
ከ 8 ሰአት በፊት
የዛሬ ስልሳ ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ-
ነጻነታቸውን ያገኙ አፍሪካውያን ሊመክሩ ነው ተባለ።
የግብጹን መሪ ገማል አብደል ናስርን ለመቀበል ከጅማ፣ ከሐረርና፣ ከአሩሲ በርካቶች ተመሙ።
ድህነትን የተጠየፈችው አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት የሚመጡ እንግዶቿን ለመቀበል የኔቢጤዎችን፣ የቀን ሰራተኞችን እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎችን አጎረች።
ሚሊዮኖች አፍሪካውያን ዜጎችን በጭቆና ቀንበር ካንበረከከው፣ ሰብዓዊነትን ከማማ ላይ ካወረደው እንዲሁም የነጮችን የባህል፣ የእሳቤና የፖለቲካ የበላይነት ለዘመናት የሰበከውን ቅኝ ግዛትን ታግለው ያሸነፉ ተምሳሌቶችም ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመምከር ከተገኙትም መካከል ነጻነቷን ካገኘች ዓመት የሆናት የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት አህመድ ቤንቤላ፣ የታንጋኒካው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የጊኒው አህመድ ሴኩቱሬ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ፣ የግብጹ አብደል ገማል ናስር ይገኙበታል።
አዲስ በተገነባው በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ እየመከሩ የነበሩት አብዮተኞች ክርክር ጦፈ።
የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባታል ሲሉም አጥብቀው ተከራከሩ።
ይህ እድል ሊያመልጠን አይገባም የአፍሪካ ሕዝብም ይቅር አይለንም አሉ።
የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም በአፍሪካዊ መልክ የቀረጹት ጁሊየስ ኔሬሬ በበኩላቸው አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር ሆነው መንግሥት መመስረት ቀስ በቀስ የሚሆን ነው አሉ።
በአንድ በኩል ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ላይቤሪያን ጨምሮ አብላጫውን የያዙት ሞኖሮቪያ የተሰኘው ቡድን የአፍሪካ መዋሃድ ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው የሚል እምነት ነበራቸው።
በሌላኛው ጎን ቁጥራቸው አነስ ያሉትና በግራ ዘመም አብዮተኞቹ እንደነ ንክሩማህ፣ ሴኩቱሬ የሚመራው የካዛብላንካው ቡድን በእሳቤ ደረጃ ሳይሆን አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር መንግሥት መመስረት ይገባል ብለው ተሟገቱ።
የአንድነት ህልማቸው ተቀባይነት ያላገኘው ክዋሜ ንክሩማህ ረግጠው ለመውጣት ዛቱ።
በዚያች ዕለት፤ በሰባዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት አጼ ኃይለ ስላሴ የጊኒው ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን ወደ ጎን ጠሯቸው።
የግራ ዘመም አብዮተኞቹን ሴኩቱሬንና ንክሩማህን ጥብቅ ወዳጅነት ኃይለ ስላሴ ያውቁ ነበር።
ኃይለ ስላሴ በፈረንሳይኛ ‘mon fils’ ትርጉሙም ልጄ እንደማለት ነው።
ልጄ ‘እለምንሃለሁ፣ ሂድና ወንድምህን አምጣ” አሉት።
ሴኩቱሬም በፈረንሳይኛ ‘oui pere’ (እሺ አባቴ) የሚል ምላሽ ሰጡ።
ሴኩቱሬ በፍጥነት ወጥቶም ክዋሜ ንክሩማህን ተመልሶ ይዘው ሲመጣ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ውስጥ ተሳታፊው በጭብጨባ እንዲሁም የአፍሪካን አንድነት ለመመስረት በነቂስ ሲጠባበቅ የነበረውም በደስታ ፈነደቀ።
ንክሩማህ ተመልሰው ከመጡም በኋላ “ለአፍሪካ ስል ተሳትፎዬን እቀጥላለሁ” አሉ።
“ንክሩማህ ረግጦ ቢወጣ አስከፊ ይሆን ነበር። በወቅቱ አጼ ኃይለ ስላሴ ድንቅ የተባለውን የዲፕሎማሲ መንገድም በመጠቀም መልሰውታል” ይላሉ የወቅቱን ሁኔታ በማስታወስ ከቢቢሲ ወርልድ ጋር በአንድ ወቅት ቆይታ አድርገው የነበሩት ዶክተር በረከት ኃይለ ስላሴ
በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩትና የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኝ የነበሩት ዶክተር በረከት ኃብተ ስላሴ የጉባኤውን ረቂቅ ቻርተርም ከጻፉት አንዱ ናቸው።

- ከተማ ይፍሩ፡ ያልተነገረላቸው የአፍሪካ አንድነት ባለራዕይ8 የካቲት 2019
- መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ያገናኘችው ታሪካዊቷ ዛንዚባር12 ግንቦት 2023
“የአፍሪካ አባት” በመባል የሚጠሩትና ኢትዮጵያን ለ44 ዓመት የገዟት አጼ ኃይለ ስላሴ ዛሬ፣ ሐምሌ 16 የተወለዱባት ዕለት ናት።
‘ያህዌ’ በሚለው መጠሪያ ‘ጃ’ እያሉ የሚጠሯቸው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮችም የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ 131ኛ የልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል።
በተለይም ንጉሱ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ጥቁር ዲያስፖራዎች ሻሸመኔ ላይ በሰጡት 500 ሄክታር የሚኖሩ ራስ ተፈሪያውያንም እለቷ በደመቀ ሁኔታ ትታሰባለች።
በተለምዶ ጃማይካ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አጼ ኃይለስላሴ ይወደሳሉ፣ሞዓ አንበሳ ምልክት ያለበት ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ይውለበለባል።
ኢትዮጵያ የተስፋይቱ ምድር እንደሆነች ይዘመራል።

‘የፊውዳሉ ጨቋኝ?’ ‘ነጻ አውጭ?’
