July 24, 2023 – EthiopianReporter.com 


የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)

ዜና ዕንባ ጠባቂ ተቋም ውሳኔውን ባልተገበሩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ክስ መሥርቻለሁ አለ

ዕንባ ጠባቂ ተቋም ውሳኔውን ባልተገበሩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ክስ መሥርቻለሁ አለ

ኢዮብ ትኩዬ

ቀን: July 23, 2023

ውሳኔውን ባልተገበሩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ ክስ መመሥረቱን፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

ውሳኔውን ባልፈጸሙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ የተጠያቂነት ሥርዓትን በተመለከተ በ2015 በጀት ዓመት በ24 መዝገቦች ላይ የወንጀል ክስ መመሥረቱን፣ ከእነዚህ መካከል ዘጠኑ ክሶች ውሳኔ እንዳገኙና 15 መዝገቦች ደግሞ በክስ ሒደት ላይ መሆናቸውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ክስ የተመሠረተባቸው ተቋማት የባህር ዳር ከተማና የአሶሳ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰባት የከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዋና ዕንባ ጠባቂው በከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከተስተዋሉ ችግሮች መካከል በሙስና የተጠረጠሩ መሐንዲሶችን በሕጉ መሠረት ወደ ሌላ ሥራ እንዲሰማሩ አድርጎ፣ ጉዳያቸውን አጣርቶ ችግር ከሌለባቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ፈንታ፣ የይርጋዓለም ከተማ ከ11 ወራት በላይ ደመወዝ እንዳልከፈላቸው ለአብነት አስረድተዋል፡፡

‹‹ሠራተኞቹን ከ11 ወራት በላይ ያለ ደመወዝ ነው ያስቀመጧቸው፡፡ እኛም ከክልሉ አፈ ጉባዔ ጋር ሰዎቹ እንዲመለሱ ውይይት አድርገን የከተማ አስተዳደሩ ፈቃደኛ አይደለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

በተጨማሪም በ12 መዝገቦች ላይ በተቋሙ ተሰጡ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ያልፈጸሙ ተጠሪ ተቋማትን አስመልክቶ ተጠያቂ ለማድረግ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት መቅረቡን አቶ እንዳለ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በፓርላማ እንዲጠየቁ ሪፖርት የተደረገባቸው ተቋማት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ እንዲሁም የትምህርት ምዘናና ሥልጠና ባለሥልጣን መሆናቸውን ዋና ዕንባ ጠባቂው አስረድተዋል፡፡

ከሰባት ዓመት የአገልግሎት ጊዜ በኋላ በሕጉ መሠረት ሥራ መልቀቅ የሚቻል ቢሆንም፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በሕጉ መሠረት መልቀቂያ የጠየቁ ፖሊሶችን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መከልከሉን የገለጹት እንዳለ (ዶ/ር)፣ ‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደግሞ ለአንዱ ፖሊስ ይሰጥና ለሌላው በትውውቅ ይከለክላል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ነው ለምክር ቤቱ ያቀረብነው፤›› ብለዋል፡፡

ከውጭ አገር የተፈቀደላቸውን ዕቃ ይዘው የሚመለሱ ሰዎችን ከፈቃድ በላይ ነው በማለት ንብረት ስለሚወረስ፣ ችግሩ እንዲቀረፍ ዕንባ ጠባቂ መመርያ እንዲያወጡ ባስተለለፈው ትዕዛዝ መሠረት፣ መመርያውን ቢያወጡም መመርያው ከመውጣቱ በፊት ንብረታቸው የተወሰደባቸው 303 ሰዎችን ንብረት ተመላሽ ባለማድረጉ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጉዳይም ለፓርላማ ሪፖርት መደረጉን አክለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመውጫ ፈተና መመርያ ከመውጣቱ በፊት ከቴክኒክና ከሙያ ምሩቃን መካከል አንዳንዶች ዲግሪያቸውን እንደሚከለከሉ፣ በተመሳሳይ ጊዜ ለተፈተኑ ሌሎች ምሩቃን ደግሞ ዲግሪያቸው የሚሰጥበትን አጋጣሚን ዕንባ ጠባቂ ስላስተዋለ፣ እንዲህ የሚያደርጉ ኮሌጆች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለፓርላማ መቅረቡን ዋና ዕንባ                                                 ጠባቂው ገልጸዋል፡፡  

