- ከጉጂ ወደ ነጌሌ ቦረና በሚወስደው መንገድ ላይ በተነሳው አመጽ መንገድ መዘጋቱ ተገለጸ
- በመንገዱ እስካሁን ከስምንት በላይ ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸው ተነግሯል

(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ከጉጂ ዞን ወደ ነጌሌ ቦረና በሚወስደው መንገድ ከአዲሱ የምስራቅ ቦረና ዞን አደረጃጀት ጋር ተያይዞ በቀጠለው አመጽ ምክንያት መንገድ መዘጋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
በዚህም ምክንያት ተሸከርካሪዎች በዚያ መንገድ እንደማያልፉ እና ወደ ነጌሌ ቦረና ከተማ ለመግባት በባሌ ወይም በሞያሌ በኩል ያለውን መንገድ መጠቀም ግድ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡
መንገዱ ከተዘጋ በኋላ በዚያ በኩል ለማለፍ ሙከራ የሚያደርጉ ተሸከርካሪዎችን ማቃጠል እና ማውደምም ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ መምጣቱን በመጠቆም፤ እስካሁን ከስምንት ተሸከርካሪዎች በላይ መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ሐምሌ 2 እና ሐምሌ 8 ቀን 2015 መቃጠላቸውንም ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡
“መንገዱን የሚዘጉት ያልታወቁና ከሌላ ወገን የተለየ ተልዕኮ የተሰጣቸው ኃይሎች ይመስላሉ” ያሉት ነዋሪዎች፤ ሌሊት መንገዱን ዘግተው ካደሩ በኋላ በጸጥታ አካላት ጠዋት ላይ እንደሚከፈት ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪዎችም ካለው ስጋት አንጻር መንገዱን መጠቀም ካቆሙ ሳምንታት መቆጠራቸውን በማስረዳት፤ “በተለይም በሦስት ቀናት ወዲህ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡
የመንግሥት የሥራ አመራሮችም በጸጥታ ኃይሎች እጀባ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱም አውስተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ ዋደራ፣ ጎሮዶላ እንዲሁም ሀረርፈማ የመሳሰሉ ወረዳች ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ስጋ ውስጥ መግባታቸውን እና በዚሁ ምክንያት የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸውን ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው መንግሥት ነዋሪውን ስለ ጉዳዩ ያወያያል እየተባለ ብዙ ጊዜ ቢወራም፤ እስካሁን ከአዲሱ የምስራቅ ቦረና ዞን አደረጃጀት ጋር ተያይዞ በቂ መረጃ ተሰጥቶ አያውቅም በማት አስረድተዋል፡፡
አዲስ ማለዳም በጉዳይ ዙሪያ ለምስራቅ ቦረና ዞን የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ መሳይ ጥበቡ የደወለች ሲሆን፤ “በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በጎሮ ዶላ ኪሊዌ በተባለች ቦታ ተሸከርካሪዎች እየተቃጠሉ መሆናቸው እውነት ነው።” በማለት፤ ወንጀሉ በማን እየተፈጸመ እንደሆነ እየተጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሰዓት መንገዱ የተከፈተ ሲሆን፤ ሰዎች ካላቸው የደኅንነት ስጋት የተነሳ አማራጭ መንገድ ሊጠቀሙ ይችላሉ ካሉ በኋላ፤ “ዞናችን በአካባቢው ካሉ የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመሆን በስፍራው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሰራ ነው።” ብለዋል፡፡
ዞኑን እንደአዲስ ማዋቀር የተፈለገው ሕዝቡ ያለውን የመልካም አስተዳደር፣ የምጣኔ ሀብት እና አገልግሎቶችን በቅርበት የማግኘት ጥያቄ ማዕከል በማድረግ ነው ያሉም ሲሆን፤ “ይሄም የሕዝባችንን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንዲረዳ ነው።” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዞኑን አዲስ አደረጃጀት የሚቃወሙ ጥቂት ግለሰቦች ከመንግሥት አካላት ጭምር መኖራቸውን በመግለጽ፤ የሕዝብ ጥያቄ አስመስሎ ማቅረብ ግን ፍጹም ስህተት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በቀጣይ በየደረጃው ካሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ለማድረግ መድረክ እያዘጋጀን ነው ያሉት ኃላፊው፤ የአዲሱን ዞን አደረጃጀት ጥቅም የምናስረዳበት ይሆናልም ብለዋል፡፡