የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ከ 7 ሰአት በፊት

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰነድን በአግባቡ ባለመያዝ በሚቀጥለው ዓመት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተወሰነ።

ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር እንዲታይ ወስኗል።

እርሳቸው ግን የፍርድ ቤት ጉዳያቸው ከ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ እንዲደረግ ሃሳብ አቅርበዋል። ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ከምርጫ በፊት መታየት እንዳለበት ተከራክሯል።

የ77 ዓመቱ ትራምፕ የመንግሥት ወሳኝ መረጃዎችን ፍሎሪዳ በሚገኘው ቤታቸው ደብቀዋል የሚል ጠንካራ ክስ ቀርቦባቸዋል።

የዓቃቤ ሕግ መከራከሪያ እንደሚለው ትራምፕ እነዚህን ሚስጥራዊ ሰነዶች በግል ቤታቸው ውስጥ በመደበቅ እንዲሁም፣ መንግሥት ሰነዶቹን እንዳያገኝ ሁኔታውን አወሳስበውበታል ብሏል።

ትራምፕ ግን ይህ የሚደረገው እርሳቸውን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር ለማስተጓጎል እንጅ የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ አስተባብለዋል።

ትናንት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ትራምፕ በሰጡት መግለጫ የፍርድ ሂደቱ እንዲታይ የተወሰነበት ቀን የእኔን የፕሬዝዳንትነት ውድድር “መስቀለኛ መንገድ ላይ የሚያስቀምጥ ነው” ብለውታል።

ይህንንም ከሕግ ቡድናቸው ጋር ሆነው እንደሚሞግቱ ተናግረዋል።

በትራምፕ ጉዳይ ላይ የተሾሙት ዳኛ ካኖን የትራምፕ ጉዳይ የሚታይበት ቦታ ፍሎሪዳ ፎርት ፒርስ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች ትራምፕ በ2020 ምርጫ ካሸነፉባቸው በርካታ ግዛቶች እንደሚውጣጡ ተገልጿል።

በሁለቱም ወገን በኩል የሚገኙ የሕግ ሙያተኞች የፍርድ ሂደቱ መቼ መካሄድ እንዳለበት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ተከራክረዋል።

ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩ የተወሳሰበ ባለመሆኑ ረጅም ጊዜ መውሰድ ሳያስፈልግ በአጭር ጊዜ የፍርድ ሂደቱ ይከናወን ብሏል።

በሚቀጥለው ታኅሣስ ወር እንዲጀመርም ይፈልጋል።

በሌላ በኩል የትራምፕ የሕግ ጠበቃዎች ከጉዳዩ የተለየ መሆን ጋር ተያይዞ ዘለግ ያለ ጊዜ ያስፈልገዋል ብለዋል። ጉዳዩ በአጭር ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ደንበኛቸው በ2024 በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርቻ ውድድር ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ አይኖራቸውም።

ቅድመ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ጋር የሚፋጠጡት ዶናልድ ትራምፕ ይሆናሉ።

ይህ ክስ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከተመሰረቱ በርካታ ክሶች አንደኛው ነው።

ባለፈው ሚያዚያ ኒው ዮርክ ውስጥ የቢዝነስ መረጃን በማሳሳት ተከሰው ነበር። ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት እንዳስታወቁት ደግሞ ከ2 ዓመት በፊት በካፒቶል ሂል በተደረገው ረብሻ እና የ2020 ምርጫን በመቃወማቸው ምክንያት በፌደራል መንግሥት ጥያቄ መሰረት በቅርቡ ለእስራት እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።

የአትላንታ እና የጆርጂያ ግዛት ጠበቆችም ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የምርጫ ውጤት ሲሰረዝ ትራምፕ ከጀርባ ስለመኖራቸው ምርመራ ጀምረዋል።

የፍትህ መስሪያ ቤቱ የካፒቶል ሂልንና የማር አ ላጎ ጉዳዮችን እንዲከታተል በጃክ ስሚዝ የሚመራ ልዩ ካውንስል አቋቁሟል።

ባለፈው ወር የከሰሷቸው ዓቃቢ ሕጎች ትራምፕ ከቢሮ ሲለቁ 300 የተከፋፈሉ ሰነዶችን ባህር ዳርቻ ወደሚገኘው ቤታቸው ወስደዋል። ከወሰዱ በኋላም እነዚህን በጥብቅ የሚፈለጉ ሰነዶችን መጸዳጃ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ስውር ቦታዎች ደብቀዋቸዋል።

አቃቤ ሕግ ጨምሮም የፌደራል መርማሪ ቡድን ወደ ስፍራው ከማምራቱ በፊት ረዳታቸው ዋልት ናውታ ሰነዶቹን እንዲያሸሹ ነግረዋቸዋል በሚልም ከሷቸዋል። የግል ረዳታቸውም ክስ ተመስርቶባቸው የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ግን ነጻ ነኝ ብለዋል።

ኒው ዮርክ ውስጥ ታዋቂዋን የወሲብ ፊልም ተሳታፊ ስቶርሚ ዳኔልስን ዝም ለማሰኘት ገንዘብ ከፍለዋል በሚልም ክስ ቀርቦባቸው ነበር። በዚሁ ጉዳይ ላይ ደዶናልድ ትራምፕ መጋቢት 25/2024 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።