ሮኔክስ ኪፕሩቶ
የምስሉ መግለጫ,ሮኔክስ ኪፕሩቶ በ2022 የኒው ዮርክ ግማሽ ማራቶን ቢያሸንፍም በአበረታች መድኃኒት ተጠርጥሮ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ግንቦት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ክብረ-ወሰን ባለቤቱ ሮኔክስ ሌላኛው ትልቅ ስም ያለው አበረታች መድኃኒት በመውሰድ የተጠረጠረ ኬንያዊ አትሌት ሆኖ ተገኝቷል።

የ23 ዓመቱ ተስፋ የሚጣልበት አትሌት ምርመራው ተጠናቆ ጥፋተና ሆኖ ከተገኘ ስማቸው ከጠለሸ ኬንያዊያን አትሌቶች መዝገብ ሊመደብ ግድ ይላል።

የቀድሞው የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤቱ ዊልሰን ኪፕሳንግ፣ የግማሽ ማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት የነበረው አብራሃም ኪፕቱም፣ የሪዮ ኦሊምፒክስ ማራቶን አሸናፊዋ ጀሚማ ሱምጎንግ፣ የለንደን ማራቶን አሸናፊው ዳንዔል ዋንጂሩ ከታገዱ መካከል ናቸው።

በተጨማሪም ሶስት ጊዜ የ1500 ሜትር አሸናፊው አዝቤል ኪፕሮፕና ምትኩ ኤላይጃህ ማንጋጎይ በቅርብ ዓመታት ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

ቅጣት ከተላለፈባቸው አትሌቶች በተጨማሪ በአበረታች መድኃኒት የሚጠረጠሩ ኬንያዊያን አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

ይህን ጉዳይ እንዲያጣራና ቁጥጥር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተሰጠው ግለሰብ ተስፋ ቢኖርም ሁኔታው አስፈሪ ነው ይላል።

“ሁሉም ሰው ተዘጋጅቶ ሊጠብቅ ይገባል። ምክንያቱም በአበረታች መድኃኒት ጉዳይ የሚጠረጠሩ ኬንያዊያን ቁጥር በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ዓመታት ይጨምራል” ይላል ብሬት ክሎዚዬ።

ብሬት የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ኃላፊ ነው። ይህ መሥሪያ ቤት የአበረታች መድኃኒትን ጉዳይ እንዲያጣረ የተቋቋመ ገለልተኛ ተቋም ነው።

“ለሁሉም የምለው ነገር አለኝ። «አይግረማችሁ። አትደንግጡ።» ይህንን ክስተት አሁኑን ካልቋጨነው ወደፊት አደጋ ነው።”

እጅግ ድንቅና ያልተነካ የአትሌቲክስ ተሰጥዖ ባለባት ሃገረ ኬንያ አበረታች መድኃኒት ሰተት ብሎ ገብቷል። ለዚህ ነው ሰውየው ቁጥሩ ቢጨምር እንጂ አይቀንስም የሚለው።

ከአራት ዓመታት በፊት ብሬት በቻይናዋ ላንዡ ከተማ አንድ ስብሰባ ከሚካሄድበት ክፍል ውስጥ ቆሞ ትንታኔ ይሰጣል።

አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች የጎዳና አትሌቲክስ ኢንዱስትሪው መሪ ተዋንያን ናቸው።

ጉዳዩ አንገብጋቢ መሆኑን የተረዳው ብሬት በያዘው ሪሞት ኮንትሮል አንድ ፅሑፍ ስክሪኑ ላይ ደገነ።

ፅሑፉ፤ ባለው ዓመት በጎዳና ላይ ሩጫ ማለትም እነ ቦስተን፣ ለንደን፣ ኒው ዮርክ፣ በርሊን እና ቶኪዮ ማራቶኖች ላይ ካሸነፉ አትሌቶች መካከል 76 በመቶው አልተመረመሩም ይላል።

እንደውም በእነዚህ ውድድሮች ድል ቀንቷቸው አንገታቸውን ዝቅ አድርገው ሜዳሊያ ከተቀበሉ ሴትና ወንድ አትሌቶች መካከል ግማሽ ያህል ምርመራ ይጠብቃቸዋል።