በሐረር፣ ኤጀርሳ ጎሮ ተወልደው ኢትዮጵያን መምራት ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቷ አጋፋሪ መሪም ሆነው ታይተዋል።
በታሪክ ጸሃፍያንም ዘንድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ካሉ መሪዎች የዓለም አቀፉን መድረክና ምናብ በመቆጣጠር ከፍተኛ ስፍራ ይሰጧቸዋል።
በታይም መጽሄት ሁለት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ሰው የሚል ስያሜ አትርፈዋል።
ንግግሮቻቸው በሬጌ ዘፈኖች ተካትተው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ደርሰዋል።
ፎቶዎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ‘የቃል ኪዳኗ ምድር’ መግቢያ ነው ተብለው ለጥቁር ዳያስፖራው ተሰጥቷል።
በህይወት ያሉ መሲህ፣ ፈጣሪ ተብለው ተሰግዶላቸዋል።
በርካቶች የሳቸውን ልብስ ለመንካት ተሻምተዋል፣ ሲያዩዋቸው አልቅሰዋል።
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል።
በተጓዙባቸው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ አገራት ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ እንደ አጀብ ተመልክቷቸዋል።
አገራት በስማቸው መንገዶች፣ ጎዳናዎች፣ትምህርት ቤቶች ሰይመውላቸዋል።
አጼ ኃይለ ስላሴ በታሪካዊው የጃማይካ ጉብኝታቸው ለትምህርት ቤት መሰረተ ድንጋይ ባስቀመጡባት ስፍራ በስማቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመዲናዋ ኪንግስተን ይገኛል።
ለአፍሪካ ነጻነት በተጫወቱት ሚናም ጁሊየስ ኔሬሬ በስማቸው ዛንዚባሯ ራስ ገዝ አስተዳዳር ስቶን ታውን ከተማም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል።
በኬንያዋ ናይሮቢ እንዲሁም በዛምቢያዋ ሉሳካ የአጼ ኃይለ ስላሴ ጎዳናዎች አሁንም አሉ።
በጥቁር ዓለሙ እንደ ነፃ አውጭ፣ የአፍሪካ አባት፣ ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከኩ፣ ጸረ ኢምፔሪያሊስት የሚል ስያሜን አትርፈዋል።
የፊውዳሉ ገዢ አጼ ኃይለ ስላሴ የፊውዳልን ስርዓት በጽኑ ይቃወሙ በነበሩ ጥቁር ግራ ዘመሞችም ዘንድ አንደ ተስፋና ነጻ አውጭ ተደርገው እንደተሳሉም የታሪክ ምሁሯ ጁሊያ ቦናቺ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይናገራሉ።
ጁሊያ ቦናቺ ራስ ተፈሪያን ወደ ኢትዮጵያን መመለስን አስመልክቶ ‘ኤክሶደስ፣ ሄይርስ ኤንድ ፖዮነሪስ ራስታፋሪ ሪተርን ቱ ኢትዮጵያ’ (Exodus! Heirs and pioneers, Rastafari return to Ethiopia) የተሰኘ መጽሃፍ ደራሲ ናቸው።
በኢትዮጵያ ባለው ገጽታቸው በአንድ መልኩ ስርዓተ መንግሥቱን ወደተማከለ አስተዳደር በማምጣት፣ትምህርትን በማስፋፋት፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን በማስጀመር ዘመናዊና ተራማጅ ነበሩ ይባላሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ባላባቶች፣ ጭቃ ሹምና መኳንንቱ አርሶ አደሩን ከሰው በታች አውርደው እያንገላቱ በገዙበት፣ በርካቶች በባርነት የነበሩባት፣ በድህነትና በጭቆና የሚማቅቅበት ስርዓት ዋና አጋፋሪ ናቸው በማለትም ይወቀሳሉ።

በእርሳቸው ስርዓት ትግራይና ወሎ ተርቦ በመቶ ሺዎች አልቀዋል።
ንጉሰ ነገስቱ በወሎ ረሃብ በርካቶች በምግብ እጦትና በጠኔ ሲረግፉ እርሳቸው 80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር ሚሊዮን ዶላሮችን አውጥተዋል ሲሉም ዶክተር ዮሃንስ ወልደማርያም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተችተዋቸዋል።
