በጠለምትና አካባቢው በትግርኛ ቋንቋ የሚጠሩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ስያሜ ወደ አማርኛ ሊቀየር መሆኑ ተሰማ
(አዲስ ማለዳ) በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙና በትግርኛ ቋንቋ የሚጠሩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ስያሜ ወደ አማርኛ ቋንቋ ሊቀየር መሆኑን አዲስ ማለዳ ከጠለምት አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰምታለች።
ኮሚቴው በጠለምትና አካባቢው የሚገኙና በትግርኛ ቋንቋ ስያሜ ያላቸው ኹሉም ወረዳዎች፤ ቀበሌዎችና ጎጦችን የአማርኛ ስያሜ ሊሰጣቸው መሆኑን አመላክቷል።
በወቅቱ ክልሎች ሲመሰረቱ አካባቢው ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለል በመደረጉ በአማርኛ ቋንቋ ይታወቅ የነበረው ስያሜያቸው ወደ ትግርኛ ቋንቋ እንዲቀየር ተደርጎ ቆይቷል ነው የተባለው።
ይህን ተከትሎም በአሁኑ ወቅት በጠለምትና አካባቢው የሚገኙ ወረዳዎችን፣ ቀበሌዎችንና ጎጦችን ስያሜ ለመቀየር እንቀስቃሴ መጀመሩን መረዳት ተችሏል።
ለአብነትም አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን ሐምሌ 01/2015 ያካሄደው የአዲርቃይ ወረዳ ምክር ቤት፤ “ሰላም በር” እና “ሰገነት” የተሰኙ ኹለት አማራጭ ስያሜዎችን ተቀብሎ በሕዝብ ምርጫ እንዲጸድቅ ወስኗል ነው የተባለው።
በተጨማሪም በወረዳው ሥር የሚገኙ ቀበሌዎች ስያሜ ለውጥ እንዲደረግ የተለያዩ ስያሜዎች ለምክር ቤቱ ቀርበው እንዲጸድቁም መወሰኑ ተጠቅሷል።
በማይጠብሪ ወረዳም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በጠለምት አካባቢ የሚገኙት እንደ ማይትክሊት፣ አዲወሰኔ፣ ጻዳቀርኒ የተባሉ ቀበሌዎች እንዲሁም አዶፋሪ፣ አዲናቴ፣ አዲሐሮሶን፣ ማይ ዳጉሳ፣ ማይ ቃጫ፣ ማይ ሎሚን የተባሉ ጎጦች የአማርኛ ቋንቋ ስያሜ ሊሰጣቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
የሥም ለውጥ የሚደረግባቸው ኹሉም ቦታዎች ሥም ዕቅድ ተዘጋጅቶ በጠለምት ሥር ለሚገኙ ወረዳዎች ምክር ቤት መሰራጨቱ እንዲሁም፤ ጉዳዩ በክልልና በዞን ደረጃም ተቀባይነት ማግኘቱ ነው የተገለጸው።
የቦታዎች ስያሜ ሲቀየር፤ የየመስሪያ ቤት ማህተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ላይ የስያሜ ለውጥ መደረጉም አይቀሬ ነው ተብሏል።
በእነዚህ አካባቢዎች ኹለቱም ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን፣ ቦታዎቹ በአማራ እና በትግራይ ክልል ሕዝብ ዘንድ በተለያዬ ስያሜ ሲጠሩ ይስተዋላል።