በእኒህ ረብጣ ብር የሚያስገኙ የጎዳና ሩጫዎች 80 በመቶው አሸናፊዎች ከረዥም ርቀት ሩጫ ቁንጮዎቹ ኢትዮጵያና ኬንያ የመጡ ናቸው።

የብሬት መልዕክት ግልፅ ነው። አዳራሽ ውስጥ የተገኙት የኢንዱስትሪው መሪዎች አበረታች መድኃኒትን መቆጣጠር ካሻቸው ገንዘብ አውጥተው ምርመራ ማድረግ አለባቸው ነው።

“እያየን ያለነው ይሄ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ኬንያዊያን አትሌቶች ጥሩ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ አበረታች መድኃኒት እየወሰዱ ነው።”

ቱባ ሯጮች ካሏት ጎረቤቷ ኢትዮጵያ በበለጠ በርካታ የረዥም ርቀት ሯጮች የምታመርተው ኬንያ ለአበረታች መድኃኒት ከተጋለጠች ቆየች።

በምጣኔ ሃብት እርከን ከዓለም 147ኛ የሆነችው ኬንያ ሯጮች በተለያየ መንገድ አሸንፈው ሕይወታቸውን ለመቀየር የሚሹባት ሆናለች።

የለንደን ማራቶን አሸናፊ 42 ሺህ ፓውንድ ያገኛል። ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው እነ ናጎያ የሴቶች ማራቶን እንኳ 250 ሺህ ዶላር ያሸልማሉ። የሴዑልና ዱባይ ማራቶች አሸናፊዎች ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ይዝቃሉ።

ብሬት ታድያ አበረታች መድኃኒቶች በኬንያ ቢስፋፉ ይገርማል ወይ ሲል ይጠይቃል።

“የጎዳና ሩጫ በአትሌቲክስ መስክ እጅግ አጓጊ ከሚባለው ነው። የአሸናፊዎች ሽልማት፤ የተሳትፎ ክፍያ. . . በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ውድድሮች ሯጮችን ይስባሉ።”

“ኬንያ እያየን ያለነው በርካታ ፕሮፌሽናል ሯጮች ሕይወታቸውን ሲቀይሩ ነው። በተለይ ደግሞ በኬንያዊያን ዓይን ሲታይ ትልቅ ገንዘብ ነው። ሕገ-ወጥ አበረታች መድኃኒቶች ኢንዱስትሪውን ዘልቀው የሚገቡት ለዚህ ነው።”

ብሬት እንደሚለው እኒህን ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች የሚሸጡ ሰዎች አትሌቶቹን ጠቅመው፤ እነሱም ደኅና ገንዘብ ያገኛሉ።

አዝቤል ኪፕሮፕ
የምስሉ መግለጫ,በአበረታች መድኃኒት ምክንያት ለአራት ዓመት የታገደው አዝቤል ኪፕሮፕ

“ኬንያን ልዩ የሚያደርጋት ነገር አለ። እኒህ ኬንያዊያን አትሌቶች ሃገራቸውን በኦሊምፒክስ መድረክ ሲወክሉ አይታዩም። ሌሎች ሃገራት ማዕከላዊ ቡድን ይዘው ፕሮፌሽናል ሯጮች በታላላቅ መድረኮች ሃገራቸውን ይወክላሉ።”

ለምሳሌ ይላል ብሬት “ለምሳሌ በሌሎች ሃገራት 100ኛ ደረጃ ላይ ያለ ሯጭ ኑሮውን የሚደጉመው በሌላ ሥራ ነው። በኬንያ ግን 100ኛ ደረጃ ላይ የማራቶን ሯጭ በየክፍለ ዓለማቱ እየዞረ ረብጣ ብር ያገኛል።”

ኬንያ ከ15 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት በተዘጋጀው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ከአንድ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ሳትወጣ ቀርታለች።