የልጅነት ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ ያሳለፉትና ጭቆናውን አይተው ላደጉት ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ዶክተር ዮሃንስ ወልደማርያም በጥቁሩ ምናብም ሆነ በዓለም ላይ እየተሳሉበት ያለው ገጽታ ሊቆም ይገባል ሲሉም ይከራከራሉ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህንን በተመለከተ ‘ዘ ሮማንቲክ ሪራይቲንግ ኦፍ ኃይለ ስላሴስ ሌጋሲ መስት ስቶፕ’ የሚል ጽሁፍም አቅርበዋል።
የተነሳባቸውን አመጽ ሁሉ በኃይል ለመመለስም ጥይት አዝንበዋል የሚሏቸው ኃይለ ስላሴ ከሚጠቀሱትም ውስጥም የጎጃም፣ የባሌና በትግራይ የተነሱ የአርሶ አደሮች አመጾች ናቸው።
በትግራይ የተነሳባቸውን ተቃውሞም ለመደምሰስ ከብሪታንያው ሮያል አየር ኃይል በመተባበር የአየር ጥቃት መፈጸማቸውን የታሪክ ድርሳናት መዝግበውታል።
ዶክተር ዮሃንስ አንዱ ጭካኔ ማሳያ አድርገው የሚያነሱት ነው።
በስልጣን ላይ የሚቀናቀኗቸውን ለማስወገድ የጭካኔ በትራቸውን የዘረጉ ናቸው የሚሏቸው ኃይለ ስላሴ “ልጅ እያሱን መስዋዕት አድርገው ስልጣን ላይ ነው” የመጡት ይሏቸዋል።
መፈንቅለ መንግሥት አንስተዋል የተባሉትን መንግሥቱና ገርማሜ ንዋይ በስቅላት መገደላቸው እንዲሁም የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎችን ለመቅጣት በሚል ያደረሷቸውን ግድያዎች ይጠቅሳሉ።
የአጼ ኃይለ ስላሴ ገጽታ በተቃርኖ የተሞላ ነው።
አፈታሪኮች፣ እምነቶች፣ ውክልና ብዙ ሁነቶችም የተቀላቀሉበት ነው።
ሆኖም በስርዓታቸው ላይ የሚነሱ ወቀሳዎች በዓለም አቀፍ ላይ ያላቸውን ገጽታ አላጠለሸውም።
“ውክልናውና እውነታው የተለያዩ ነገሮች ናቸው” የሚሉት ዶክተር ዮሃንስ የሚባሉትን “ነጻ አውጭ፣ የጥቁር መብት ተሟጋች” ሳይሆኑ ትከክለኛ ገጽታቸው “አምባገነን መሆናቸው” ሊነገር ይገባል ሲሉም ለቢቢሲ ያስረዳሉ።
የአንዱ ነጻ አውጭ ለሌላኛው ጨቋኝ መሆን የተለያዩ የታሪክ ታላላቆች እውነታ ቢሆንም የኃይለ ስላሴን ያህል ግን የታሪክ እንቆቅልሽ የሆነ እንደሌለ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታን በጥቂቱ
በርዕዮተ ዓለምና በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ተከፋፍለው የነበሩትን አዲሶቹን መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ቀላል አልነበረም።
በተለይም ጉዳዩን አወዛጋቢ ያደረገው በወቅቱ የሞኖሮቪያ አባል የነበሩት የቶጎው መሪ መገደል ያኛውን ቡድን መወንጀልና ሁኔታዎችም መካረር ጀመረ።
በርካታ ነገሮችንም ለማለሳለስና ለዚህ ጉባኤ ስኬት ዋነኛው የአጼ ኃይለ ስላሴ ቀኝ እጅ የነበሩት በንጉሱ ዘመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ።
አቶ ከተማ ኃይለስላሴ የነበራቸውን ዝናና ክብርም በመጠቀምም እነዚህን መሪዎች ማሰባሰብ የቻሉት።
በዚህም ጉባኤ ላይ ነጻ ላልወጡ አገራት የአፍሪካ የነጻነት እንቅስቃሴ (አፍሪካን ሊበሬሽን ሙቭመንት) እንዲመሰረት ተወሰነ።
በመጨረሻም በ32 አባል አገራት በጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ተጠናቀቀ።
“ያለፉ የፍትህ መጓደል ትዝታዎች አሁን ካለንበት ጠቃሚ ምዕራፍ ሊያዘናጋን አይገባም። የጥላቻ አሲድ ነፍሳችንን እንዳይሸረሽርና ልባችንን እንዳይመርዝ ቂም በቀልን በመተው ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻችን ጋር በሰላም መኖር አለብን” ሲሉም ኃይለ ስላሴ በምስረታው ወቅት ተናገሩ
ንክሩማህ ይህ ሁሉ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በተለይም በአዲስ አበባ በነበራቸው አስደሳችና የማይረሳ ቆይታ ከልብ የመነጨ ምስጋናቸውንም አደረሱ።
ለማጠቃለያም በጋናዊ ገጣሚ ለኢትዮጵያ ክብር የተጻፈች ግጥም ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አነበቡላቸው።
ግጥሙም “ኢትዮጵያ ትነሳለች፣ የአፍሪካ ብሩህ ዕንቁ፣ በለመለመ ኮረብታዎች መካከል ከፍ ያለች