ዕንባ ጠባቂ ተቋም በ2015 በጀት ዓመት አስተገበርኳቸው ባላቸውን ሁለት አዋጆች አፈጻጸም፣ በኢትዮጵያ ተከስተው በነበሩ ዋና ዋና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም መግለጫ አውጥቷል፡፡

ከሸገር ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ናቸው ተብለው ከፈረሱ ቤቶች ጋር በተያያዘ፣ በቤተ መንግሥት ግንባታ (የጫካ ፕሮጀክት) ሳቢያ ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎችን በተመለከተ፣ በአማራ ክልል ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ያለ በቂ ካሳና ምትክ ተነስተናል የሚሉ ዜጎች በመበራከታቸው፣ በበጀት ዓመቱ ለተቋሙ የቀረቡ አቤቱታዎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀሩ ጭማሪ እንዳላቸው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ልዩ ልዩ ትኩረቶችን ከሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተመለከተ የወጡ መመርያዎች ውሳኔዎች በ36 ተቋማት ላይ ተደረገ በተባለ ክትትል ሥልጠና የወሰዱ ብቁ መምህራንና ምቹ አካባቢ አለመኖር፣ ድርብ የአካል ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች ታሳቢ ያላደረገ የትምህርት ሥርዓት ችግር መጉላቱን፣ በዚህም አካል ጉዳተኞች ከታችኛው ወደ ከፍተኛው የትምህርት ዕርከን የማቋረጥ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑ ተረጓግጧል ብሏል፡፡

በዝውውርና በሥልጠናዎች የሚደረግላቸው የልዩ ድጋፍ ዕርምጃ አተገባበር የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ 1064/2010ን ባላሟላ ሁኔታ እየተተገበረ በመሆኑ አድሎአዊ የሥራ ቅጥር መኖሩን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሠራተኞች እንደ ሥራዎቹ ባህሪና እንደ ጉዳታቸው ዓይነት እየተመቻቸላቸው አለመሆኑንም የተቋሙ መረጃ ያስገነዝባል፡፡   

በዜጎች ላይ በሚደርስ አስተዳደራዊ ችግር ሳቢያ በበጀት ዓመቱ 7,416 አቤቱታዎች ለተቋሙ እንደቀረቡ፣ ከእነዚህ ውስጥ 277,698 ሰዎች መካተታቸው ተመላክቷል፡፡

የቀረቡ አቤቱታዎች በዓይነት ሲታዩም ከሥራ ጋር በተያያዘ 2,235 (30.12 በመቶ)፤ አገልግሎት ባለማግኘት 1,772 (23.6 በመቶ)፣ በይዞታ ጉዳዮች 1,588 (21.4 በመቶ)፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በሚመለከት 1119 (15.5 በመቶ)፣ በካሳ ክፍያ 208 (3.3 በመቶ)፣ ከትምህርት ጋር በተያያዘ 195 (3.1 በመቶ)፣ ጡረታን በተመለከተ 158 (2.13 በመቶ)፣ በመረጃ ጥያቄ 141 (2.2 በመቶ) ናቸው፡፡

ውሳኔ እንዲያገኙ ከተደረጉ መዝገቦች መካከል በ36 መዝገቦች የተካተቱ 1,332 ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ የደረጃ ዕድገት እንዲያገኙ፣ ከአንድ እስከ አሥር ወራት የሚሆን ያልተከፈለ ደመወዝ እንዲከፈላቸው መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማም በ18 መዝገቦች ለተካተቱ 32 አቤቱታ አቅራቢዎች ካሳና ከ200 እስከ 500 ካሬ ሜትር ምትክ ቦታዎች እንዲሰጡ፣ በአሥር መዝገቦች የተካተቱ 28 አቤቱታዎች አቅራቢዎች የጡረታ መብታቸው እንዲከበር፣ በ16 መዝገቦች የተካተቱ 257 አቤቱታ አቅራቢዎች ከሕግ ውጪ የተከለከሉዋቸውን ልዩ ልዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉን መግለጫው አክሏል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከቀረቡት አቤቱታዎች በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ ጥራትና የአገልግሎት ችግር እንዳለባቸው ማረጋገጡን ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