በዓለም አቀፍ መድረክ በአትሌቲክስ ስሟ የጎላው ኬንያ የፀረ-አበታች መድኃኒት ተቋም የመሠረተችው በፈረንጆቹ 2016 ነው።

በወቅቱ ኬንያ ከሪዮ ኦሊምፒክስ መድረክ ልትባረር ከጫፍ ደርሳ ነበር።

በ2018 የዓለም ፀረ-አበታች መድኃኒት ተቋም [ዋዳ] “አበረታች መድኃኒት በኬንያ” ሲል ባወጣው ፅሑፍ 138 ኬንያዊያን አትሌቶች ምርመራቸው ‘ፖዘቲቭ’ ሆኗል ብሏል።

እኒህ አትሌቶች አበረታች መድኃኒት ወስደው የተገኙት ከ2014-18 ባለው ጊዜ ቢሆንም 14 በመቶው ብቻ ናቸው ከውድድር በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ የተገኙት።

የዋዳ ሪፖርት እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ አትሌቶች የወሰዱት መድኃኒት በቀላሉ የተገኘ ነው። ብሬት እንደሚለው ግን በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጉዳዩ ውስብስብ እየሆነ ወደ “የተቀናጀ የወንጀል ሥራ” አምርቷል።

በዚህ ዓመት አበረታች መድኃኒት ወስደው የተገኙት ቤቲ ሌምፐስ እና ኤግሌ ናልያኛ ከዶክተር አመጣነው ያሉት ወረቀት ሐሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ምርመራውን ያደረገው ተቋም ይህ ማለት አበረታች መድኃኒት የሚወስዱ ኬንያዊያን አትሌቶች ከጀርባ የሚያግዛቸው ሰው እንዳለ ጠቋሚ፤ እኒህ አጋዦች ወንጀል እየፈፀሙ ነው ብሏል።

በ2020 እንደ አሲክስ፣ አዲዳስ እና ናይኪ ያሉ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች በጥምረት 300 የረዥምር ርቀት ሯጨችን ለመመርመር 3 ሚሊዮን ዶላር ለግሰዋል።

ነገር ግን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ይህ የምርመራ ሂደት ላለፉት ሶስት ዓመታት በጣም ቀርፋፋ በሚባል መልኩ በመካሄዱ 80 አትሌቶች ብቻ ናቸው የተመረመሩት።

በ2022 ደግሞ የኬንያ መንግሥት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለፀረ-አበታች መድኃኒት የሚሆን 5 ሚሊዮን ዶላር ለመመደብ ቃል ገብቷል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝደንት ሎርድ ኮ በ2015 በአበረታች መድኃኒት ምክንያት ሩሲያን ከአትሌቲክስ ማገዳቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ የሩሲያ አበረታች መድኃኒት በመንግሥት ስፖንሰር የተደረገ ቢሆንም ኬንያ ከኢንዱስትሪው ባለመታገዷ ዕደለኛ ናት የሚሉ አሉ።

በአበረታች መድኃኒት ምክንያት በርካታ አትሌቶች ከታገዱባቸው ሃገራት መካከል ሩሲያና ሕንድ ብቻ ናቸው ከኬንያ በላይ የተቀመጡት።

በኬንያ ያለው ሙስና “አሳሳቢ ነው” የሚለው አንቲ ኢንተግሪቲ ዩኒት በቅርቡ የኬንያ መንግሥት ቃል የገባው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ይሻል።

እርግጥ ነው በርካታ አትሌቶች ተመረመሩ ማለት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጥ ነው።

ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲዎች እንደሚሉት ቁጥራቸው ያነሰ አትሌቶች ውጤታቸው ‘ፖዘቲቭ’ መሆኑ ሊያስፈነድቅ አይገባም።

“ካልደፈረሰ አይጠራም” የሚል እምነት ያለው ብሬት እንደሚለው በርካታ ኬንያዊያን አትሌቶች ምርመራው ወድቀው መገኘታቸው እንደውም ስኬት ነው።

ለዚህም ነው አበረታች መድኃኒት ወስደው የሚገኙ ኬንያዊያን አትሌቶች ቁጥር መጨመሩ መልካም ነው የሚለው።

የአጭር ጊዜ ሕመም፤ ለረዥም ጊዜ እፎይታ።