መቼም የማይነጥፈው የአባይን ወንዝ (የናይል ወንዝ) የወለደች
ኢትዮጵያ ትነሳለች፣ ኢትዮጵያ፣ የጥበብ ሃገር
ኢትዮጵያ፣ የጥንታዊ የአፍሪካ ጀግንነት አገዛዝ መገኛ፣ የአፍሪካ ባህል ትምህርት ቤት
ኢትዮጵያ፣ ጥበበኞች ይነሱብሻል። የአፍሪካን ተስፋ እና ዕጣ ፈንታንም እንደገና ያሰርጻሉ” አሉ።

ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስና በጥቁሮች ምናብ
ለተወሰኑ ማህበረሰቦች ኢትዮጵያና ነገስታቶቿ የግፍ ምንጭ፤ በደሎች፣ ግዛት ለማስፋፋትና ህዝብ ለማስገበር ጭፍጨፋዎችን የፈጸመች እንዲሁም ባርያዎችን በሕይወታቸው የቀበረች ናት።
ለሌሎች ደግሞ የስልጣኔ መነሻ፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ የጥበበቦች መዳረሻ ለነጮች ያልተንበረከከች፣ የራሷ ፊደልና የቀን መቁጠሪያ ያላት፣ የበርካታ ድንቅ ባህሎች መዳረሻ ናት።
ለተለያዩ ማህበረሰቦች የተለያየ ገጽታ ነበራት ብለው የሚቀበሉት ያሉትን ያህል እንደ ራስ ክዊንታሰብ ላሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የተቀደሰች አገር በመሆኗ ‘በጫማም’ ለመርገጥ የሚሳሱላት ናት።
የካሪቢያኗ ደሴት ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ተወላጁና ኃይለ ስላሴ የሙዚቃ ማዕከላቸው የሆነው የሬጌው ሙዚቃ ተጫዋቹ ራስ ክዊንታሰብ አገሬ ወደሚሏት ኢትዮጵያ ከመጡ እርሳቸው እንደሚሉት ‘ከተመለሱም’ 27 አመታትን ደፍነዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ ደጋግሞ የተነሳውና ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’ የተባለላት ኢትዮጵያ ለራስ ተፈሪያን የቃል ምድር፣ ጽዮን ናት።
ራስ ክዊንታሰብ ከቢቢሲ ጋር በስልክ ባደረጉት ዘለግ ያለ ቆይታ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ አጼ ኃይለ ስላሴ ሲናገሩ ዋቢ የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው።
ስለ ኢትዮጵያ ‘የተስፋዋ ምድር’ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት ልጅ እያሉ ነበር።
ህጻን እያሉ ኢትዮጵያ የተጠቀቸስበት የግሪክ አፈታሪክ መጽሐፍ አነበቡ።
መጽሐፉ የግሪክ አማልክት ከሰዎች ጋር መዝናናት ሲፈልጉ ወደተመረጠችው ኢትዮጵያ ጎራ ይላሉም ይላል።
የልጅነት አዕምሯቸውም ትክክለኛ ስፍራ አልመሰላቸውም።
አጼ ኃይለ ስላሴ በታሪካዊው የካሪቢያን ደሴቶች ጉብኝታቸውም የሳቸው ትውልድ ቦታ ወደሆነችው ትሪንዳድ እና ቶቤጎ መጡ።
ልጅ የነበሩት ክዊንታሰብ በጋዜጣ ላይ የአጼ ኃይለ ስላሴን ፎቶ ተመለከቱ።
በነጭ ፈረስ ላይ ከሚታዩት ኃይለስላሴ ፎቶ ስርም ‘ታላቁ የአፍሪካ ንጉስ’ የሚል ተጽፎበት ነበር።
ከዚያን ጊዜም ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ ቃል የተገባላት የተስፋይቱ ምድር፣ አጼ ኃይለ ስላሴም አምላክ መሆናቸው መነሻ እንደሆናቸው ያስረዳሉ።
በፈረንሳይ ‘ኢንስቲትዩት ኦፍ ሪሰርች ፎር ሰስቴይነብል ኦፍ ዴቨሎፕመንት’ በተሰኘ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ጁሊያ ለበርካታ ዓመታትም በኢትዮጵያ ሰርተዋል።
ለታሪክ ተመራማሪዋ የኃይለ ስላሴ በዓለም አቀፉ ያላቸው ገጽታም ሆነ ዋነኛው መነሻ ኢትዮጵያ የነበራት ስፍራ ነው።
ጥቁር ዓለም ተብሎ በሚጠራው ዘንድ ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ስለነበራትና፣ የትግል ተምሳሌት መሆኗም ነው።
እንዲሁም ሉዓላዊነትን ወክላ መታየቷ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የሰው ልጆች እንደ ሸቀጥ በተሸጡበትና በተለወጡበት፣ አፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿን በባህሮች በገበረችበት ኢትዮጵያ እንደ ተስፋ መታየቷ መጠቀስ አለበት ይላሉ።
