
ከ 8 ሰአት በፊት
ለአራት ዓመት ያህል በኦሃዮ መካነ አራዊት ውስጥ ወንድ መሆኑ ይታወቅ የነበረ ጎሬላ ልጅ ወልዶ ሠራተኞቹን አስገርሟል።
ኮለምበስ በተሰኘ መካነ አራዊት እኤአ ከ2019 ጀምሮ ትኖር የነበረችው ሳሊ፣ ሐሙስ እለት ልጇን ታቅፋ ተገኝታለች።
የመካነ አራዊቱ ሰራተኞች የጎሬላዋ ልጅ “በመልካም ጤንነት ላይ” እነደምትገኝ በብሎጋቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህ ወንድ ነው ተብሎ የታመነችው ጎሬላ፣ ስሟ ሳሊ ሲሆን ልጇንም በጥሩ ሁኔታ እነየተንከባከበች መሆኑ ተገልጿል።
ሳሊ ከዚህ በፊትም በመልካም ጤንነት ላይ የነበረች ሲሆን አሁን የጾታ መደበላለቁን ተከትሎ ምንም ዓይነት የሕክምና ምርመራ አያስፈልጋትም ተብሏል።
“ያልተጠበቀ ነው። ይሁንና ለተንከባካቢዎቿ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። ደህንነታቸው አደጋ ላይ ለወደቀ እንስሳት ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ የመካነ አራዊቱ ተንከባካቢዎች በብሎጋቸው ላይ አስፍረዋል።
የመካነ አራዊቱ ተንከባካቢዎች “ወንድ ጎሬላ” ልጇን ስታጠባ እስኪያዩ ድረስ ምንም የጠረጠሩት ነገር አልነበረም።
“የወጣት ጎሬላዎችን ጾታ መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል ስለሁኔታው ሲያስረዱ።
በስምንት ዓመቷ ሳሊ ለአካለ መጠን የደረሰች ቢሆንም ጾታዋን ለመለየት ግን አዳጋች ነበር ሲሉ ያክላሉ።
“እስከ ስምንት ዓመታቸው ድረስ ወንዶች እና ሴቶች ተመሳሳይ ቁመት ነው ያላቸው። ጎልቶ የሚወጣ የመራብያ አካልም የላቸውም። ወንዶችም አስራ ሁለት እና ከዚያ በላይ እስኪሆናቸው ድረስ ጀርባቸው ላይ ያለውን አብረቅራቂ ምልክት ጎልቶ አይወጣም”
ጎሬላዎች ሆዳቸው ትልቅ በመሆኑ የተነሳ እርጉዝ በሚሆኑበት ወቅት አያስታውቁም።
ጨቅላ ጎሬላዎች ደግሞ ገና ከሚወለድ የሰው ልጅም እጅጉን ያነሱ ናቸው።
“አዲስ በተጨመረው የቤተሰብ አባል እጅግ በጣም ደስተኞች ነን” ብለዋል የመካነ አራዊቱ ባልደረቦች።
“በኮለምበስ መካነ አራዊት ከ1956 ጀምሮ ከተወለዱ ጎሬላዎች ጋር ሲቆጠር 34ኛዋ ናት ማለት ነው። እነዚህን አስደናቂ አንስሳት በመጠበቅ ስራ ውስጥ እጅግ በጣም ወሳኟ አካል ናት”
መካነ አራዊቱ የሳሊን ልጅ አባት ለመለየት የዘረ መል ፍተሻ አካሂዳለሁ ብሏል።
ሳሊ የምትኖረው የ39 ዓመቱ ማክ በሚመራው ቡድን ውስጥ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ ደግሞ የ10 ዓመቱ ካሞሊ እና የስድስት ዓመቱ ጄጄም ይገኛሉ።
ምንም እንኳ የሳሊን ጾታ መለየት ያቃታቸው የመካነ አራዊቱ ሠራተኞች በሁኔታው ቢደነቁም የሳሊን ልጅ ጾታ ግን እርግጡን መናገር አንችላለን እያሉ ነው።
“ሴት ናት! ቡድናችን ፎቶዎችን አንስቶ በሌላ የመካነ አራዊት ውስጥ ለሚገኝ የእንስሳት ባለሙያ በመላክ ጭምር አረጋግጧል” ብለዋል።