በእንጦጦ ፓርክ እና አካባቢው በተደራጁ አካላት የሚፈጸም ዝርፊያ ተባብሷል ተባለ
(አዲስ ማለዳ) በእንጦጦ ፓርክ እና አካባቢው የተደራጁ አካላት በየጊዜው ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ እንዲሁም፤ ለመዝናናት ወደ ፓርኩ በሚያቀኑ ሰዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የደህንነት ስጋት መደቀናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተለይም ከልህቀት ማዕከል ወደ እንጦጦ ማርያም እና ወደ ሽሮ ሜዳ በሚወስደው በቅርቡ ተለዋጭ መንገድ ተብሎ ለተሽከርካሪ ክፍት በተደረገው መንገድ ላይ የተደራጁ ዘራፊዎች መኪና በማስቆም ጭምር የዝርፊያ ተግባር እንደሚፈጽሙ ነው የተገለጸው፡፡
አካባቢው በደን እና በእጽዋት የተሸፈነ መሆኑም ዝርፊያ ለሚፈጽሙ አካላት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተመላክቷል።
በመሆኑም በዚህ መንገድ በእግርም ሆነ በተሸከርካሪ ለማለፍ ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ስጋት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በአካባቢው አልፎ አልፎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የሚታዩ ቢሆንም ደርጊቱ መባባሱ ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የእግር ጉዞ እያደረገች በተንቀሳቃሽ ስልክ ስታወራ የነበረች አንዲት ሴትን ስልክ አንድ ግለሰብ ለመንጠቅ ሙከራ ማደረጉን እና ቦታው ገደላማ ስለነበር ተያይዘው ገደል ውስጥ መግባታቸውን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሰል ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የተጠቀሰ ሲሆን፤ ብዙዎች ወደ ሥፍራው ለማቅናት የደኅንነት ስጋት እንዳላባቸው መረዳት ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ጉዳዩ ለኮሚሽኑ እንግዳ እንደሆነ እና ሰምተው እንደማያውቁ ጠቅሰው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች የሚፈጸምባቸው ግልሰቦችም በአካባቢያቸው ለሚገኝ የፖሊስ ጽህፈት ቤት ባስቸኳይ እንዲያመለክቱም ኮማንደር ማርቆስ አሳስበዋል፡፡