ለዚያም ነው የታሪክ ተመራማሪዋ በምዕራቡ ዓለም በጥቁሮች የተመሰረቱ ጽዮን፣ አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ምኒልክ የሚሉ ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት የተሰየሙት ይላሉ።
በዚህ የታሪክ ማማ ላይ ነው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ወደ ስልጣን የመጡት።
ዶክተር ዮሃንስም ቢሆኑ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰች መሆኗ፣ ቅኝ ግዛት ያልተገዛች እንዲያውም አውሮፓውያኑን ያሸነፈች አገር መሆኗ፣ ኃይለ ስላሴ በወቅቱ ባይኖሩም የአድዋ አሻራ እንደተከተላቸው ይጠቅሳሉ።
“አንድ ጥቁር ኃይል መብቱን ለማስከበር አድዋ ላይ ተዋግቶ፣ አሸንፎ አሳፍሮ ላካቸው ይሄም ለአጼ ኃይለ ስላሴ ጠቅሟቸዋል። የሳቸው ማንነት ሳይሆን የነበረው ታሪካዊ ሁኔታ ተጠቃሚ አደረጋቸው። ማንነታቸው ቢታወቅ ኖሮ ብዙ ሰው የሚያደንቅበት ላያገኝ ይችላል” ይላሉ።
ጥቁሩ ዓለም በጭቆና በሚማቅበት ወቅት “ሁሉንም ሊያነቃንቅ የሚችል አንድ ተወካይና ምልክት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበር። እናም ኢትዮጵያ የምትባል አገር ፤ አጼ ኃይለስላሴንም አገኙ”ሲሉም ያስረዳሉ

ኃይለ ስላሴ በዓለም አቀፉ ምናብ
ኃይለ ስላሴን በጥቁሩ ዓለም ምናብ ከፍ ያለ ስፍራ ውስጥ የሚያስቀምጧቸውም በርካታ ክስተቶች አሉ።
የታሪክ ተማራማሪዋ ከሚጠቅሷቸው አንዱ በጎሮጎሳውያኑ 1920ዎቹ የባርነት ስርዓት መወገድ ነው።
የዓለም መንግሥታቱ ኅብረት የሆነውን ሊግ ኦፍ ኔሽንን ለመቀላቀል አንደኛው የተቀመጠው መስፈርት በአገሪቷ ውስጥ የነበረውን የባርያ ፈንጋይ ስርዓት ማስወገድ ነበር።
ጁሊያ እንደሚሉት ይህ “ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫን የቀየረ ብቻ ሳይሆን በባርነት ለመጡና በቅኝ ግዛት ስር እየማቀቁ ለነበሩ” ተስፋ የሚያንጸባርቅ ነበር።
ኢትዮጵያም ከሌሎች የመንግሥታት ስፍራ ተቀመጠች።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ባርነትን ለማስወገድ አዋጅ ብታወጣም በህጋዊ መንገድ ሙሉ በሙሉ የታገደው በአውሮፓውያኑ 1942 ነበር።
አጼ ኃይለ ስላሴ ለጥቁሮች መብትም ሆነ አፍሪካውያን ነጻ እንዲወጡ የተጫወቱት ሚናም የለም የሚሉት ዶክተር ዮሃንስ እንዲያውም የባርነት ፈንጋይ ስርዓትን ለማስወገድ ፈቃደኛም አልነበሩም ሲሉ ይተቻሉ።
አንደኛው የሚያነሱትም የጃማይካዊው መብት ተሟጋች ጋርቬይ “የባሪያ አሳዳሪ ናቸው” ብሎ የተቻቸውን ነው።
ኢትዮጵያ የተወሰኑትን የራሷን ህዝቦች በባርነት እየሸጠችና እየለወጠች እንዴት የነጻነት ተምሳሌት ትሆናለች ብለውም የሚጠይቁ አለ።
ሌላኛው ጁሊያ ደግሞ የሚጠቅሱት በ1920ዎቹ መጀመሪያ ኃይለ ስላሴ ከአንዳንድ ጥቁር ተቋማት ጋር ግንኙነት መመስረታቸውን ነው።
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ዘውድ ስም ደብዳቤዎች ስለመጻፋቸው የሚያሳዩ ምንጮች እና የታሪክ ማህደሮች እንዳገኙ የታሪክ ምሁሯ ይናገራሉ።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ የጥቁር ብሄርተኛ ድርጅት ተብሎ የሚጠቀሰውና በማርከስ ጋርቬይ የተቋቋመው universal Negro improvement Association (UNIA) አንዱ ነው።
ሌላኛው የዓለምን ምናብ የተቆጣጠረው ብለው የሚያነሱት የአጼ ኃይለ ስላሴ የንግሥና ሲመት ነው።
መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት የአጼ ኃይለ ስላሴ ዘውድ መድፋታቸው የጥቁር አፍሪካ ሉዓላዊ ፖለቲካዊ ኃይል መወከያም አደረጋቸው ይላሉ።
የንግሥና ሲመቱም ናሺናል ጂኦግራፊን ጨምሮ አሉ በሚባሉ ሚዲያዎች ፎቶዎች መውጣታቸውም በጥቁሮች ምናብም ሆነ በመላው ዓለም የራሱን ሚና ተጫውቷል ይላሉ።
