
ከ 5 ሰአት በፊት
ከሁለት ዓመት በፊት ሙከራ ላይ መዋሉ በተገለጸው ዲጂታል መታወቂያ ለመጠቀም 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መመዝገባቸው ተገለጸ።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም 70 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የመመዝገብ እቅድ እንደተያዘም ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ እና በተወሰኑ የክልል ከተሞችም በባለፉት ሁለት ዓመታት የሙከራ ምዝገባ ተጀምሮ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
አቶ አቤኔዘር እንደሚሉት የዲጂታል መታወቂያ የቀበሌ መታወቂያን አይተካም።
በዋነኝነት የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሰጪዎች የግለሰቦችን ማንነት ለመለየት እንደ መነሻ እንዲያገለግል ሆኖ መዘጋጀቱን ያስረዳሉ።
ዲጂታል መታወቂያ ግለሰቦች ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል እና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ታማኝ ዲጂታል ማረጋገጫ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ያብራራሉ።
በአሁኑ ሰዓት የዲጂታል መታወቂያ ዋነኛ ዓላማ ሁሉም ሰዎች አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ማስቻል መሆኑን የሚናገሩትአቶ አቤኔዘር፣ በዚህም የተነሳ ነዋሪነታቸውን በሕጋዊ መንገድ በኢትዮጵያ ያደረጉ በሙሉን እንደሚመዘግቡ ያስረዳሉ።
“ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚኖሩ ሰዎች ዲጂታል መታወቂያ አውጥተው መጠቀም ይችላሉ።”
- ኢንስትራክተር ሠላም፡ የሉሲዎቹ የቀድሞ አሰልጣኝ የላይቤርያ ብሔራዊ ቡድንን በኃላፊነት ተረከበች20 ሀምሌ 2023
- በጠለፋ ዙሪያ የሚካሄድ ባሕላዊ ሽምግልና ከኢትዮጵያ ሕግ ጋር ይቃረናል?20 ሀምሌ 2023
- የአዳዲስ ክልሎች መፈጠር በደቡብ ኢትዮጵያ ሲነሳ ለቆየው ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል?12 ሀምሌ 2023
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስር የሚመራ ፕሮግራም ነው።
ይህ ፕሮግራም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመጣው ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማም ለኢትዮጵያ ነዋሪዎች በሙሉ የተለየ የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት ነው።
ይህ የነዋሪነት መታወቂያ “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርህ ይዞ የግለሰቡን መረጃዎች በመውሰድ የራሱ የሆነ የነዋሪነት መታወቂያ እንዲኖረው ማድረግ መሆኑን ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አብራርተዋል።
ድርጅታቸው የሚሰጠው መሠረታዊ መታወቂያ የሚባለውን መሆኑን የሚናገሩት አቶ አቤኔዘር፣ ይህም ማለት የአንድን ግለሰብ ማንነት ብቻ ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ያስረዳሉ።
ነገር ግን የግለሰቡን ማንነት ለማረጋገጥ የሚረዱ መረጃዎችን በአጠቃላይ እንደሚይዝም አክለው ገልፀዋል።
እንደ አቶ አቤኔዘር ገለጻ ለዲጂታል መታወቂያ ለመመዝገብ አንድ ግለሰብ ሕጋዊ የሆነ ማንነቱን የሚገልጽ ፓስፖርት፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የልደት ምስክር ወረቀት፣ የእድር ደብተር የመሳሰሉትን ይዞ መምጣት ብቻ በቂ ነው።
በምዝገባው ወቅትም የግለሰቡ ስም፣ የትውልድ ቀን፣ የሚኖርበት አድራሻ እና ዜግነቱ አስፈላጊ ባይሆንም ስልክ እና ኢሜልም በተጨማሪነት ከሚሰበሰቡት መረጃዎች መካከል መሆናቸውን አቶ አቤኔዘር ያስረዳሉ።
ዲጂታል መታወቂያን ከሌሎቹ መታወቂያዎች የሚለየው የባዮ ሜትሪክ መረጃ አወሳሰዱ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።
ባዮ ሜትሪክ ዳታ ሲወሰድ የአይን አሻራ፣ የአስር ጣት የእጅ አሻራ፣ እና የግለሰቡ ፎቶ ይወሰዳል።
ከዚህ በኋላ ነው ባለ 12 አሃዝ ልዩ የሆነ የዲጂታል የምዝገባ ቁጥር ለተመዝጋቢው በስልክ አድራሻው እንዲደርሰው የሚደረገው።
በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦቹ ይህንን ባለ 12 አሀዝ የዲጂታል መታወቂያ ቁጥር፣ በስልካቸው አልያም በመታወቂያ መልክ ታትሞ እንዲይዙት እንደሚደረግ ጨምረው አስረድተዋል።
ይህንን ባለ አስራ ሁለት አሃዝ መለያ ቁጥር፣ የፋይዳ ቁጥር፣ እንደሚባል የሚናገሩት አቶ አማኑኤል፤ በዚህ ነዋሪዎች ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል።
‘አንድ ሰው አንድ ነው’
በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሆነ የመታወቂያ ስርዓት የለም።
ይህም ማለት በባዮሜትሪክስ የታገዘ መታወቂያ እስካሁን አልነበረም።
