
ከ 2 ሰአት በፊት
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ሰላማ ቤተ ክህነት ከተመረጡት አስር ኤጲስ ቆጶሳት መካከል የስድስቱን ሹመት ዛሬ ሐምሌ 16፣ 2015 ዓ.ም በአክሱም አከናወነ።
ዛሬ በአክሱም ጽዮን ማርያም ሹመት የተሰጣቸው ኤጲስ ቆጶሳት በትግራይ ለሚገኙ ሃገረ ስብከቶችና እንዲሁም በውጭ አገራት እንዲያገለግሉ መሆኑንም ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የትግራይ ቤተ ክህነት ኤጲስ ቆጶሳት እንሾማለን ማለታቸው የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና ህጓን የሚጥስ እንደሆነ በመግለጽ የፌደራሉም መንግሥትም ጣልቃ በመግባት እንዲያስቆሙት መጠየቁ ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በመነጠል የተቋቋመው መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነት ለመጀመሪያ ጊዜ የጵጵስና ሹመቱንም ያካሄደው በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው።
በኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙት ውስጥ አምስቱ በትግራይ ባሉ ሃገረ ስብከቶች የሚያገለግሉ አንደኛው ደግሞ በአሜሪካ አገልግሎት እንደሚሰጡም ተገልጿል።
በዛሬውም ዕለት ሹመት የተሰጣቸው አቡነ ሊባኖስ ለደቡብ ትግራይ፣ አቡነ ናትናኤል ለምዕራብ ትግራይ፣ አቡነ እምባቆም ለደቡብ ምስራቅ ትግራይ እንዲሁም አቡነ አረጋዊ የትግራይ ቤተ ክህነት መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ኤጲስቆጶስና ዋና ጸሃፊ ሆነዋል።
በተጨማሪም አቡነ ዮሃንስ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲሁም አቡነ አትናቴዎስ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶሳት ሆነው ተሹመዋል።
በምርጫው ውስጥ መካተታቸው የተነገረው የአውስትራሊያ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ አባ ሰረቀብርሃን ወልደ ሳሙኤል አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ወደ ትግራይ ለመሄድ ተከልክለው ከቀናት በኋላ ወደ ህንድ በአስገዳጅ መልኩ መላካቸው ተዘግቧል።
ዛሬ የተደረገውን ሹመት በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ ባትሰጥም ሐምሌ 11/ 2015 ዓ.ም ባወጣችው መግለጫ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ “አገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነትን የሚያናጋ ብሎም ሃገራዊ ቀውስ የሚያስከትል” ስትል ገልጻዋለች።
ይህንን መግለጫ ያወጣው የመንበረ ፓትርያተርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር የትግራይ ክልል ተወላጅ ጳጳሳትና ሊቃውንት “የድርጊቱን ቀኖና መጣስና የሚያስከትለውን ጉዳት” በተመለከተ በትግርኛ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሚዲያ እንዲያስተላልፉም አቅጣጫ አስቀምጧል።
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይቅርታ ላይ ከትግራይ የተሰጠ ምላሽ7 ሀምሌ 2023
- ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲያስቆም መንግሥትን ጠየቀ13 ሀምሌ 2023
- የትግራይ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለመመለስ ምን ይላሉ?25 ግንቦት 2023
በተጨማሪም ሰላማዊ አማራጮች እንዳሉ ሆኖ የህግ አግባብን በመጠቀም “የቤተክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም እንዲከበርም” መመሪያ እንዲሰጥበት ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል።
ይህንንም አስመልክቶ የትግራይ መንበረ ሰላማ ቤተ ክህነት ዋና ጻሃፊ ተስፋዬ ሃደራ “እኛ ህጋዊ ነን። እነሱ (ሲኖዶሱ) የኛን ህጋዊነት የሚጠይቁን እነማን ናቸው። ራሳቸውስ ህጋዊ ናቸው?” የሚል ምላሽ እንደሰጡም የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ለሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስን ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን በገንዘብ እና በቅስቀሳ በጦርነቱ ተሳትፋለች ብለው የትግራይ አባቶች ይወቅሷታል። በተጫማሪም በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት ውድመትና ምዕመናን ላይ ግድያ ሲፈጸም ሲኖዶሱ ዝምታን መርጧል በማለትም ይወቅሱታል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የቤተክርስቲያኗን አባቶች እና ምዕመናንን ደኅንነት በተመለከተ አስፈላጊውን ሁሉ ባለማድረጉ ይቅርታ መጠየቁን ቢገልጽም ከትግራይ አባቶች ዘንድ በቂ አይደለም የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከትግራይ አባቶች ጋር ለመነጋገር ወደ መቀለ ቢያቀናም የትግራይ አባቶች በውይይቱ ላይ ባለመገኘታቸው ንግግሩ አለመካሄዱ የሚታወስ ሲሆን በኋላም የትግራይ ቤተ ክህነት “ውይይቱን በተመለከተ የደረሰን ደብዳቤ የለም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።