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ፣ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዘ እምነገደ ይሁዳ፣ ስዩመ እግዚአብሔር፣ ተብለው በጎሮጎሳውያኑ ህዳር 2፣ 1930 ተሰየሙ።
ጃማይካዊው ፖለቲከኛና የሰብዓዊ መብት ተማጋች ማርከስ ሞሳያህ ጋርቬይ ከሲመታቸው በፊት “ጥቁር ንጉስ ዘውድ ሲቀዳጅ በአፍሪካ ተመልከቱ። የመዳን ቀን ቀርቧል” የሚል ተናግሮ ነበር።
ከአጼ ኃይለስላሴ የንግሥና ስርዓትም ጋር ተያይዞ የጋርቬይ ንግግር እንደ ትንቢት መፈጸሚያ ታየ።
በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ለነበሩም ነጻ የመውጫ ቀን መድረሷ ተነገረ።
ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች የንግስናውን ሲመት ፎቶዎች ይዘው ወጡ።
ከዓለም መሪዎች ስጦታ ጎረፈ።
ለራስ ኩዊንታሰብም ሆነ ለሌሎች ራስ ተፈሪያን ይህች ቀን አምላክ በስጋ የተገለጠባት ዕለት ናት።
በዚህ ወቅትም ነበር መጽሐፍ ቅዱስና የአጼ ኃይለስላሴን የንግስና ስርዓት የሚያሳዩ ፎቶዎች በጃማይካ መታየት የጀመሩት።
ከሰለሞን ስርወ መንግሥት ዘራቸው የሚመዘዝ፣ አፍሪካዊ ራስ ተፈሪ የሚባሉ አምላክ አሉ ተባሉ።
የመጀመሪያው ራስ ተፈሪያን እየተባለ የሚጠራው ሰባኪው ሌናርድ ሃውል ከፍተኛ ዕውቅና ማትረፍ ቻለ።

የራስ ተፈሪያኒዝም እንቅስቃሴ በቅኝ ገዥዋ ብሪታንያ በቀላሉ ሊታይ አልቻለም።
ሆኖም ሌናርድ የቅኝ ገዥዎቹን ትዕዛዝ በመጣስም ኃይለ ስላሴ አምላክ በስጋ የተገለጠበት ነው አለ።
ጃማይካውያንንም የብሪታንያ ተገዢዎች አድርገው እንዳያዩም መከረ።
እናንተ ኢትዮጵያውያን ናችሁ አለ።
ኃይለ ስላሴ ፈቃደኛ የሆኑ ጃማይካውያንንም ቃል ወደተገባላቸው የኢትዮጵያ ምድር ለመውሰድ መርከብ አዘጋጅተዋል ሲልም ለህዝቡ ነገረ።
5 ሺህ የሚሆን የአጼ ኃይለስላሴ የንግሥና ሲመት ፎቶዎችም ታተሙ።
እነዚህ ፎቶዎች ጽዮን ብለው ለሚጠሯት ኢትዮጵያ መግቢያ እንደ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት) እንደሚያገለግልም ለተከታዮቻቸው ተነገረ።
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት መሰረት ሌሎች ክርስቲያኖች የኢየሱስን ዳግም መምጣት ቢጠባበቁም ለራስ ኩዊንታሰብም ሆነ ለራስታዎች ኃይለስላሴ “(‘jesus reincarnate) ኢየሱስ ራሱን የገለጠባቸው” ናቸው።
ሌላኛው በዓለም አቀፉ ዘንድ ሰብዕናቸው ከፍ ብሎ እንዲወከሉ ያደረጋቸው ለታሪክ ምሁሯ የጣሊያን ወረራ ነው።
ዶክተር ዮሃንስም ቢሆኑ የጣሊያኖች ወረራና ያደረሱት ግፍ ንጉሱ ከፍ ያለ ስፍራ አሰጥቷቸዋል ይላሉ።
ክዋሜ ንክሩማህ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በአሜሪካ እየተማሩ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያን መወረር ሲሰሙ “ባቡር ላይ ነበርኩ እናም አለቀስኩ” በማለት መጽሐፋቸው ላይ መጥቀሳቸውንም ያወሳሉ።
ንጉሱ የፋሺስት ወረራውንም ለመታገል ከፊት ሆነው መጡ።
መላው ጥቁርም ይህንን ተቃወመ።

ኢትዮጵያን ከዚህ ወረራ መከላከል እንዲቻልም በርካታ ጸረ ፋሽስት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ።
ለኢትዮጵያ ጉዳይም የተነሳ ትልቁ ንቅናቄ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ሲሉ ነው የሚጠሩት የታሪክ ባለሙያዋ።
የጥቁሮች የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ መወረር ጥቁሮች እንደተወረሩ ተደርጎ ተቆጠረ።
ትግሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካን ትግል ተደርጎም ተወሰደ።
በጣሊያን አምስት ዓመቱ ወረራ ወቅት ኢትዮጵያን ለመደገፍ የአጼ ኃይለ ስላሴ የግል ሐኪም በነበሩት ዶክተር መላኩ በየን እና በአፍሪካን አሜሪካውያን የተመሰረተውም Ethiopian World Federation (ኢደብልዩ ኤፍ)ም አንዱ ነበር።
አጼ ኃይለ ስላሴ የተባበሩት መንግሥታት ሊግኦፍ ኔሽን የሆነችው አገራቸው በሌላ አባል በሆነችው ጣሊያን መወረሯን አገራቱ ለመተባባር የገቡትን ጽንሰ ሃሳብ በጽኑ የሚጥስ ነው ብለው አጥብቀው ተቹ።
