
ከ 4 ሰአት በፊት
የጋና ውሃ ሀብት እና ፍሳሽ ሚኒስቴር፣ ሲሲሊያ ዳፓ፣ ሁለት የቤት ሠራተኞች ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ በመስረቅ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የቤት ሠራተኞቹ በርካታ ሚሊየን የጋና ቼዲ የተገመተውን ገንዘብ (ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ) የሰረቁት አክራ ከሚገኘው የሚኒስቴሯ መኖርያ ቤት ነው ተብሏል።
የጋና አገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እድሜያቸው 18 እና 30 መሆናቸውን የተነገረላቸው የቤት ሠራተኞች ከሚኒስትሯ ገንዘብ እና ሌሎች ውድ እቃዎችን የሰረቁት ባለፈው ዓመት መሆኑን ዘግበዋል።
ሁለቱ የቤት ሠራተኞች ወንጀል ለመፈጸም በማሴር እና በስርቆት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ሌሎች ሶስት ግለሰቦች ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገልጿል።
በአክራ የሚገኘው ፍርድ ቤት ከተከሳሾቹ መካከል አንዷ የምታጠባ እናት ስለሆነች የዋስትና መብቷ እንዲጠበቅ የፈቀደ ሲሆን ቀሪዎቹ አራቱ ግን በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል።
ጋናውያን ይህንን ዜና ከሰሙ በኋላ ሚኒስትሯ ይህን ያህል በርካታ ገንዘብ እንዴት በመኖርያ ቤታቸው ሊቀመጥ ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል።
በጋና ዋነኛ ተቃዋሚ የሆኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆን ማሀማ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ “ገራሚ ነገር” ሲሉ ተሳልቀዋል።
“ይህ ወንጀል እውነት ተፈጽሞ ቢሆን እንኳ ስለምን ይህን ያህል መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ ቤት ውስጥ ማስቀምጥ አስፈለገ? ፕሬዝዳንት አኩፎ አዶ በስራቸው ላሉ የሕዝብ አገልጋዮች መልካም ምሳሌ መሆን ይችሉ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የሕዝብ እንደራሴዎችም የተባለው እውነት ከሆነ ሚኒስትሯ ከሥልጣን ተነስተው የገንዘቡ ምንጭ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ሚኒስትሯ እስካሁን ድረስ ያሉት ነገር የለም።
እኤአ በ2013 የጋና ኮሙኑኬሽን ምክትል ሚኒስትር የነበሩት፣ ቪክቶሪያ ሐማ፣ 1ሚሊዮን ዶላር እስኪያካብቱ ድረስ ስልጣን ላይ እንደሚቆዩ የገለፁበት የዽምጽ ቅጂ በመገኘቱ ከስልጣን እንዲነሱ ተደርጎ ነበር።
በወቅቱ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ታሪክ የእርሳቸውን ስም ለማጠልሸት በተቀናቃኞቻቸው የተፈበረከ መሆኑን በመግለጽ ተከተራክረዋል።