በዚህም የተነሳ ይህ “ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ” የመጀመርያው ነው።
አቶ አቤኔዘር አንድ ሰው የዲጂታል መታወቂያ እንዲኖረው ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊ መረጃ እንደሚወስዱ ገልጸው፣ ይህም “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል ልዩ በሆነ ሁኔታ ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ይናገራሉ።
አንድ ሰው የዓይን አሻራውን፣ የአስር የእጅ ጣቶቹን አሻራ እና ምስሉን ከሰጠ በኋላ ሌላ ሰው በስሙ ምንም ዓይነት መረጃ ሊያስገባ እና መታወቂያ ሊያገኝ አይችልም ማለት ነው።
ስለዚህ ከሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ጋር የሚሰጠው ባዮሜትሪክስ ዳታ ተቀናጅቶ የሚሰጠው ባለ 12 አሃዝ የዲጂታል ምዝገባ ቁጥር የግለሰቡ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
እስካሁን ድረስ አንድ ግለሰብ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተመሳሳይ ስም፣ የተለያዩ መታወቂያዎችን በማውጣት መጠቀም የተለመደ ነው።
ይህ የዲጂታል መታወቂያ ግን ይህንን ያስቀራል።
ስለዚህ ግለሰቦች በተሰጣቸው የመለያ ቁጥር በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ።
ስለዚህ አንድ ግለሰብ መረጃውን የሚሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ብቻ ባለ 12 አሃዙ የመለያ ቁጥር ይሰጠዋል።
ሌላ ግለሰብም በአንድ ግለሰብ ስም ሌላ ዲጂታል መታወቂያ ሊያወጣ አይችልም።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ባዮሜትሪክስ ዳታም ግለሰቡን የሚመዘግበውም ሆነ የሚለየው አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ ነው።
የዲጂታል መታወቂያ ዓላማ?
የዓለም ባንክ በ2018 እኤአ ባወጣው ጥናት መሰረት በዓለም ዙርያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ማስረጃ የላቸውም።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ 81 በመቶ ያህሉ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል ነው።
በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች መሠረታዊ ከሆኑ የጤና፣ የትምህርት፣ የማህበራዊ ጥበቃና ፋይናንስ አገልግሎቶች ይገለላሉ ይላል ጥናቱ።
አቶ አቤኔዘር ደግሞ አሁን ባለው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት 40 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕጋዊ የሆነ መታወቂያ የለውም ይላሉ።
ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ሕጋዊ የሆነ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸውም ቢሆኑ፣ መረጃቸው ዲጂታል በሆነ መንገድ አይገኝም።
ስለዚህ የተለያዩ መንግሥታዊ የሆኑ እና የግል አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሰዎችን ባላቸው የዲጂታል መታወቂያ ተጠቅመው አገልግሎት ማቅረብ ፈተና ይሆንባቸዋል።
ከእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱ የፋይናንስ ዘርፉ ተጠቃሽ መሆኑን አቶ አቤኔዘርበምሳሌነት ያነሳሉ።
ባንኮች ተፈላጊውን አገልግሎት ያለምንም ስጋት ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ ማነቆ ከሚሆንባቸው ነገሮች መካከል አንዱ፣ አስተማማኝ የሆነ እና ተዓማኒነት ያለው የዲጂታል መታወቂያ አለመኖሩ ነው።
ባንኮች ውስጥ በተጭበረበሩ መታወቂያዎች የቁጠባ ሂሳቦችን በመክፈት፣ የማጭበርበር ድርጊቶች ተፈጽመው ያጋጥማል የሚሉት አቶ አማኑኤል፣ ባንኮች ይህንን ለማስቀረት የሚያገለግላቸው እንደ ዲጂታል ያለ መታወቂያ ባለመኖሩ መጭበርበሮችን መከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውን ያነሳሉ።
ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ መሰረት ይላሉ አቶ አቤኔዘር በመታወቂያ ማጭበርበር ብቻ በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች በአጠቃላይ ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር አጥተዋል።
ስለዚህ ዲጂታል መታወቂያን በባንኮች ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት መጠቀም ሲጀመር፣ እንዲህ ዓይነት መጭበርበሮችን ያስቀራል ማለት ነው ሲሉ ያለውን ጥቅም ያስረዳሉ።
ባንክ ላይ ብቻ ሳይሆን ትምህርት፣ ጤና፣ ኢሚግሬሽን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች ጋር ዲጂታል መታወቂያን ተጠቅሞ አገልግሎት ማግኘት እና ተመሳሳይ የሆነ ዳታ መያዝ እንዲቻል ያደርጋል ሲሉ ያብራራሉ።
በዲጂታል መታወቂያ ላይ ብሔር ይጠቀስ ይሆን?
