July 21, 2023 

  • መንግሥት ለኢትዮጵያ ወደብ ለማስገኘት የሰላምና የኃይል አማራጮችን የመጠቀም ሐሳብ እንዳለው ጠ/ሚ ዐብይ ገለፁ
  • የኢትዮጵያ መንግሥት በወደብ ጉዳይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በድርድር ላይ ይገኛል

አምባ ዲጂታል፤  በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ ከባለሐብቶች እና ነጋዴዎች ጋር ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 13፣ 2015 ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትን በተመለከተ የወቅቱን የመንግሥታቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡

አምባ ዲጂታል በስብሰባው ከተሳተፉ ሦስት ሰዎች ማረጋገጥ እንደቻለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያለች የ120 ሚሊዮን ሕዝብ አገር ያለ ወደብ ልትኖር አትችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የወደብ ወጪ ከጂዲፒዋ 25 በመቶው በላይ እንደሚሆን ገልፀው ይህ ሊቀጥል እንደማይገባም ተናግረዋል።

ዐቢይ በዚሁ ማብራሪያቸው ወቅት አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩትለትን ወደብ ለማግኘት ኢትዮጵያ ሦስት የጎረቤት አገራት አማራጭ እንዳላት ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው ሦስት አገራት ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊላንድ ናቸው፡፡