ወንጀሉ የተፈፀመበት ሥፍራ

ከ 7 ሰአት በፊት

ከመሸታ ቤት ተባረርኩ በሚል ምክንያት አንድ መጠጥ ቤት አቃጥሎ 11 ሰዎች ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ሜክሲኮ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ጥቃቱ የደረሰው ባለፈው አርብ ምሽት ከአሜሪካ በምትዋሰነው ሳን ሉዊዝ ሪዮ ኮሎራዶ ነው።

መሸታ ቤቱ ከአሜሪካ ድንበር ጥቂት ሜትሮች ርቆ ይገኛል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ሰካራሙ ወጣት ከመሸታ ቤት ሲባረር ሞሎቶቭ ኮክቴል የተባለ ፈሳሽ ወርውሯል።

ሞሎቶቭ ኮክቴል ውስጥ ተቀጣጣይ ፈሳሽ ያዘለ ጫፉ እሣት የያዘ ጠርሙስ ነው።

ተጠርጣሪው ከመጠት ቤቱ ከመባረሩ በፊት ሴቶችን ይጎነትል እንደነበርም ተዘግቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ባለፈው ቅዳሜ በትዊተር ገፃቸው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉን ቢገልጹም ስሙን ግን አልጠቀሱም።

ግለሰቡ የቀሰቀሰው እሣት በፈጠረው አደጋ ምክንያት ሰባት ወንዶችና አራት ሴቶች ሞተዋል።

ሌሎች ሰዎች ደግሞ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸውን የሴኖራ ግዛት አቃቤ ሕግ ቢሮ ገልጧል።

በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ድንበር ተሻግሮ ከሚገኝ የአሜሪካ ሆስፒታል ገብተዋል።

“በርካታ የዓይን እማኞች እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ወጣት ግለሰብ ሴቶችን ሲጎነትል ስለነበር ከመሸታ ቤቱ እንዲባረር ተደርጓል” ይላል የአቃቤ ሕግ ቢሮ መግለጫ።

የዓይን እማኞቹ ጨምረው ግለሰቡ ወደ መሸታ ቤቱ የወረወረው “ሞሎቶቭ ኮክቴል የመሰለ ነገር” መሆኑን ተናግረዋል።

“በሴኖራ ግዛት ማንም ከሕግ በላይ አይደለም” የሚለው መግለጫ፤ ምርመራ መቀጠሉን ጠቅሶ “ፍትሕ ይወርዳል” ብሏል።

ግለሰቡ የፈፀመው ድርጊት ከተደራጀ ወንጀል ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እስካሁን ግልጥ አይደለም።

የአሜሪካ ጎረቤት በሆነችው ሜክሲኮ ለዓመታት በተደራጀ ወንጀል ስታተመስ ኖራለች።