ዲጂታል መታወቂያን በአገልግሎት መስጫ መስኮቶች ለመጠቀም በመሰረታዊነት የሚያስፈልጉ መረጃዎች በሙሉ ታሳቢ መሆናቸውን አቶ አቤኔዘር ይጠቅሳሉ።
አገልግሎት ለማግኘት የሚሄድ ማንኛውም ሰው ብሔሩ አይጠየቅም።
ሆኖም ስም፣ የትውልድ ቀን፣ ዜግነት እና ከመኖርያው አድራሻ በተጨማሪ የባዮሜትሪክስ ዳታ ብቻ እንደሚሰበሰብ ይናገራሉ።
የዲጂታል መታወቂያ ዋና አላማ መታወቂያውን የያዘው ግለሰብ እርሱ መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ስለሆነ በመታወቂያው ላይ ብሔር እንደማይካተት አረጋግጠዋል።
ከዚያ ውጪ ያሉ መረጃዎችን አገልግሎት ሰጪዎች የሚፈልጉ ከሆነ በራሳቸው መንገድ ጠይቀው ይመዘገባሉ ብለዋል።
ተጨማሪ የሆኑ መረጃዎች ካስፈለጉ አገልግሎት ሰጪው በማንኛውም ሰዓት ሊጠይቅ እና ሊያሟላ እንደሚችልም ይናገራሉ።
ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ሌላ ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ የግለሰቦች ዳታ ደህነንት ጉዳይ ነው።
የግለሰቦች ዳታ ወደ ሶስተኛ ወገን አይተላለፍም የሚሉት አቶ አቤኔዘር ፣ አገልግሎት ሰጪዎችም ቢሆኑ የግለሰቡን ማንነት ለመለየት ሲፈልጉ መታወቂያው ላይ ባለው ኪውአር ኮድ ተጠቅመው ወደ ብሔራዊ ዳታ ሰርቨር ገብተው እንደሚያገኙት ይናገራሉ።
ይህ ዲጂታል መታወቂያ መታደስ የማያስፈልገው ሲሆን፣ የስም ለውጥ ካለ ግን ሕጋዊ ማስረጃ በማምጣት ማስተካከል እንደሚቻል ኃላፊው ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ስማርት ስልኮችን አልያም ላፕቶፖችን ተጠቅመው id.et ወደተሰኘው ድረገጽ በመግባት ቅድመ ምዝገባ ማካሄድ እንደሚችሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ተመዝግበው ሲጨርሱ ባዮሜትሪክ ዳታ የሚሰጡበትን ቀነ ቀጠሮ ይሰጣቸዋል።
ከዚያም በአዲስ አበባ በአንድነት ፓርክ፣ በፖስታ ቤት ቅርንጫፎች፣ በተመረጡ የተለያዩ ባንኮች ቅርንጫፎች፣ በተመረጡ የገቢዎች ቢሮዎች መመዝገብ ይቻላል።
በክልሎች ከገቢዎች ቢሮው ጋር በመሆን ምዝገባ መጀመራቸውን አቶ አቤኔዘር ጨምረው ገልፀዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለማግኘት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ክፍያ አይጠየቅም።