
ከ 9 ሰአት በፊት
በኢትዮጵያ በዩኒቨርስቲዎች የመውጪያ ፈተና ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ጀምሮ ከተሰጠ በኋላ ለመውጫ ፈተናው ከተቀመጡት 61ሺ 54 ተማሪዎች 40.65 በመቶ የማለፊያውን ነጥብ ማስመዝገባቸውን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል።
62.37 በመቶ የመንግሥት ተቋማትና 17. 2 በመቶ የግል ተቋማት ተማሪዎች የማለፊያውን 50 በመቶና ከዛም በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ቢቢሲ በጉዳዮ ላይ ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ኃላፊ ይህ ውጤት አስደንጋጭ አይደለም ይላሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኤባ ሚጀና ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰጠው የዩኒቨርስቲዎች የመውጫ ፈተና ውጤቱ በአንጻራዊነት ሲታይ የተሻለ ሆኖ ታይቶናል ብለዋል።
“እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ይህ ነጥብ በጣም ያስደነገጠን አይደለም።”
ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጂ በአገሪቷ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ለምርቃት ለደረሱ ተማሪዎች ሁሉ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰጠው የመውጫ ፈተና ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ ለዚህ ፈተና በቂ ዝግጅት አልተደረገም በማለት ይከራከራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስርዓተ ትምህርት ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ፍርዲሳ ጀቤሳ፣ የትምህርት ጥራት የሚመጣው በደንብ በማስተማር እንጂ ለምረቃ የደረሱ ተማሪዎችን ፈተና በመስጠት አይደለም ይላሉ።
ዶ/ር ፍርዲሳ መጀመርያ ትምህርት ሚኒስቴሩ ምክር እንዲሰጡት እንደ እርሳቸው ያሉ ስለ ስርዓተ ትምህርት ያጠኑ ባለሙያዎችን ቢጋብዝም በኋላ ግን ምክንያቱን ባላወቁት መንገድ ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ይናገራሉ።
አሁንም ቢሆን ተማሪዎችን ከስር ጀምሮ ብቁ እያደረጉ ካላመጡ በስተቀር ድንገት ተነስቶ ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ ስኬት አይገኝም ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያገኙት 40 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹን ተከትሎ ከተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎች ቅሬታዎች ይሰማሉ።
ዶ/ር ኤባ ሚጀና ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ምላሽ ሲሰጡ ይህ የተማሪ ብቃት ምዘና ፈተና የመውጫ ፈተና በሚል አሁን ቢጀመርም ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ፈተና ነበር በማለት ተማሪ መቼውንም ቢሆን ዝግጁ መሆን አንዳለበት ያስገነዝባሉ።
“ እንደዚህ ዓይነቱ አገራዊ ፈተና በስምንተኛ፣ በ10ኛ እና በ12ኛ ክፍሎች ላይ አለ። በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም።”
- በኢትዮጵያ ሕጋዊ ነዋሪ ለሆኑ ሁሉ ይሰጣል የተባለው ዲጂታል መታወቂያ ምንድን ነው?21 ሀምሌ 2023
- 51 ኮርሶችን A+ ያመጣው ተማሪ21 ሀምሌ 2023
- ጃፓን ላይ የወረደው አቶሚክ ቦምብ ፈጣሪ፤ ሮበርት ኦፕንሃይመር ማን ነው?21 ሀምሌ 2023
‘ፈተና እየሸሹ ዲግሪ መፈለግ ይቃረናል’
የትምህርት ሚኒስትር ኃላፊው አክለውም “ዝግጅት የለም እያሉ ዲግሪ ለመውሰድ መዘጋጀት የሚቃረኑ ነገሮች ናቸው” ሲሉ የቅሬታ አቅራቢዎቹን ሀሳብ ይሞግታሉ።
“ዝግጅት የለም ማለት የመውጫ ፈተና ያስፈራል ማለት ነው። እኛ የምንሰጠው ዲግሪም የውሸት መሆኑን ያሳያል። በአንድ በኩል ተማሪዎችን አብቅተናል ብለን ዲግሪ ለመስጠት እየተዘጋጀን በሌላ በኩል ደግሞ ዝግጅት ስለሌለ ፈተና መሰጠት የለበትም ሲባል ይህ የመከራከሪያ ነጥብ መሆን የሌለበት ነው። እንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው የትምህርት ጥራትን ጎድተው የትምህርት ዘርፉን የሚያቀጭጩት” ይላሉ ዶ/ር ኤባ።
ይህንን ፈተና አስተማሪዎች ራሳቸው ተማሪዎቻቸው ሲማሩ ከከረሙት ያወጣሉ የተለየ አይደለም በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊው።
እንደዚህ ዓይነት ፈተና ከዚህም በፊት እንደ ሕግ እና ጤና ትምህርት ክፍሎች ውስጥ ሲሰጥ የነበረ መሆኑን በማንሳት ሙሉ በሙሉ አዲስ አይደለም ይላሉ።