ህዝቤ በመርዝ ጋዝ እያለቀ ነው አሉ።ፋሺስዝምንም አወገዙ።
በዚህም ወቅት ነው ታይምስ መጽሄት የዓመቱ ምርጥ ሰውም ሲል የሰየማቸው።
ኃይለ ስላሴም በእንግሊዟ ባዝ ከተማ ለግዞት ተዳረጉ።
ምንም እንኳን እንደነ ማርክስ ጋርቬይ የስደት ሁኔታም በከፍተኛ ሁኔታ የተቹት ቢኖሩም ለአገራቸው ድምጽ ለመሆንና ድጋፍ ለማሰባሰብ ረድቷቸዋል የሚሉ አልታጡም።

ከአምስት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በብሪታንያ ድጋፍ ከጭቆና እና ጭፍጨፋ ነጻ ወጣች።
በዓለም ላይ ካሉት ድሃ አገሮች አንዷ ሆና የአውሮፓ ኃያልን አገር ባለ በሌላ መሳሪያዋ እንዴት አሸንፋ፣ ነጻነቷን አስጠበቀች የሚለውም ለራስ ኪውንታሰብና በሌሎችም ዘንድ እንደ ተዓምር ታየ።
“የአፍሪካውያን ነጻነት ያነሳሳው የኢትዮጵያውያን ድል ነው። ” ይላሉ ክዊንታሰብ።
“በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን እንኳን እምነት፣ ድፍረት እና ፍትሃዊ ምክንያትን ከያዘ ዳዊት አሁንም ጎልያድን ያሸንፋል” ሲሉም ኃይለ ስላሴ ተናገሩ።
ኃይለ ስላሴ ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ መጓዛቸው በዓለም አቀፉ ምናብ የራሱን ሚና እንደተጫወተም ጁሊያ ይጠቅሳሉ።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ እርሳቸው በርካታ ጉብኝቶችን ያደረገ የአፍሪካ መሪ አልነበረም።
ኃይለ ስላሴ በአገር ውስጥ “መሬት ለአራሹ” እንቅስቃሴ ተቃውሞ በቀጠለበትም ወቅትም እንኳን በዓለም አቀፉ መድረክ የተከበሩ መሪነታቸው ተጠናክሮ ቀጠለ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፍራንሲስ ቻርለስ ደጎል ቀብር ላይ ተከብረው ፊት ለፊት ከተቀመጡ መሪዎች አንዱ ናቸው።
በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ መቶ ሚሊዮኖች ዶላር ወጥቶበታል (ቢሊዮን ዶላር ፓርቲ) ተብሎ በሚጠራው የፋርስ 2 ሺህ 500 ስርወ መንግሥት ሲከበርም የኢራኑ ሻህ መሃመድ ረዛ ፓህላቪ ከጋበዟቸው አንዱ ናቸው።
ነጻ የሆኑ የአፍሪካ አገራትን መጎብኘት፣ የሰላም ማስከበር ጉባኤዎች፣ የልማት ዕርዳታ ማሰባሰቢያዎች ላይ በክብር ከሚጋበዙት መካከል አጼ ኃይለ ስላሴን የሚስተካከል አልነበረም።

የአጼ ኃይለ ስላሴ ታሪካዊው የካሪቢያን ደሴቶች ጉብኝት
አጼ ኃይለ ስላሴ እንደ አምላክ ወደሚታዩባት ጃማይካ ሲያቀኑ የነበረው ስሜት ለየት ያለ ነበር።
ኃይለ ስላሴ ሚያዝያ 13/1958 ዓ.ም በጃማይካ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሱ።
ሲያዩዋቸው ያለቀሱ፣ ልብሳቸውን ለመንካት ሽሚያ ነበር።
እጃቸው ላይ ኢየሱስ እንደተሰቀለበት የችንካር ምልከት ታይቷል ተባለ።
ጃማይካ ከአጼ ኃይለ ስላሴ ጉብኝት አራት ዓመታትን ቀድማ ነው ነጻነቷን ያገኘችው።
የብሪታንያን እሴት አንቅሮ የተፋው የራስ ተፈሪያኒዝም እንቅስቃሴ ለብሪታንያ ተቀባይነት አልነበረውም።
የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ብሪታንያም ሆነ እንደ አዲስ ለተቋቋመው የጃማይካ መንግሥት አጼ ኃይለ ስላሴ ወደ ጃማይካ ቢመጡም እንቅስቃሴውን ሊገታው ይችላል የሚል እሳቤ እንደነበር ጁሊያ ይናገራሉ
“አምላክ የሚሉትን ይህንን ግለሰብ አጠር ያለ ጠይም ሰው መሆኑን ሲያዩ ነገሮች ይቀየራሉ” የሚል ነበር።
ነገር ግን የተገላቢጦሽ ተፈጠረ።
ጉብኝታቸው የራስታ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ አዲስ ጉልበት፣ አዲስ መንፈስ ሰጠው።
የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ በማዋቀር ትልቅ ሚና ነበረው።
“ ጉብኝቱን እንደ ጥምቀት ልናየው እንችላለን። አምላክ በምድር ላይ የተገለጠበት” ተብሎ እንደሚታመን ይናገራሉ።
ኃይለስላሴስ እነዚህን አገራት ለምን ለመጎብኘት መረጡ?
