የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር “ክልሉን እንታደግ” ሲሉ ጥሪ አቀረቡ
(አዲስ ማለዳ) ባልተለመደ ሁኔታ በላለፉት ሦስት ቀናት በዝግ የተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት፤ በክልሉ ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከአባላቱ ጠንካራ ጥያቄዎችን ማስተናገዱ ተሰምቷል፡፡
በምክር ቤቱ ሰብሰባ ላይ ጥያቄ ያነሱት የሕዝብ ተወካዮች፤ “የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት ቀን ከሌሊት የሚሰሩ አካላት አሉ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አባላቱ ክልሉ አሁን ላይ የገጠመውን አለመረጋጋት ለመፍታት መጀመሪያ የክልሉ አስተዳደር መዋቅር ራሱን መፈተሸና ማስተካከል አለበትም ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ አባላት አክለውም፤ “ክልሉ ያሉበትን መዋቅራዊ ችግሮች ካላስተካከለና ራሱን አስተካክሎ በግልጽ ካላወጣ፣ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አይቻልም” ሲሉ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በየአካባቢው የሚስተዋሉ ውጊያዎች የክልሉን ሕዝብ እያዳከሙ ነው ያሉት አባላቱ፤ የክልሉ መንግሥት መከላከያ ሠራዊት አስገብቶ ውጊያ እንዲደረግ መፍቀድ አልነበረበትም የሚል ትችትም አንስተዋል።
ከምክር ቤት በአባላቱ ጠንካራ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡትም ምላሽ፤ “ክልሉን እንታደግ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ችግራችንን በራሳችን የመፍታት አቅም እንፍጠር” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በየዞኑ ከምክር ቤት አባላት አምስት አምስት ሰው ተመርጦ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የተሳተፉበት ውይይት ያለምንም ገደብ እንዲደረግም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ ያቀረቡት የውይይት ጥሪ በአስር ቀናት ውስጥ እንዲካሄድም ነው የጠየቁት። በውይይቱ የሚነሱ ጉዳዮች በወረዳ፣ በዞንና በክልል በየደረጃው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥረት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
አስተዳደራቸው ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ በመሰጠት፤ በሽዋ፣ በወሎ፣ በጎጃምና በጎንደር ውይይት እንዲደረግ ዕድል መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ “እንታደገው” ያሉትና የሚመሩት ክልል፤ በተለይ የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከተሰማራ ጊዜ ጀምሮ በውጊያ፣ መንገድ በመዝጋት፣ በሕዝብ ተቃውሞና በመሳሰሉት ሁነቶች ውስጥ እያለፈ ነው፡፡
የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከአማራ ክልል የሰላም እጦት ጋር በተያየዘ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፤ “ክልሉ ፓራላይዝድ ሆኗል” ሲሉ መደመጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፊልድ ማርሻሉ የአማራ ክልል አስተዳደር ሽባ ሆኗል የሚል ይዘት ያለው አስተያየት ከሰጡ በኋላ፤ የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ውስጥ ገብቷል፡፡
በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ያለው ግጭት፤ ገና ከጅምሩ በውይይትና በድርድር እንዲፈታ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጥሪ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው፡፡