የስርዓተ ትምህረት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ፍርዲሳ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ዪኒቨርስቲዎች ባላቸው የትምህርት ግብዓት እና መምህራን እኩል ስላልሆኑ ተመሳሳይ ብቃት የሌላቸው ተማሪዎች ተፈጥረዋል ይላሉ።
በዚህም የተነሳ ተማሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ የሆነ ፈተና መፈተን አያስችላቸውም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
“በዩኒቨርስቲዎች መካከል ልዩነት መኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለምም ያለ ነው። የተማሪ ብቃት እዚያ ባለው አስተማሪ እና አመራር ይወሰናል” የሚሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊው ዶ/ር ኤባ ናቸው።
አክለውም ዩኒቨርስቲዎች ዲግሪ ለመስጠት እስከተዘጋጁ ድረስ የውጫ ፈተና ለመስጠት ደግሞ እንዴት ሳይዘጋጁ ይቀራሉ ሲሉ ይጠይቃሉ።
ይህንን የውጫ ፈተና አስመልክቶ የሚነሳው ቅሬታ እና ክርክር በጥናት የተደገፈ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ኤባ “ለውጥን መቀበል አለመፈለግ ነው እንጂ ሌላ መሰረት የለውም” ሲሉ አጣጥለውታል።
ዶ/ር ኤባ አክለውም “የሌላው ዓለም ዩኒቨርስቲዎች እንደዚህ ዓይነት ፈተና ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ ሁኔታ ነው የሚሰጡት። እኛ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይሆን በምናስተምርበት የትምህርት ተቋም ደረጃ ላይ እንኳ ተመስርተን እንስጥ ብለን ነው የተነሳነው” ይላሉ።
“ለወደፊት ዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የሚስማማ ፈተና ሰጥተን ልጆቻችን በዓለም ደረጃ እንዲወዳደሩ ማዘጋጀት እንፈልጋለን” ሲሉ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን እቅድ ተናግረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ፈተና እንዲሰጥ ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፉን የሚናገሩት ዶ/ር ኤባ፣ ወደፊት ጊዜው ሲደርስ ከመጨናነቅ አስቀድመን የፈተና ባንክ አዘጋጅተን ልንሄድበት እንደሚገባ አሳይቶናል ይላሉ።
ከዚህም ውጪ ይህንን አሁን ያለውን ስርዓተ ትምህርት ተመልሰን ማየት እንዳለብን፣ የአስተማሪዎች ስልጠና እና በፈተና አስተዳደር ላይም መስራት እንዳለባቸው ፈተናው እንዳሳያቸው ይገልጻሉ።
“ከዚህ ተምረን ለወደፊት ከዚህ በበለጠ የሚያረካ ነገር እንሰራለን የሚል ተስፋ አለኝ።”
የወደቁት ተማሪዎች እጣ ፈንታ
በዚህ ፈተና የወደቀ ተማሪ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል? ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ያገኛሉ? የሚሉ ጥያቄዎች በተማሪዎች እና በወላጆቻቸው በስፋት ይነሳል።
በዚህ ጥያቄ ላይ ዶ/ር ኤባ “አንድ ተማሪ በአንድ ጊዜ ሳይሳካለት ከቀረ እስከሚፈልገው ድረስ ደጋግሞ መፈተን ይችላል። ባለቤቱ እንደ እቅዱ ጊዜ ወስዶ ፈተናውን ደጋግሞ መውሰድ ይችላል” ብለዋል።
ፈተና የወደቁት ተማሪዎች ይመረቃሉ ወይስ አይመረቁም የሚለው ጉዳይ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ አላስቀመጠም የሚሉት ዶ/ር ኤባ “ስለ ምርቃት ዩኒቨርስቲው ነው በሴኔት የሚወስነው። ትምህርት ሚኒስቴር በምርቃት ላይ መመሪያ አላወጣም” ይላሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ፈተና የወደቁ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ከተመለሱ ከስድስት ወር በኋላ ተመልሰው መፈተን ይችላሉ እእደሚልም ጨምረው ተናግረዋል።
ነገር ግን የት እና እንዴት ይህንን ፈተና መውሰድ ይችላሉ ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው “በዚህ ጉዳይ ገና በእቅድ ደረጃ ላይ ነው። በኦንላየን መውሰድ እንዲችሉ ሲስተም እየፈጠርን ነው። በኦንላየን ፎርም ሞልተው በአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርስቲ እንዲፈተኑ እናደርጋለን።”
ዶ/ር ፍርዲሳ ጀቤሳ፣ ተማሪዎቹ የማይጠበቅባቸውን ፈተና ደጋግሞ መፈተን የተማሪዎችን ጊዜ ያባክናል፣ የመንግሥትን በጀት ይበላል በማለት አሁንም በአስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
ይህንን አስመልክቶ ዶ/ር ኤባ፣ “ይህንን ፈተና ያለፉት ዲግሪያቸውን ይወስዳሉ። ይወዳደራሉ። ያላለፈ ደግሞ ዲግሪውን ስላላገኘ መወዳዳር አይችልም። የትምህርት ማስረጃ ላለፉት ብቻ ይሰጣል።” ሲሉ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።