ጁሊያ እንደሚሉት ኃይለ ስላሴ ፓን አፍሪካዊ የሆነ ዓላማ ነበራቸው።
አንደኛው የመረጡት ወቅት አገራቱ ከአውሮፓውያኖቹ ቅኝ ገዥዎቻቸው ነጻ ከወጡ በኋላ ነው።
በወረራው ወቅት ጥቁሩ ሕዝብ አቤቱታ በማስገባት እንዲሁም በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን ለመስጠት ነበር።
በወቅቱ በቅኝ ግዛት ውስጥ ሆነውም ኢትዮጵያን ለመደገፍ በጦርነት ሊዘምቱም ባለመቻላቸው ጋዜጦችን በማሳተም ድምጻቸው እንዲሰማ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
በርካታ ጥቁር ነዋሪዎች ያሉባቸው እነዚህ አገራት ታማኝነታቸውን ለብሪታንያ የነገስታት ቤተሰብ ሳይሆን ለኢትዮጵያው ዘውድ መሆኑም የራሱ መልዕክት ነበረው።
በቅኝ ግዛት፣ እንዲሁ ድኅረ ቅኝ ግዛትም በድህነትና ሲማቅቅ የነበረው ሕዝብም ብሪታንያን አንቅሮ መትፋቱ ለብሪታንያም ሆነ ለነጻው የጃማይካ መንግሥትም እንዲሁ በቀላሉ የሚያዩት አይደለም።
የራስታ እንቅስቃሴንም በኃይል ለመግታት አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ጸጉራቸውን መላጨት፣ እስር፣ ግድያ፣ ስወራ ሌሎች የጭቆና መንገዶች ቀጠሉ።
ራስ ክዊንታሰብ እንደሚናገሩት ለዘመናትም ራስታዎች ስራ አለማግኘት ዘብጥያ መውረድና ሌሎች መከራዎችን አስተናግደዋል።

ሬጌ ሙዚቃና ኃይለስላሴ
አጼ ኃይለስላሴንም ሆነ ኢትዮጵያን ከስም በላይ ስም እንዲኖራቸው ያደረገ እንደ ሬጌ ሙዚቃ የለም።
ስለ አጼ ኃይለ ስላሴ መሲህነት፣ ነጻ አውጭነት፣ ባቢሎን ብለው የሚጠሩት የምዕራባውያኑ አለም መበስበስ እንዲሁም ቃል ወደተገባላት ምድር ጽዮን መመለስ ሌላም ሌላም መልዕክቶችን የሰሙት በሬጌ ሙዚቃ እንደሆነ ክዊንታሰብ ይናገራሉ።
ሩቅ በሚመስሉ እንደ ኢንዶኔዥያ ባሉ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬጌ ባንዶች እንዲኖሩ ሙዚቃው የፈጠረው ተጽእኖ ማሳያ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ያየነው ኢንዶኔዥያዊ ሙዚቀኛ ኢትዮጵያውያን በሚጠሩበት ራስ ሙሃመድ ስለ ኃይለስላሴ ማውራት የሚያስደንቅ ሊመስል ይችላል።
ከካሪቢያን ወጥቶም በአውሮፖ እንደ ጀንትል ማን ያሉ ነጭ የሬጌ ሙዚቀኞች እንዲሁም የራስ ተፈሪያኒዝም ዕምነት ተከታይ ነጮችንም በኢትዮጵያ ማየት የተለመደ ነው።
የሬጌ ሙዚቃን ከፍ ወዳለ ስፍራ በማሻገርም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበረው ቦብ ማርሌይ ተወዳዳሪ ያለው የለም።
ቦብ ማርሌይ በአውሮፓውያኑ ኃይለስላሴ በ1963 ኒውዮርክ ተካሂዶ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ አድርገውት የነበረውን ንግግራቸውን ‘ዋር’ በሚለው ዘፈኑ ውስጥ አካትቶታል።
“እንዲሁም የዘር ልዩነትን በሚመለከት ረገድ አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል፣ ይሻላል የሚለው እምነት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ ካልተወገደ….” ሰላም አይመጣም የሚለው በድምጻቸው ገብቷል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም እንደ ቴዲ አፍሮ ያሉት ሙዚቀኞችም ‘ጃ ያስተሰርያል’ በሚለው ሙዚቃው ለአጼው ያለውን ክብር ጠቅሷል።

በአጼ ኃይለ ስላሴም ዘመን ቢሆን ህዝቧ በረሃብ የረገፋባት፣ ጭቆና የተንሰራፋባት፣ ይህ ነው የሚባል መሰረተ ልማት ያልነበራት አገርና በድህነት ከዓለም ጫፍ የተቀመጠች ናት ይላሉ ዶክተር ዮሃንስ።
ኃይለ ስላሴም ለአገሪቷም፣ ለጥቁር ህዝብም ሆነ ምንም ፋይዳ ያለው ስራ አልሰሩም የሚሉት ዶክተር ዮሃንስ በመላው ዓለም የተሳሉበት ገጽታ ትክክል አይደለም ሲሉም ይሞግታሉ።
ኃይለ ስላሴ አገሪቷም ሆነ እሳቸው በነበራቸው እውቅና “መራብ ሳይሆን ከፍተኛ ዕድገት ላይ መድረስ ይቻል” እንደነበርም ንጉሱ ያልሆኑትን ስም መስጠትና ማጀገንና ማድነቅ ተገቢ አይደለም ይላሉ።
የኃይለ ስላሴ የግዛት ዘመን በጣም ረጅም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ክስተቶች የተስተናገደበት ከመሆኑ አንጻር ገጽታቸውም ሆነ ታሪካቸው ይህንን ውስብስብ ሂደት የሚያሳይ ቢሆን ጥሩ ነው ሲሉም ጁሊያ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።