገር ዋጋ መክፈል ካለብኝ በዚህ መልኩ ደስታቸውን ማየት ነው ይላል።

በእንጅባራ እና በባሕርዳር መካከል ያለው ርቀት ቅርብ ቢሆንም ዳግም ብዙ ጊዜ ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ ባሕርዳር አይሄድም።

በዚህ ቤተሰቦቹ ደስ ባይላቸውም “ለትምህርቴ ሲሉ ተቀብለውት ቆይተዋል፣ ይህም በነጻነት ትምህርቴ ላይ እንዳተኩር አግዞኛል” ይላል።

ዳግም እና እናቱ

ዳግም ፕላንት ሳይንስ የመጀመሪያ ምርጫው አልነበረም።

ፍላጎቱ በጤና ዘርፍ መማር ነበር።

ይህንን ፍላጎት ግን የመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ምርጫው ባለመሳካቱ አልተሳካም።

“በዩኒቨርሲቲው የዲፓርትመንት እጥረት ስላለ የፈለግነውን መምረጥ አልቻልንም። በመሆኑም ካሉት የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ያልነውን መርጠን ነው የተማርነው” ይላል ዳግም።

እስካሁን የሥራም ሆነ የትምህርት ዕድል እንዳልቀረበለት ዳግም ተናግሯል። የትምህርት ዕድል ካገኘ በተለይም ደግሞ ለየት ያለ ትምህርት ቅድሚያ መስጠት ይፈልጋል።

በተማረበት የፕላንት ሳይንስ ግብርና ላይ የሚታይ ለውጥ የማምጣት ዕቅድ አለው።

“የተማርሁት ትምሀርት በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው። በመሆኑም በግሌም ሆነ በብዙ አርሶ አደሮች ዘንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሥራ የመሥራት ዕቅድ አለኝ፝” ብሏል የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የሜዳሊያ ተሸላሚው ዳግም ተስፋዬ።